Tuesday, 4 November 2025

ብሔረ ብፁዓን


‎አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን

‎ባሕረ ጥበባት የሆነች ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን አስተምህሮዋ ሙሉ በሙሉ በመለኮታዊ መገለጥ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በሥጋዊና በደማዊ የግል አስተሳሰብና ፍልስፍና ላይ የተመሠረተ አንድም አስምህሮ የላትም፡፡ ከልዑል እግዚአብሔር ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የነበራቸው ልጆቿም ቅድስናን ገንዘብ ያደረጉ ናቸው፡፡ ቅድስናንም ገንዘብ ማድረጋቸው ሰማያዊው ምሥጢር ፍንትው ብሎ እንዲታያቸው ምክንያት ሆኗቸዋል፡፡

‎ፈጣሬ ዓለማት ልዑል እግዚአብሔር አንድ ዓለም ብቻ ሳይሆን 20 የተለያዩ ዓለማትን እንደፈጠረ የምታውቅ ብቸኛዋ የእምነት ተቋም ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ብቻ ናት፡፡ ስነ ፍጥረትን እጅግ በሚገርም ሁኔታ ተንትኖ የሚያቀርበው መጽሐፈ አክሲማሮስም ሆነ ሌሎቹ ቤተክርስቲያን ድርሳናት እንደሚያስረዱት ከሆነ እግዚአብሔር 20 የተለያዩ ዓለማትን ፈጥሯል። እነዚህም፡- 5ቱ ዓለማተ መሬት፣ 4ቱ ዓለማተ ማይ፣ 2ቱ ዓለማተ ነፋስ እና 9ኙ ዓለማተ እሳት ናቸው፡፡



‎📌 5ቱ ዓለማተ መሬት የሚባሉት ገነት፣ ብሔረ ሕያዋን፣ ብሔረ ብፁዓን፣ ይቺ የምንኖርባት ዓለም እና በርባሮስ ናቸው፡፡ የጋራ መጠሪያ ስማቸው ዱዳሌብ ይባላል፡፡

‎📌 4ቱ ዓለማተ ውሃ የሚባሉት ሐኖስ፣ ጠፈር፣ ውቅያኖስና ውኃ (ከታች የምድር ምንጣፍ የሆነው ውኃ) ሲሆኑ የጋራ መጠሪያቸው ናጌብ ይባላል፡፡

‎📌 2ቱ ዓለማተ ነፋስ የሚባሉት ደግሞ ባቢል እና ታላቁ ነፋስ ነው፡፡ ባቢል የሚባለው ነፋስ ነፋስ ከላይ ሐኖስን የተሸከ ሲሆን ረግቶ ያለ ነው፡፡ ታላቁ ነፋስ ደግሞ ከታች ከበርባሮስ ጀምሮ ይህችን ዓለም የተሸከመ ታላቅ ነፋስ ነው፡፡ የጋራ ስማቸው አዜብ ይባላል፡፡

‎📌 9ኙ ዓለማተ እሳት የሚባሉት ሦስቱ ዓላማተ መላእክት(ኢዮር፣ ራማ፣ ኤረር)፣ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት፣ ሰማይ ውዱድ፣ መንበረ ስብሐት፣ ጽርሐ አርያም፣ ባሕረ እሳት እና ገሀነመ እሳት ናቸው፡፡

‎ዓለማተ መሬት የሚባሉት የመሬት አካል የሆኑ ናቸው፣ የተፈጠሩትም ከመሬት (ከአፈር) ነው፡፡ እነርሱም ይህች ዓለም እስክታልፍ ድረስ ለሰው ልጆች የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ናቸው፡፡ ከእነዚህም ዓለማተ መሬት ውስጥ ብሔረ ብፁዓን አንዷ ናት፡፡


