የአድዋ ድል የጥቁር ህዝቦችና የመላው አፍሪካ ኩራት ነው። ከዛሬ 125 ዓመታት በፊት ፋሺስቱ የኢጣሊያ ጦር ባህር ተሻግሮ፣ ድንበር ጥሶ በመጣ ጊዜ ጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን ለወሬ በማይመች መልኩ ውርደትን አከናንበው ሸኝተውታል። ባልዘመነ የጦር መሳሪያ ጠላትን ለመመከት አድዋ የዘመተው የኢትዮጵያ ጦር ታላቅ ነኝ ያለችውን ኢጣሊያን ያንበረከከው አቻ በሚባል የውጊያ ስልቱ አይደለም። የዛኔ በውስጡ ከሰነቀው አይበገሬነት በቀር በቂ የሚባል ትጥቅን አልያዘም።
ያለአንዳች መጫሚያ በባዶ እግሩ ተጉዞ በሶሎዳ ተራሮች ዙሪያ ሲተም እዚህ ግባ ከማይባል ኋላ ቀር መሳሪያውና ከጦርና ጋሻው በቀር ጠንካራ መከላከያ አልነበረውም። አባቶቻችን ትናንት በከፈሉልን መስዋዕትነት ዛሬ ላይ ቆመን የምንመሰክረውን አኩሪ ታሪክ ጽፈውልናል። በእነ እምዬ ምኒልክ ደምቆ የታተመው ጀግንነትም ከሀገራችን አልፎ ለጥቁር አፍሪካ ህዝብ የነጻነት ምልክት ሊሆን በቅቷል።
መላው አፍሪካ በቅኝ ግዛት ቀንበር በወደቀበት ዘመን ኢትዮጵያ «እምቢኝ» ስትል ታላቅ የተጋድሎ ዋጋ መክፈሏን ዓለም ያውቀዋል። ይህ መሆኑ ደግሞ ዛሬ እንደሌሎች ሀገራት የነጻነት ቀኗን ሳይሆን የድል በአሏን ለማክበር ግንባር ቀደም አድርጓታል። ይህን ተጋድሎ የውጭ ሀገራት ጸሀፍት ሳይቀሩ በበርካታ ታሪካዊ ድርሳናቸው ሲከትቡት ኖረዋል።
ከሁሉም በላይ ግን በተለያዩ የኪነ-ጥበብ ዘርፎች እየተዋዛ ሲቀርብ የቆየው የኪነ-ጥበብ አውድ ግዙፉን ታሪክ ይበልጥ አጉልቶ ለማሳየት ታላቅ አቅምን መፍጠር ችሏል።
አድዋ በሎሬት ጸጋዬ ብዕር ዋ! አድዋ
ከኪነጥበብ ማሳያዎች አንዱን ስናነሳ ደግሞ በዋናነት የሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህንን የስንኝ ቋጠሮ እናስታውሳለን። ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን አድዋን ባነሳበት ስንኙ የጦርነት ውሎውንና የተገኘውን አኩሪ ድል ለማሳየት ሞክሯል። የአድዋ ጦርነት የኋላ ታሪክ የእያንዳንዱ ኢትዮጵዊ አኩሪ ድል የሁሉ አፍሪካዊ ደማቅ ታሪክ ነው። ይህንን ሀቅ መላው ዓለም የማይዘነጋው ስለመሆኑ ደግሞ ጸጋዬ በብዕሩ አሳምሮ ከትቦታል። ሎሬቱ ከአድዋ ተራሮች ጥግ የወደቁት ጀግኖች፣ የዛሬው ትውልድ ህያው ምስክሮች ስለመሆናቸው አስቀምጧል። በአድዋ የረገፍው አጽም፣ የፈሰሰው ደምና ስለ ሀገር ሲባል የተከፈለው መስዋዕትነት ሁሌም በትንሳኤ አዲስ ሆኖ እንደሚወሳ ያሰፈረበት የተባ ብዕሩ አይረሴ ተጽዕኖውን እንዳቀለመ እስከዛሬ ዘልቋል።
«አድዋ ሩቋ፣
የአድማስ ምሰሶ አለት ጥጓ፣
ሰማይ ጠቀስ ጭጋግ ዳሷ።
አድዋ! በአንቺ ብቻ ህልውና፣
በትዝታሽ ብጽእና፣
በመስዋዕት ክንድሽ ፣
አበው ታደሙ እንደገና።
ዋ! አድዋ!
የዘር አጽመ ርስቷ የደም ትበያ መቀነቷ
የኩሩ ትውልድ ቅርሷ
የኢትዮጵያዊነት ምስክሯ አድዋ!
ከሞት የባርነት ስርዓት
በደም ለነጻነት ስለት
አበው የተሰውልሽ ዕለት
አድዋ !
የኩሩ ድል በአንቺ ጽዋ
ታድላ በመዘንበሏ
አጽምሽ በትንሳኤ ነፋስ ደምሽ
በነጻነት ህዋስ ሲቀሰቀስ
ትንሳኤዋ ተግ ሲል ሲንር ትቢያዋ ብር፣
ትር ሲል ጥሪዋ
ድው እልም ሲል ጋሻዋ
ሲያስተጋባ ከበሮዋ ዋ!
አድዋ!…»
አድዋ በእጅጋየሁ ዜማ
ስለ አድዋና ኪነጥበብ ስናወሳ እጅጋየሁ ሺባባውን /ጂጂ/ አለማሰታወስ አይቻልም። ጂጂ ልብ ሰርስሮ በሚገባው ተስረቅራቂ ድምጿ ስለአድዋ ታላቅ ተጋድሎ አዚማለች። ይህ ዜማ ዓመት አልፎ ዓመት በተተካ ቁጥር ሳይፈዝና ሳይደበዝዝ በድምቀት መሻገሩ ደግሞ ለብዘዎች አድናቆትን ያጭራል።
ጂጂ አድዋን የምትስለው በጦር አውድማው በአካልየተገኘች ያህል ተጠግታ ነው። በእርሷ አይረሴ ስዕል የተቀረጸው የጦርነት አውድም ዓመታትን ተሻግሮ በአድማጩ ልቦና ለመስረጽ ጊዜ አልፈጅበትም። ከያኒዋ የአድዋን ውሎ ስታስቃኘን ጀግኖች አርበኞቻችንን በእማኝነት ያየቻቸው ያህል እንደምስክር ሆና ነው። በጂጂ አንደበት አድዋን ስናደምጥም በአይነ ህሊናችን ጀግኖቻችንን እንድንስል ተጽዕኖ ፈጥሮብናል። በጂጂ ዜማ በኩል እነሱን ባገኘን ጊዜ የፈረሶቻቸው ኮቴ ይሰማናል፤ የሳንጃው መሞሻለቅ፣ የመድፍና መትረየሱ ጨኸት ያሸብረናል። የጥይቱ ባሩድ በአፍንጫችን እያሸተትን በድል የወደቁት ጀግኖች ድምጽ ይሰማናል። ይህኔ አሁን የቆምንባትና በነጻነት የምንራመድባት ሀገር ደምና አጥንት የተከፈለባት መሆኑ ይገባናል። ጂጂ የኋላውን ዘመን በትዝታ ጎትታ በክብር የወደቀውን የወገን አጽም ታስቆጥረናለች። የትላንቱን እውነት ዛሬ ላይ አቅርባም ህያው ታሪክነቱን እንዲህ ታሳየናለች።
«የሰው ልጅ ክቡር ሰው መሆን ክቡር፣
ሰው ሞቷል ሰው ሲያድን ሰውን ሲያከብር።
በደግነት፣ በፍቅር፣ በክብር ተጠርቶ።
በክብር ይሄዳል ሰው ሊኖር ሰው ሞቶ።
የተሰጠን ህይወት ዛሬ በነጻነት፣ ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ከአጥንት።
ስንት ወገን ወደቀ በነጻነት ምድር፣ ትናገር አድዋ ትናገር ትመስክር።
ትናገር አድዋ ትናገር አገሬ፣ እንዴት እንደቆምኩኝ ከፊታችሁ ዛሬ።
በኩራት፣በክብር፣በደስታ፣ በፍቅር፤ በድል እኖራለሁ ይኼው በቀን፣ በቀን፣ በቀን… ደግሞ መከራውን ያን ሁሉ ሰቀቀን።
አድዋ ዛሬ ናት ፣አድዋ ትናንት፤መቼ ተነሱና የወዳደቁት።
ምስጋና ለእነሱ ለአድዋ ጀግኖች፤ ለዛሬው ነጻነት ላበቁኝ ወገኖች።
የጥቁር ድል አምባ አድዋ… አፍሪካ፣ እምዬ፣ ኢትዮጵያ፤ ተናገሪ፣ተናገሪ፣ የደም ታሪክሽን አውሪ።
አድዋ በቴዲ አፍሮ ዜማ
አድዋና የመላው አፍሪካ ወርቃማ ድል ሲነሳ ታላቁን የጦር መሪ አጼ ምኒልክን እናስታውሳለን። እኚህ ስመጥር ንጉስ በሀገራቸው ላይ የዘመተውን የጠላት ጦር ለመመከት መላውን ህዝባቸውን የቀሰቀሱት በተለየ ስልትና ወኔ ነበር። አገር ወዳዱ ኢትዮጵያዊም የንጉሱን ቃል አክብሮ «እምቢኝ» ለሀገሬ ሲል ዘመቻውን ሲቀላቀል ንጉሱን ተማምኖነው።
ይህን እውነታ ወደኋላ መለስ ብሎ በታሪካዊ ምልሰት ሊያስቃኘን የሞከረው ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን /ቴዲ አፍሮ/ የምኒልክን ጀግንነትና የህዝቡን ወኔ ያቀነቀነበት ዜማው ጆሮ ገብ ሆኖ ተደምጦለታል። ቴዲ ዘመኑን በዋጀበት ድንቅ ሙዚቃ የታሪኩን እውነታ በትውስታ ለማሳየት ሞክሯል። ወራሪውን የኢጣሊያ ወታደሮችና ልበ ሙሉዎቹን ኢትዮጵያዊያን አርበኞች የጦር ሜዳ ገሀዳዊ ገጽታም በድርጊት አስቀንጭቧል። ታላቁን ንጉስ አጼ ምኒልክንም «ጥቁር ሰው» ሲል አፍሪካዊ ጀግንነታቸውን አስመስክሯል።
«ባልቻ አባቱ ነፍሶ መድፉን ጣለው ተኩሶ አባ አጤ ምኒልክ ጥንድ አርጎ ሰራው የኔን ልብ ባልቻ ሆሆ ሆሆ ሆሆ
… ጊዮርጊስ ፈረሱ ቆሞ ሳይ ድል ቀናኝ ሳልል ዋይ አባቴ ወኔውን ተኮሰው ምኒልክ ጥቁር ሰው።
ዳኛው ያሉት አባ መላ ፈት ሐብቴ ዲነግዴ ሰልፉን በጦር አሰመረው ፊት ሆኖ በዘዴ። ሳልል ዋይ ሳልል ዋይ ….
አድዋ ሲሄድ ምኒልክ ኑ ካለ አይቀርም በማርያም ስለማለ ኧረ አይቀርም በማርያም ስለማለ።
ታዲያ ልጁስ ሲጠራው ምን አለ? ዎይይይ…
ወይ ሳልለው ብቀር ያኔ እኔን አልሆንም ነበር እኔ።
ምኒልክ ጥቁር ሰው
ታላቁን የአፍሪካ ድል ለመላው ዓለም ለማስተዋወቅ ዕውቀትና ችሎታቸውን ተጠቅመው እውነታውን ያስመሰከሩ የኪነጥበብባለሙያዎች በርካቶች ናቸው። ልክ እንደቴዲ አፍሮ የሙዚቃ ሁሉ የአድዋውን ነባራዊ ሁነት ከመድረክ አውርደ አገር ያወቀው ጸሀይ የሞቀው ትዕይንት እንዲሆን ያደረጉ የቴአትር ባለሙያዎችም ታሪካዊ አሻራቸውን አሳርፈዋል።
አድዋ በአባተ መኩሪያ ተውኔት:
አድዋን በቴአትር ዘውግ ስንቃኝ ደግሞ በመጀመሪያው ረድፍ ጸሐፌ ተውኔት አባተ መኩሪያን እናገኛለን። አርቲስት አባተ መኩሪያ በ1979 ዓ.ም የአዲስ አበባን አንድ መቶኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ባዘጋጀው «ዝክረ አዲስ አበባ» የአድዋ ዘመቻን ትክክለኛ ገጽታ ለማሳየት ሞክሯል። ከስድስት ሺህ በላይ ሰዎች በተዋናይነት የተሳተፉበት ይህ አስደናቂ ትዕይንት የጦርነቱን ሁነትና የጥንቱን ሀገራዊ ወኔ ያመላከተ ነበር።
አባተ መኩሪያ «የአድዋ ጦርነት » የሚል ስያሜ በሰጠው ትዕይንት ሴት ወንዱ፣ አዛውንት ወጣቱ በበቅሎና በፈረስ ወደ ዘመቻው ሲጓዝ ይታያል። የዛኔ ካባና ጇኗቸውን ደርበው ጦርና ጋሻቸውን አንግበው ወደ አድዋ የተመሙት ኢትዮጵያውያን አሁን ላይ በደረሱበት ዘመንም ልክ እንደጥንቱ ሆነው በገሀድ ተገልጠዋል። ለሰንደቅ አላማቸውና ለውድ ሀገራቸው መስዋዕት ለመሆን ስለመዘጋጀታቸውም ተውኔቱ በድርጊት አረጋግጧል።
ጋሽ አባተ አድዋንና ሀገራዊ ስሜቱን ለማመላከት ባዘጋጀው የመንገድ ላይ ተውኔት ትዕይንቱ ቴአትር መሆኑ እስኪያጠራጥር ድረስ አድናቆት እንዲቸረው አድርጓል። በወቅቱ ዘመኑን የሚጠቁሙ ኋላቀር የጦር መሳሪያዎች፣ ወታደራዊ ትጥቅ ያልተሟላለት እግረኛ ጦር፣ ስንቅ አዝለው የሚጓዙ ሴቶች የተውኔቱ አካል ነበሩ። ጀግንነትና ሀገራዊ ስሜትን ተላብሶ ወደ ጦር ሜዳ የሚጣደፈው የዛን ዘመኑ ትውልድ በነገሪት ጉሰማ ታጅቦ የንጉሱን የክተት አዋጅ እያጣጣመ ሲጓዝ ማየትም የኪነጥበቡን ልቀት እጅግ አስገራሚ ያደርገዋል። የተለያዩ የኪነጥበብ ዘርፎች ስለ አድዋ ታሪክ ብዙ ብለዋል። የመላው አፍሪካ ድልና የጥቁር ህዝቦች ኩራት የሆነውን አኩሪ ድል ለማንጸባረቅም ሰአሊያን በብሩሻቸው፣ ጸሐፍት በብዕራቸው፣ ተዋንያን በመድረካቸው፣ ድምጻውያን በዜማቸው ቀርጸው ለትውልድ ለማስተላለፍ ሲጥሩ ቆይተዋል።
ጀግኖች ኢትዮያውን ይህን እውነት በወርቃማ መዝገብ ማስፈራቸው ያለአንዳች ምክንያት እንዳልሆነ ለማሳየት ኪነጥበብና ጥበበኞቿ ታላቁን ድርሻ መወጣታቸው ቀጥሏል። ዛሬም ቢሆን ስለአድዋ ተነግረው የማያልቁ፣ ተሰምተው የማይጠገቡ በርካታ ታሪኮች አሉን። ይህ ድል ህያው ምስክራችን ነው። አድዋ ማለት ለእኛ የነጻነታችን ምልክት የክብራችን መገለጫ ነው። በአድዋ ታሪክ ለመላው አፍሪካውያን ነጻነት ሰበብ መሆን ችለናል። ይህን ባለፈርጥ እውነታ ለሚገባው ሁሉ ለማድረስም ኪነጥበብ መቼም ቢሆን አታንቀላፋም። ጥበበኞቿም የአድዋን ተጋድሎ አጉልቶ ከማሳየት አይደክሙም፣ አይሰንፉም። ለምን ቢሉ እውነታው ነጻነት፤ ታሪኩም አድዋ ነውና።
No comments:
Post a Comment