Saturday, 6 February 2021

ኢኮኖሚያችን እድሜው የእለት ነው!

 



እኛ ሀገር የለት የለቱን ሰርቶ የሚኖረው በርካታ ህዝብ ነው! ምክንያቱም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ መደበኛ ባልሆነው (Informal economic sector) ላይ ነው ኢኮኖሚካሊ ህይወቱ የተመሰረተው! ስለዚህ የትኛውም አይነት ብጥብጥ ከአንድ ቀን በላይ ከቆየ በልቶ የማደርን ህልውና ነው የሚያሳጣው።

ለምሳሌ፦ የቀን ሰራተኞች፤ የመንገድ ላይ ነጋዴዎች፤ ሹፌሮች እና ረዳቶቻቸው፤ ጫኝ እና አውራጆች፤ ሊስትሮዎች፤ ሎቶሪ እና ሞባይል ካርድ አዟሪዎች፤ መኪና አጣቢዎች እና ጎሚስታዎች፤ ኢንተርኔት ቤቶች፤ የጀበና ቡና እና ምግብ የሚሸጡ፤ አትክልት ሻጮች፤ ወዘተ ላይ የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ገቢያቸው በየእለቱ ነው እንጂ ከፍተኛ ቁጠባ ኖሯቸው ከሱ የሚጠቀሙ አይደሉም። ስለዚህ የትኛውም አይነት የሰዎችን መደበኛ እንቅስቃሴዎች የሚገድቡ ሁኔታዎች ግለሰባዊ ገቢን ሲያልፍ ደግሞ ጠቅላላ ሀገራዊ የምርት መጠንን ያዳክማል።

ሀገራችን ኢኮኖሚው ከሚፈልገው የስራ እድሎች አንፃር ደካማ አዳዲስ ቋሚም ሆነ ግዚያዊ የስራ እድሎችን የመፍጠር አቅም እንዳላት ይታወቃል! ይህ አይነት የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ እያለ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ቀጥሮ የሚያሰራ ኢንቨስትመንት መነሻው ምንም በሆነ ብጥብጥ ሲወድም "ወደ ኋላ ሁለት!" የሚባለው አይነት እርምጃ ነው።

መንገዶች ሲዘጉ፤ ንብረቶች ሲወድሙ ሰው ሰራሽ የዋጋ ንረት እንዲፈጠር ያደርጋል ምክንያቱም የሀገራችን ገበያዎች የዋጋ ሁኔታ የሚወሰነው በእለቱ ባለው አቅርቦት ላይ ተመስርቶ ነው! ምን ማለት ነው? ለምሳሌ፦ የሽንኩርት፤ ጎመን፤ ቲማቲም፤ ወዘተ የእለት ዋጋ የሚወሰነው ወደ ገበያ በገባው ብዛት እና የነገ አቅርቦት ሁኔታ ላይ ተመስርቶ ነው። ስለዚህ ነገ በሆነ ምክንያት መንገድ እንደሚዘጋ ከታወቀ የዛሬው የመሸጫ ዋጋ በቅስፈት ይጨምራል። የዚህ አይነቱ ሁኔታ የሚደጋገም ከሆነ ዋጋ የማይገመት እና ተፈጥሯዊ በሆነ ምክንያት ብቻ የማይመራ እንዲሆን ያደርጋል።

ለምሳሌ፦ የዛሬ 4 ዓመት የዓለም ባንክ ባወጣው ሪፖርት አዲስ አበባ ከተማ ብቻዋን የሀገሪቱን ግማሽ (50%)ጠቅላላ የሀገራዊ የምርት መጠን ወይም GDP የምታመነጭ መሆኗን አሳውቆ ነበር! ስለዚህ ከተማዋ ለአንድ ቀን መደበኛ እንቅስቃሴዎችን የሚያውኩ ሁኔታዎችን ባስተናገደች ቁጥር የሀገሪቷን ኢኮኖሚ ምን ያህል እንደሚጎዳ ማስላት ቀላል ነው።

ደካማ የዜጎች የቁጠባ አቅም ባለበት ሀገራችን ንብረት የሚወድምበት ሰው (መኪና መሰበር እና መቃጠል፤ የቤቶች መስታወት መሰበር፤ ድርጅት መቃጠል፤ ወዘት)ንብረቶችን ሊያስጠግን የሚችለው ከዝቅተኛው ቁጠባው በማውጣት አልያም በከፍተኛ ወለድ በመበደር ነው ሊሆን የሚችለው ይሄ ደግሞ ነገን ዛሬ መኖር አይነት ነው። የሚወድሙት ሰራተኛ ቀጥረው ያሰሩ የነበሩ ድርጅቶች ከሆኑ ጉዳቱ ብዙ ቤተሰቦችን የሚነካ ነው የሚሆነው። ያልዳበረ የፖለቲካ ባህል መኖር ኢኮኖሚያዊ ፍጥነትን ከሚገቱ ምክንያቶች መካከል ዋነኛው መሆኑን እያየን ነው።

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ ንግድን ለመጀመር ሀገራት ምን ያህል ምቹ እንደሆኑ በሚገልጸው Easy Business Doing Report ላይ ደካማ ጥበቃ ከሚያደርጉት ዋነኛ ሀገራት መካከል አንዷ ነች። ስለዚህ ብጥብጥ በተፈጠረ ቁጥር ድርጅቶች የጥቃት ሰለባ የሚሆኑ ከሆኑ፣ ድርጅቱ ድጋሚ ለማገገም የሚቸገር እና ተጨማሪ የኢንቨስትመንት ፍላጎት በዘርፉ ላይ እንዳይመጣ ያደርጋል።

ከውጪ ወደ ሀገራችን ኢንቨስት ለማድረግ የሚያስቡ ባለሀብቶች ለድርጅቶች የሚደረግን ጥቃት በጣም ነው በትኩረት የሚከታተሉት ስለዚህ ዜጎች ገቢ የሚያገኙበትን ድርጅት የሚያወድሙ ከሆኑ በዚህ ሀገር መዋለ-ንዋይ ማፍሰስ ላይ እርግጠኛ እንዳይሆኑ ያደርጋል። ስለዚህ በረጅም ግዜ ውስጥ የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍላጎትን ያዳክማል።

መንግስት በየትኛውም ምክንያት የሚነሱ ግርግሮች በተቻለ መጠን በፍጥነት እንዲቆም በማድረግ መደበኛ እንቅስቃሴዎች እንዲጀመሩ ማድረግ ባልቻለ ቁጥር በዕለታዊ እንቅስቃሴ ላይ የተመሰረቱ ኢኮኖሚያዊ መሰረቶች ስለሆነ ይዘን የምንቀሳቀሰው በድምር ውጤታቸው ጠቅላላ ሀገራዊ የምርት ስርዓትን ስለሚያዛንፍ ኢኮኖሚው በህመም ስር ለመቆየት ይገደዳል። በተጨማሪም ህግ ያለመከበር ምክንያት የመንግስት ተቋማት ተግባር እና ሃላፊነትን በአግባቡ በጥበብ ካለመወጣት ጋር ስለሚገናኝ ንብረታቸው የወደመባቸውን በዋናነት የኢንቨስትመንት ተቋማት መልሰው እንዲያገግሙ የማድረግ ስራዎችን ማከናወን ይጠበቅበታል (ለምሳሌ፦ አፋጣኝ ብድር ማቅረብ፤ ተለዋጭ የመስሪያ ቦታ ማቅረብ፤ ወዘተ)።

በብጥብጥ የሚደርሰው ኢሰባዊ፤ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ እንዳለ ሆኖ ኢኮኖሚው ለዜጎች ከለላ የመስጠት አቅም እንዲኖረው ሆኖ የተገነባ ባለመሆኑ እንዲሁም በአስተሳሰብ፤ በአመለካከት እና በተግባር የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን በተግባር ካለመረዳት ከቅርብ ግዜ ወዲህ በየአጋጣሚው በሚነሱ ግርግሮች በየእለቱ ኢኮኖሚያችን እንዲሞት እየተደረገ መሆኑን ሳይ ያሳዝነኛል።

No comments: