👉Neway Kassahu's View (መ/ር ንዋይ ካሳሁን)
ነነዌ
ወቅቱ በቤተክርስቲያናችንን አስተምህሮ በቀናት አነስተኛ የሆነችው ጾም፤ ጾመ ነነዌን የምንጾምበት ወቅት ነው፡፡ ቀኑ እንጂ ተግባሩና ትምህርቱ ግን ሰፊ ነው። ነነዌን ብዙ ጊዜ ከምንሰማውና ካስተማርነው በላይ ትልቅ ምስጢራዊና ታሪካዊ ከተማ ናት፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያና ነነዌን የምናነጻጽርበት ብዙ ገጽታ አለን፡፡
ነነዌ የአሦራውን ጥንታዊ ከተማ ስትሆን በላዕላይ መስጴጦምያ በአሁኑ አጠራር በሰሜናዊ ኢራቅ የምትገኝ ከተማ ናት፡፡ ከተማዋን ሶርያ ቱርክ ኢራን ያዋስኗታል፡፡
ከክርስቶስ ልደት በፊት በ 1800 ዓ.ዓ በኩሽ ልጅ ናምሩድ የተቆረቆረች ከተማ እንደሆነች መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ ዘፍ. 10፣ 11
በወቅቱ በአሦራውያን ግዛት ትልቋ የዓለም ከተማ ስትሆን በወቅቱ ታላቅ የሃይማኖት መዲና እንዲሁም የአሶራውያን አማልክት (ኬሽታር) ማማለኪ ስፍራ ተገንብቶባትም ነበር፡፡ ከተማዋ በተደጋጋሚ መሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ሲገጥማት የማምለኪያ ስፍራው ቢወድምም ከተማዋ እንደገና በ2260 ዓ.ዓ አካዲን በተባለው ንጉስ በድጋሚ ታንጻለች፡፡
ነነዌ በመጀመሪያ ስሟ የተጠቀሰው በዘፍጥረት 10፡11 ላይ ሲሆን የአሦር ግዛት ዋና ከተማ ነበረች፡፡ በንጉሡ ሕዝቅያስ ዘመን የይሁዳ ነቢይ የነበረው ኢሳይያስ የኖረባት፤ ሰናክሬም በ705 - 681 ዓዓ የገዛት፤ በኋላም በሁለት ልጆቹ አድራማሌቅና ሶርሶር በተባሉ ልጆቹ የተገደለባት ከተማ ናት፡፡ ኢሳ 37፡37-38
ነነዌ በአሁኑ አጠራር በሰሜናዊ ኢራቅ ከተማ ሞሱል (Mosul) በሚባል ስም ትጠራለች፡፡ በወቅቱ መቶ ሃያ ሺኽ ሰው ያኽል ይኖርባት የነበረ ሲሆን ከተማዋን ትንንሾቹን መንደሮች ጨምሮ ዞሮ ለመጨረስ ሶስት ቀን ይፈጃል።
ነነዌ በበደል ምክንያት እግዚብሔር ተቆጥቶ ሊያጠፋት ይኽንንም እንዲውቁ ዮናስን እንዲያስተምር አዘዘው፡፡ ሕዝቧ ሩህሩህ ስለነበር ከንጉሡ እስከ ሕዝቡ ሕጻናት እንስሳት ሳይቀሩ የእግዚአብሔርን ፊት ፈለጉ፣ ንሰሐ ገቡ እግዚአብሔርም ራራላቸው ይቅርም አላቸው፡፡ ነቢዩ ዮናስና ናሆም የነበረውን ታሪክ ጽፈው አቆዩልን፡፡ ነቢዩ ዮናስና ነቢዩ ዳንኤል መቃብር በዚያ የነበረ ሲሆን በአክራሪው እስልምና ISIS ሰራዊት ፈራርሷል፡፡