‎                            ብሔረ ብፁዓን


‎ብሔረ ብፁዓን ከአምስቱ ዓለማተ መሬት አንዷ ናት። ብሔረ ብፁዓን እጅግ ደስ የምትልና በዓለም ሁሉ የሚመስላት የሌለ የገነት አምሳል የሆነች ምድር ነች፤ ይህቺ ምድር የእግዚአብሔርን ፍቃድ የሚፈጽሙ የብፁዓን መኖሪያ ነች፤ መዓዛዋ በምድር ካለ ሽቱና መልካም መዓዛ ይልቅ የተወደደ ነው፤ በዚህች ምድር በገነት ካልሆነ በስተቀር የማይገኝ እንደ እርሱ ያለ የሌለ ልዩ ውኃ አለ፤ ዕፅዋቶቿም ታላላቅና ከመልካም ፍሬዎች ሁሉ በየዓይነቱ የያዙ ናቸው፣ አትክልቶቿና ዕፅዋቶቿም በዓለም ሁሉ የሚመስላቸው የሌለ ልዩ ናቸው፡፡

‎ብሔረ ብፁዓን እራሳቸውን ከዚህ ዓለም ግብር ለጠበቁ በፈቃደ እግዚአብሔር ለጸኑ ብፁዓን እግዚአብሔር ያዘጋጃት ምድር ነች፡፡ እግዚአብሔር ባወቀው ይህችን ምድር በኃጥአን ከመታወቅ መኖሪያም ከመሆን ሰውሯታል፡፡ በብሔረ ብፁዓን ከገቢረ ኃጢአት በስተቀር የጽድቅ ሥራዎች ሁሉ የሚሰሩባት የብፁዓውያን አበው መኖሪያ ነች፡፡




‎እግዚአብሔር ከፈቀደላቸው ጥቂት ቅዱሳን በቀር ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ወደ ብሔረ ብፁዓን የሄደ፣ ያቺንም ቦታ ያየ ማንም የለም፡፡ ነገር ግን በዚህ ዓለም ሳሉ ተነጥቀው ተወስደው ብሔረ ብፁዓን ከተመለከቱት ቅዱሳን ውስጥ ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስንና በዮርዳኖስ በረሃ ይኖር የነበረውቅ ቅዱስ ንጹሕ ባሕታዊ አባ ዞሲማስን መጥቀስ ይቻላል፡፡

‎በብሔረ ብፁዓን ቀንና ሌሊት እኩል ነው፤ ውርጭና ብርድ፣ ክረምትና በጋ የለም፤ ድካም መውጣትና መውረድ፣ መዝራትና ማጨድ የለም፣ ብርና ወርቅ መሸጥና መለወጥ፣ ደሃና ሃብታም የለም ሁሉም እኩል ነው፤ ለበጎ ነው ብሎ መዋሸትና ሐሰት መናገር የለም ይሄን የመሳሰለው የሰብአ ዓለም ግብር ሁሉ በዚያ የለም፡፡ በብሔረ ብፁዓን የሚኖሩ ብፁዓውያን እንደ እኛ የሚያረጅና የሚያልቅ ልብስ የሚለብሱ አይደሉም፤ ራቁታቸውን ቢሆኑም ጸጋ እግዚአብሔር ዙሪያቸውን የከበባቸውና የእርሱን ክብር የለበሱ በመሆናቸው ኀፍረታቸው አይታይም ለሚመለከታቸው እንደ ፀሐይ የሚያበሩ ናቸው፡፡ ይህም አባታችን አዳም ፈጣሪውን ሳይከዳ በገነት ሳለ ተሰጥቶት የነበረው ጸጋ ነው፡፡

‎አንበሶችና አውሬዎች ከብፁዓኑ ጋር ይኖራሉ ነገር ግን አይነኳቸውም፣ ብፁዓውያኑ ሥጋ አይበሉም የወይን ጠጅም አይጠጡም፣ አድካሚ ከሆነው ከዚህ ዓለም ከሚደረገው ምንም ምን አያደርጉም፡፡


‎ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከንጽሕት ድንግል ማርያም ሲፀነስ፣ ሲወለድ፣ ሲጠመቅ፣ መከራ ሲቀበል፣ ሲሞት፣ ሲቀበር፣ በሦስተኛው ቀን ሲነሣና ወደ ሰማያት ሲያርግ ይህንን ሁሉ መላእክት ይነግሯቸው ነበር፡፡

‎ሁልጊዜ በዐበይት በዓላትም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሄሮድስ በግፍ ከገደላቸውና ከሴት ጋር ካልረከሱ ከመቶ አርባ አራት ሺህ ሕፃናትና ከቅዱሳን መላእክት ጋር ወደ እነርሱ ይመጣል፣ በቤተ ክርስቲያናቸው መካከል ይቀመጣል፣ በእጆቹም ያቆርባቸዋል፡፡ እነርሱም ሁል ጊዜ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ይጾማሉ፣ በዘጠኝ ሰዓት በዛፎች ላይ ካለው ፍሬ የሚበቃቸውን ያህል ይወርድላቸዋል፣ ከዛፎቹ ሥር ንፁሕ ውኃ ይፈልቅላቸዋል፤ እስከሚቀጥለው ቀን ድረስ ፍሬዎቹ ወደ ዛፉ ይመለሳሉ፣ ውኃውም ይደርቃል፤ በቀጣዩ ቀን ሰዓት ሲደርስ ፍሬው ይወርድላቸዋል ውኃውም ይፈልቅላቸዋል፡፡


‎ታላቁ የጌታችን ጾም ሲደርስ የዛፍ ፍሬዎች ወደ ላይ ይወጣሉ፣ ጾም እንደ ደረሰ በዚህ ያውቃሉ እስከ ምሽትም ይጾማሉ፤ በእራት ጊዜም የሚበቃቸውን ያህል መና ከሰማይ ይወርድላቸዋል፣ ውኃም ከምድር ይፈልቅላቸዋል ከዚያም እስከ ማግስት ይደርቃል፡፡ በብሔረ ብፁዓን ብፁዓውያኑ በቅዱስ ጋብቻ ይኖራሉ፤ ቁጥራቸው ብዙ የሆኑ አረጋውያን፣ ወጣቶች፣ ሕፃናት ይኖሩባታል፡፡

‎ከብፁዓውያኑ መካከል አንዱ ሚስት ቢያገባ መጀመሪያ አንድ ጊዜ ብቻ በግብር ያውቃትና ትፀንሳለች፤ ወዲያውም ወደ ሴቶች ተመልሳ የበኩር ወንድ ልጅዋን ትወልድና አሳድጋ በሕይወቱ ሁሉ ለቤተ እግዚአብሔር አገልጋይ እንዲሆን መብዓ አድርጋ ለእግዚአብሔር ትሰጠዋለች፤ ከዚያ በኃላ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ባሏ ትመለስና አንድ ጊዜ ብቻ በግብር ያውቃትና ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ልጁ አድጎ የእናቱን ጡት መጥባት ሲተው ሦስተኛ አንድ ጊዜ ብቻ ያውቃትና ትፀንሳለች ሴት ልጅም ትወልዳለች ከዚያ በኃላ ፈጽሞ ወደ ባሏ አትመለስም እርሱም ወደ እርሷ አይደርስም፡፡ ሴቶች ከሴቶች ጋር ወንዶችም ከወንዶች ጋር ይኖራሉ ፤ ወንዶች ከሴቶች ጋር አይደባለቁም፤ ሚስቱን በፍትወት ዐይን የሚያይ ማንም የለም፤ ሚስት ያገባም ቢሆን በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ሚስቱን የሚያውቃት ሦስት ጊዜ ብቻ ሲሆን ይኸውም ሁለቱ ዘር ለመተካት አንዱ ደግሞ ለእግዚአብሔር መብዓ እንዲሆን ነው፡፡


‎በዚህ ቦታ የሚኖሩ ሰዎች 1000 ዓመት ሲሞላቸው  እንደሚሞቱ ይነገራቸዋል። መሞት ከፈለጉ ይሞታሉ መሞት ካልፈለጉ ግን ዕፀ ሕይወት የምትባል ከእርጅና የምታድስ ዕፅ አለች እሷን በልተው ይታደሳሉ። በዚያው በብሔረ ብፁዓን መኖር ከፈለጉ በብሔረ ብፁዓን ይኖራሉ። ወደሁለተኛዋ ዓለም ወደብሔረ ሕያዋን መሄድ ከፈለጉ ግን ወደብሔረ ሕያዋን ሂደው እስከ ምጽአት ድረስ በዚያ ይኖራሉ።

‎በብሔረ ብፁዓን ታናሹ ከታላቁ በፊት አይሞትም፣ ታላቁ ቀድሞ ይሞታል እንጂ፡፡ ከብፁዓውያኑ መካከል የአንዱ ጥሪው (ዕረፍተ ሞቱ) በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር መልአኩን ወደ እርሱ ይልካል ‹‹ወንድሜ ሆይ! እግዚአብሔር ወደ እርሱ ትመጣ ዘንድ ከመላእክቱም ጋር ደስ ይልህ ዘንድ ላከኝ›› ይለዋል፣ ጥሪ የደረሰው ቅዱስም ብፁዓውያኑን ሰብስቦ ‹‹ወደ እግዚአብሔር ልሄድ ነውና ደስ ይበላችሁ›› ይላቸዋል፡፡ መላእክትም ወርደው ከብፁዓውያኑ ጋር ሆነው ያንን ሰው ሕያው እንደ ሆነ ወደ መቃብሩ አብረውት ይሄዳሉ፣ ከመላእክት ጋር እግዚአብሔርን ስለ እርሱ ያመሰግናሉ፣ በመንፈሳዊ ሰላምታ እጅ ነስተው ይሰናበቱታል፤ ነፍሱ ያለ ድካም ትወጣለች፣ መላእክትም ‹‹የጻድቅ ሞት በእግዚአብሔር ዘንድ ክቡር ነው›› እያሉ ሥጋው እስኪቀበር ድረስ ያመሰግናሉ፤ በምስጋናም ነፍሱን ብፁዓውያኑ እያዩአት ወደ ሰማይ ያሳርጓታል፡፡



‎ንፋስ በነፈሰላቸው ጊዜ የገነት ዕፅዋት መዓዛን ያሸታሉ፤ መላእክትም ሁልጊዜ ሲያመሰግኑ ይሰማሉ፤ ከእነርሱም ጋር አብረው እግዚአብሔር ያመሰግናሉ፡፡ ብፁዓውያኑ እግዚአብሔር ይገልጽላቸው ዘንድ የፈለጉት ነገር ካለ ተነሥተው ወደ እግዚአብሔር በጸለዩ ጊዜ ወዲያውኑ ከሰማይ ቃል መጥቶ ለጥያቄያቸው መልስ ይሰጣቸዋል፡፡ በዓለም ያሉ ሰዎች ንጹሐንና ጻድቃን ሲሆኑ ያቃሉ በእነርሱም ደስ ይሰኛሉ እስከ መጨረሻውም ያጸናቸው ዘንድ ስለ እነርሱ እግዚአብሔርን ይለምናሉ፤ ኃጥአን በሆኑት ደግሞ አዝነው ስለ እነርሱ ያለቅሳሉ፡፡

‎ በብሔረ ብፁዓን ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ በብርሃን ደመና ተጭኖ ሄዶ አስተምሯቸዋል፤ እነዚህን ብፁዓውያን አበውን ያይና አኗኗራቸው እንዴት እንደሆነ ያውቅ ዘንድ ለዐርባ ዓመታት በጾምና በጸሎት እግዚአብሔር የለመነው ቅዱስ አባ ዞሲማስ ፍቃዱ ተፈጽሞለት ሰብአ ዓለም ዜናቸውን ሰምተው ይማሩበት ዘንድ ግብራቸውን በመጽሐፍ ጽፏል፡፡

‎ብሔረ ብፁዓን ውሸት የማይታወቅባት ኀጢአት የሌለባት ቀንም ሆነ ሌሊት ብርሃን የማይለያት ዓለም ናት።

‎አባ ዞሲማስ በንጽሕና ሆኖ በበረሃ በታላቅ ተጋድሎ የሚኖር በቅድስና ያጌጠ ታላቅ አባት ነው፡፡ ሁልጊዜም የነቢያትን፣ የሐዋርያትንና የሰማዕታትንና የቅዱሳንን መጻሕፍትን ያነብ ሕይወታቸውንም ይመረምር ነበር፡፡ እንዲህ ሆኖ ሲኖር ከዕለታት በአንድ ቀን የነቢያትን መጻሕፍት ሲያነብ በነቢዩ ኤርምያስ መጽሐፍ ውስጥ ስለ ብሔረ ብፁዓን የተጻፈ አገኘ፡፡ በዚያም ዘመን ለጣዖት የሚሰግድ ንጉሥ በተነሣ ጊዜ ሕዝቡንም ሁሉ ለጣዖት እንዲገዙ አስገደደ፡፡ በዚህም ጊዜ ነቢዩ ኤርምያስ ሕዝቡን ስለ ከአምልኮተ ጣዖት በንስሓ እንደዲመለሱ ገሠጻቸው፡፡ ዳግመኛም ካልተመለሱ እግዚአብሔር በመቅሰፍት እንደሚቀጣቸውና ለዘላለም በገሀነመ እሳት እንደሚቀጣቸው ነገራቸው፡፡ ነገር ግን እነርሱም ከኃጢአታቸው አልተመሱም ነበር፡፡ በወቅቱም እግዚአብሔርን በማመንና ሕጉን በማሰብ የታመኑትን እንደነ አሚናዳብ ያሉትን ደጋግ ሰዎች ሊመጣ ካለው መቅሰፍት እንዲድኑ ነቢዩ ኤርሚያስ ጸለየ፡፡ ጸሎቱም ተሰምቶት በወቅቱ የነበሩት ደጋግ ሰዎች ወደ ብሔረ ብፁዓን እንደተወሰዱ በመጽሐፍ ተጽፎ አለ፡፡


አባ ዞሲማስም ቅዱሳት መጻሕፍትን ሲመረምር ይህን ታሪክ ሲያነብ በብሔረ ብፁዓን ያሉ ቅዱሳንን አኗኗር ያይ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፡፡ ዳግመኛም የሐዋርያትንም መጻሕፍት በመረመረ ጊዜ ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ ወደ ብሔረ ብፁዓን ሔዶ እንዳየ አነበበ፡፡ከዚህም በኋላ አባ ዞሲማስ በጾም በጸሎት ተጠምዶ ሱባኤ ያዘ፡፡ እግዚአብሔርም ጸሎቱን ሰምቶለት መልአኩን ላከለት፡፡ መልአኩም አባ ዞሲማስን ወደ ብሔረ ብፁዓን ወስዶት በዚያ ያሉ የቅዱሳንን አኗኗራቸውንና ገድላቸውን ተመለከተ።

‎አባ ዞሲማስም  ወደዚህ ቦታ ከገባ በኋላ የብሔረ ብፁዓን ሰዎች አክብረው ተቀብለው የሚያስተምርበትን ቦታ ሰጥተው ልጆቻቸውን እንዲአስተምርላቸው ይጠይቁታል፡ እሽ ብሎ ማስተማሩን ቀጠለ፤  አንድ ቀን  የጸሎት ሰዓት ሲደርስ ሕፃናቱን ሰው መጥቶ መምህራችሁ  የት ሂዶ ነው ካሏችሁ የለም በሉ ብሏቸው ጸሎት ጀመረ። ሰዎች መጥተው መምህራችሁ የት ሂዶ ነው ብለው ይጠይቋቸዋል ሕፃናቱም ውሸት አያውቁምና እንደነሱ ሀገር የለም እንደኛ ሀገር ግን ከዚህ አለ ብለው ያለበትን ቦታ ጠቁመው አሳዩዋቸው በዚህ ጊዜ የሀገሪቱ ሰዎች ተበሳጭተው ልጆቻችን ውሸት ያስተምርብናል ብለው መልሰው ወደዚህ ዓለም ልከውታል እሱም ውሸት አይሆንም ብሎ በተናገረው  ነገር ብሔረ ብፁዓንን በዕንባ ተሰናብቷታል ፡ የተሻገረባት ዛፍ ተመልሳ ከባሕሩ ላይ እንደመሰላል ሁናለት  እኛ ወዳለንበት ዓለም እያለቀሰ ተመልሷል።

‎አባ ዞሲማስ በዚህ ንግግሩ እንዲህ ከተቀጣ እኛ በየሰከንዱ ሽርፍራፊ ወሬ ለማጣፈጥ በምንዋሸው ውሽት ቅጣታችን ምን ይሆን?

‎በመጨረሻም አባ ዞሲማስ  በረከታቸውን ተቀብሎ ወደ ምድር ተመልሶ መጠጥቶ ገድላቸውን ጽፎላቸዋል፡፡ ንጹሐን ጻድቃን የሆኑ ከጠላት ወጥመድ ያመለጡ፣ ትእዛዙን የሚፈጽሙ፣ ከመላእክት ጋር የተወዳጁ፣ ዘወትር ውዳሴና ምስጋና የሚያቀርቡ፣ ከሰዎች አኗኗር ወደ መላእክት አኗኗር የተሸጋገሩ፣ በብሔረ ብፁዓን የሚኖሩ የብፁዓውያን አበው አኗኗር ይህ ነው፡፡

‎አባ ዞሲማስ ከፍልስጤም ሰዎች ወገን ነው፡፡ ወላጆቹም ደገኛ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ አባ ዞሲማስንም በሃይማኖት በምግባር ካሳደጉት በኋላ እንዲማር ለአንድ መምህር ሰጡት፡፡ መምህሩም እያስተማረ በሃይማኖት አሳደገው፡፡ አመንኩሶም ወደ ታላቅ ተጋድሎ መራው፡፡ በገዳምም 45 ዓመታት በታላቅ ተጋድሎ ከኖረ በኋላ ቅስና ተቀበለ፡፡ ተጋድሎውንም ጨምሮ በቅስና አገልግሎት 13 ዓመት ከቆየ በኋላ በልቡ ‹‹…ከበጎ ሥራዎች ሁሉ እኔ ያልሠራሁት ምን ነገር አለ?›› ይል ጀመር፡፡ ጌታችንም ሊተወው አልወደደምና መልአኩን ልኮ ወደ ዮርዳኖስ አቅራቢያ ወዳለው በረሃ እንዲሄድ ነገረው፡፡ በዚያም ሌሎች ደጋግ አባቶችን አገኘና ከእነርሱ ተማረ፡፡ በዚያም ሳለ ወደ በረሃው ገብቶ የሚጽናናበት ነገር ይገልጥለት ዘንድ ወደ ጌታችን በጸለየ ጊዜ ማርያም ግብፃዊትን አገኛትና የ47 ዓመታት የተጋድሎ ሕይወቷንና ምሥጢሯን ሁሉ ነግራዋለች፡፡ አባ ዞሲማስም መልካም የሆነ አገልግሎቱን ፈጽሞ በ93 ዓመቱ  ሚያዝያ 9 ቀን በሰላም ዐረፈ፡፡ ረድኤት በረከቱ ይደርብን በጸሎቱ ይማረን!የብሔረ ብፁዓን ጻድቃን በሰማዕትነት ያረፉበት መታሰቢያ በዓላቸው ሚያዝያ 9 ነው፡፡ እንዲሁም የእግዚአብሔርን ምስጋናን ከአፉ ፈጽሞ የማያቋርጥ ከ45 ዓመታት ጽኑ ተጋድሎው በኋላ ወደ ብሔረ ብፁዓን ተነጥቆ ተወስዶ የቅዱሳንን አኗኗራቸውንና ገድላቸውን አይቶ የጻፈልን ታላቁ አባት አባ ዞሲማስ ዕረፍቱ ሚያዝያ 9 ነው፡፡ የብሔረ ብፁዓን ጻድቃንና የአባ ዞሲማስ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን፡፡

 

No comments: