መጥምቀ መለኮት ሳሌዳ ዮሃንስ ቤተክርስቲያን አምሓራ ሳይንት |
በደቡብ ወሎ ዞን በአምሐራ ሳይንት ወረዳ በ04 ቀበሌ ልዩ ስሙ ሳሌዳ በሚባል አካባቢ ከዞኑ ርአሰ ከተማ ደሴ 185 ኪ.ሜ ርቀት ላይ እንድሁም ከወረዳው ከተማ አጅባር በምስራቅ አቅጣጫ 5 ኪሜ ርቀት ላይ የሚገኝ ጥንታዊ ደብር ነው፡፡
ከባህር ወለል በላይ 2647 ሜ ከፍታ ላይ የሚገኝ ሲሆን የአየር ንብረት ክልሉ ደግሞ ወይነጋማ ነው፡፡ ደብሩ ከትልቅ ገደል አፋፍ ላይ የሚገኝ እና ለአይን የሚማርክ በሆነ ደን ተሸፍኖ ተመልካችን ያማልላል÷ መንፈስን ያድሳል ፡፡ የደብሩ የደን ሽፋን 10.2 ሄ ስፋት የሚሸፍን ሲሆን በውስጡ ከሚገኘው የእጽዋት ዝርያ መካከል 75 ፐርሰንት የሚሆኑት በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ናቸው ፡፡ በዚህ ታላቅ ደብር የሚገኙ የእጽዋት ዝርያ ዎችን ይህን ያህል ብሎ በዝርዝር ማስቀመጥ ከባድ ቢሆነም ዋናዋናዎቹ አንፋር ፣ እባጮ ፣ ቀጋ፣ ኮሶ ፣ ቁልቋል፣ ዋንዛ፣ ወይራ፣ ሬት ፣ጦስኝ ፣ድድሆ፣ ብሳና፣ የአበሻ ጽድ ወዘተተጠቃሾች ናቸው፡፡
በተናጠል ስናይ ደግሞ ብዙን ቁጥር የያዘው የወይራና የአበሻ ጽድ ነው፡፡ ውስጡም አመቱን በሙሉ ክረምት ከበጋ በአረንጓደ ቀለም ባሸበረቁ ትንንሽ እጽዋትና የእንስሳት ዝርያዎች በውበት ላይ ውበትን አክለው ከነፋሻው አየር ጋር ተደማምሮ በመልካቸው አእምሮው ላይ የስሜት ሀሴትን ይፈጥራል ፡፡
በዚህ የደብር ደን ውስጥ ተጠልለው የሚኖሩ በርካታ የእንሰሳትና የአእዋፍ ዝርያዎች ይገኛሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ ቀበሮ፣ ዝንጀሮ፣ ጥንቸል ፣ ጦጣ ፣ ጉሬዛ ግንዴ ቆርቁር፣ ቁራ ፣ ሰሳ፣ ሚዳቆ ፣ ድመት፣ወዘተ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ የነዚህ ታላቅ ደብር የደን ሽፋን እንድህ ለቦታው ውብ የሆነ ግርማ ሞገስን አጎናጽፎ እንድይዝ የደብሩ ነዋሪዎች በደብሩ ደን ላይ በሚያደረጉት ጥብቅ ቁጥጥር እንክብካቤ ሳይሆን ራሱ ታቦቱ በሚያሳየው ገቢር ታምራት መሆኑን የደብሩ እድሜ ጠገብ አባቶች ይናገራሉ ፡፡
የደብሩን አመሰራረት በተመለከተ ትክክልኛ የጹሁፍ ማስረጃ ባይገኝም እንኳን ከቅድመ አያቶቻችን የተቀበሉትን አፈታሪክ እንደመረጃ በመጠቀም በወቅቱ የደብሩ አገልጋይ የሆኑት ቄስ ውበቱ ታከለ እንደሚከተለው ያስረዳሉ፡-
ይህውም በአብርሀ ወጽብሀ ዘመነ መንግስት እንደ ተመሰረተና በአህመድ ግራኝ ዘመን ሚካኤል ሀብታ የተባለች የቤተ ክርስቲያን እናት የቅዱስ ሚካኤልን ታቦተ ጽላት ይዛ በመምጣት ከደብሩ በምስራቅ አቅጣጫ በሚገኛውና ›› ጋን ዋሻ› የተባለ በሚጠራው ትልቅ ዋሻ ውስጥ ለማስቀመጥ አሲዛ በመግባት በዚሁ ዋሻ ውስጥ የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሀንስን ታቦተ ጽላት እንዳገኘችውና ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሁለቱም ታቦተ ጽላት በዋሻው ውስጥ ሲገለገሉ ከኖሩና ከአህመድ ግራኝ ወረራ በኃላ ከዋሻው አውጥተው አሁን ባለበት ቦታ ላይ ህንጻ ቤተክርስቲያን ገንብተው እንደገቡም ጭምር ይገልጻል፡፡
ይህንን እውነት የሚመሰክሩ በዋሻው ውስጥ የሚገኙ የቤተመቅደስ ፍርስራሾችና የንዋየ ቅድሳት ስብርባሪዎች ጥቂት አይደሉም፡፡ ዋሻው ሁለት በሮች ያሉት ሲሆን ከዚህ ዋሻ ሲገቡ ከ2 ደቂቃ ጉዞ በኃላ ከዋሻ ጣሪያ ላይ ጠብጠብ የሚል በርካታ ደዌዎችን የሚፈውስ ጸበል ይገኛል ፡፡ ዋሻው በሚገባበት ወቅት ከዚህ መጣ የማይባል መልካም መአዛ ያለውሽታ ያጥነገንጋል ፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ መላከ ጽሀይ አዳነ ጌታነህ እንደገለጹት የዋሻው አፈር እንደ እምነትሲቀቡትና በጥብጠው ሲጠጡት ከመንፈስም ሆነ ከስጋ ደዌ ይፈውሳል ፡፡ በነዚህም መካከል ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው::
ከህንጻ ቤተ ክርስቲያን በምእራብ አቅጣጫ በስውር ይኖር የነበረ ፈዋሽ ጸበል በ1998 ዓ.ም አባ መሸ በከንቱ የተባሉ ባህታዊ አባት በወርሀ ግንቦት ከብዙ ሱባኤ በኋላ ተሰውሮ የነበረው ጸበል ተገልጦላቸው ባርከው አውጥተዋል ፡፡ የፈለቀው ጸበልም ዋናው የመጥምቀመለኮት ቅዱስ ዮሀንስ ይሁን እንጅ በሌሎች ቅዱሳን ስም የወጡ የፈለቁ ጸበሎች አሉ፡፡ እነዚህም የአቡነ ተክለሀይማኖት ፣ የቅድስት ድንግል ማርያም የመድሀኔአለም ፣የአማኑኤል ፣ የአቡየ ገ/ መንፈስ ቅዱስ ይገኙበታል::
የዚህ ታላቅ ደብር ጠበል ከሌሎች ቦታዎች ጠበል ለየት የሚያደርገው የሚጠመቀው/ የምትጠመቀው ጠበልተኛ በጣም የሚወራጭ/ አእምሮን ያሳተ / ቢሆን ተጠማቂውን /ዋን በማንም ሰው ሳይያዙና ሳይወራጩ ራሱ በፈቃዱ እስኪያበቃው ቁጭ ብሎ እንድጠመቅ ያደርገዋል ፡፡ ጸበልተኛው እየተጸበለ ሌላ በመካከል ገብቶ መጸበልም ሆነ መቅዳት አይፈቀድም ፡፡
የደብሩ አስተዳዳሪ መላከ ጽሀይ እንደሚገልጹት በአሁኑ ወቅት በዚህ ታላቅ ደብር በማንኛውም ቀን ከ20-30 ጸበልተኛ ፣የወር በገባ በ30 ደግሞ ከሌሊቱ 11፡00 እስከ ቀኑ 6፡00 የሚጸበል ደንበኛ እየተስተናገደ ይገኛል፡፡
ጠበሉ ተባርኮ አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ ይሰቃዩ ከነበረበት ደዌ ተፈውሰው ራሳቸውን የቦታው ምስክር ያደረጉ ከበሽታቸው የተፈወሱት ምዕመናን በቦታው ላይ በመገኘት ምስክርነታቸውን እንየሠጡ ይገኛሉ፡፡
ምንጭ፡- የአምሃራ ሳይንት ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤ
No comments:
Post a Comment