Tuesday, 2 March 2021

ከአድዋ ምን ተማርን? ምን አተረፍን? ምንስ እንስራ?


 


በአፄ ምኒልክና በተቀሩት ጀግና የጦር መሪዎቻቸው  የሚመራው የኢትዮጵያ ወታደር በወራሪው ጣሊያን ላይ ድል ከተቀዳጀ ይኸው 125 ዓመት ሆነው። ከረጅም ዓመታት ጀምሮ የአድዋ በዓል በየአመቱ ይከበራል። በአሁኑ ወቅት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ይህንን ታላቅ የድል በዓል ያከብራል። አገሩን ከሚወደውና አዲስ ኢትዮጵያን በጠንካራ መሰረት ላይ ለመገንባት ከሚፈልገው ጀምሮና፣ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ከውጭ ኃይሎች ጋር በማበር ዛሬ አገራችን የምናየው ውድቀት ውስጥ እንድትወድቅ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ለማበርከት ከበቃው ድረስ፣ ሁሉም በየፊናው ይህንን በዓል ያከብራል።

አድርባዩ፣ የማርክሲዝምን አርማ አንግቦ ወጣቱን ያሳሳተውና ለብዙ ሺሆች ወጣቶች መሞት ተጠያቂው እስከሆነው ድረስ፣ ካለምንም ምህረት ወጣቱን በመጨረስ የሚታወቀው ወታደራዊ አገዛዝና ሌሎች ሺህ በሺህ የሚቆጠሩ አድርባዮችና፣ የአድዋን ድል ትርጉም በደንብ ያልተረዳውና ግራ የተጋባው፣ በኢትዮጵያዊነትና በአሜሪካዊነት መሀከል የሚዋልለው ሁሉና፣ ባንዲራውን ረግጦ ከወጣ በኋላ ”የዚህች ባንዲራዬ ነገር“ እያለ ወጣቱን የሚያሳስተው ሁሉ፣ ሁላችንም አባቶቻችን በወራሪው ጣሊያን ላይ የተቀዳጁትን ድል በማስታወስ እንኮራለንም፣ እናቀራራለንም።

አባቶቻችን በአድዋ ላይ የተቀዳጁት ድል ታላቁን ቦታ ቢይዝም፣ ቀደም ብለውና በኋላም የነበሩ አባቶቻቸን አገራችንን ለመውረር የመጡ የውጭ ጠላቶችን በሙሉ እየመከቱ በመመለስ አገራችንን ከቅኝ ግዛትነት ለማዳን በቅተዋል። የአድዋን ድል ከፍተኛ የሚያደርገው አባቶቻቸን እጅግ ወደ ኋላ በቀረ መሳሪያ በመታገዝ በካፒታሊዝም አፍላ ወቅት ላይ የሚገኝና የተሻለ የአደረጃጀት ስልት የነበረውን ወራሪ ኃይል ቅስሙን ሰብረው ማባረራቸው ነው። ጣሊያን በአድዋ ላይ ከተሸነፈ በኋላ አርፎ ