ጥቁር ገበያ ምክንያት እና ጉዳት
የጥቁር ገቢያ (Black market)፤- ማለት በአንድ ሀገር ውስጥ በህጋዊ መንገድ አንድን እቃ ወይም አገልግሎት መግዛትም ሆነ መሸጥ ክልክል በሆነበት ሁኔታ ውስጥ ገዝቶ ወይም ሸጦ መገኘት ነው።
ለምሳሌ፤- የመሳሪያ ሽያጭ፤ የውጪ ምንዛሬ ሽያጭ፤ አደንዛዥ እጽ ሽያጭ፤ የሰው እና የሰው አካል ሽያጭ፤ እንሰሳት እና የእንሰሳት አካላት፤ ወዘተ መግዛት ወይም መሸጥ ማለት ነው።
የጥቁር ገበያ ምክንያቶች
1. በህጋዊ መንገድ ማግኘት የተከለከለ እና ከፍተኛ የሰዎች ፍላጎት ያለው እቃ ሲሆን፣
2. በጥቁር ገበያ የሚገኝ እቃም ሆነ አገልግሎት በዋጋ ደረጃ እርካሽ ስለሚሆን (ለምሳሌ፦1 ዶላር በህጋዊ ባንኮች በ39 ብር ሲመነዘር በጥቁር ገበያ 50ብር አልፏል)፣
3. ሙስና (ለምሳሌ፤- አቅርቦቱን በመደበቅ ፍላጎት ሲያድግ ጠብቆ በህገወጥ መንገድ ለመሸጥ!) ኢትዮጲያ ውስጥ የስኳር መድሃኔት፤ ሲሚንቶ፤ ነዳጅ፤ ዘይት፤ ስኳር የመሳሰሉት የመንግስት አካላት እና አቅራቢዎች ተመሳጥረው በመሸሸግ በጥቁር ገበያ በከፍተኛ ዋጋ እንዲሸጥ የሚደረግበት ሁኔታ ዜና ነው፣
4. የንግድ ስርዓቱ ህጋዊ ቢሆንም ከግብይቱ የሚጠበቅ ግብር ላለመክፈል ሲባል……..
የጥቁር ገበያ ጉዳቶች
1. መንግስት ተገቢውን ገቢ እንዳያገኝ ያደርጋል (ለምሳሌ፦ መንግስት ከህጋዊ ባንክ ቤቶች አንድ ህዶላር ለመነዘሩበት 1 ብር የገቢ ግብር ያስከፍል ከነበረና 1 ሚሊዮን ዶላር በጥቁር ገበያ ቢመነዘር መንግስት 1 ሚሊዮን ብር ገቢ ያጣል ማለት ነው)፣
2. መንግስት በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን ትክክለኛ የገንዘብ መጠን እና እንቅስቃሴ እንዳያውቅ ያደርጋል፣
3. ህገ ወጥነትን ያስፋፋል (ለምሳሌ፦ የመሳሪያ ንግድ) እንዲሁም ህጋዊ ነጋዴውን ወደ ህገወጥ ገበያ እንዲገባ ያደርጋል (ለምሳሌ፦ በህጋዊ መንገድ ኤልሲ ማሰራት 6 ወር የሚፈጅ ከሆነ እና በቀላሉ በጥቁር ገበያ የሚገኝ ከሆነ ወደ እዛ ሊሳብ ይችላል)፣ ይህ ማለት ከህጋዊው ገበያ ውጪ ያለው አቅም እየጠነከረ ከመጣ ህጋዊ ተቋማት አቅም እያጡ ስለሚመጡ ስርዓት አልበኝነት ይስፋፋል።
ለምሳሌ፦ ኢትዮጵያ የብር ኖት ለመለወጥ ከተገደደችበት ምክንያቶች መካከል አንዱ ከባንኮች ቁጥጥር ውጪ ወደ 130 ቢሊየን ብር በገበያው ማለትም በሰዎች እጅ ይንቀሳቀስ ስለነበረ ነው! ይህ ደግሞ ገበያው እና የመንግስት አገልግሎት መንግስት ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥሩ ስር እንዳይሆኑ አድርጎ ነበር።
4. በዓለም ላይ 15-18% የሚሆነው የስራ እድል ተፈጥሮላቸው የሚገኙ ሰዎች በጥቁር ገበያ ውስጥ የሚሳተፉት ናቸው። ስለዚህ የዚህ ትክክለኛ መረጃ ስለማይገኝ መንግስትም ሆነ ፖሊሲ አውጪዎች ምን ያህል ስራ-አጥ እና ሰራተኛ በአገሪቷ እንዳለ ማወቅ አይችሉም።
ለምሳሌ፦ በ2018 በሩሲያ የጥቁር ገበያው የጠቅላላ የሀገሪቷን ምርት (GDP) 20% ይሸፍን ነበር። ይህ ማለት የሩሲያ መንግስት ህጋዊ በሆነው ገበያ መፍጠር የቻለው እና በቁጥጥሩ ስር የሚገኘው ድርሻ 80% ብቻ ነው ማለት ነው።
5. ህጋዊ አምራቾች ትክክለኛው የገበያ የፍላጎት መጠንን ማወቅ አይችሉም።
በሀገራችን የጥቁር ገበያ ከጠቅላላ ሀገራዊ ምርት (GDP) ያለውን ድርሻ መንግስት ቢያጠናው ጥሩ ነው።
No comments:
Post a Comment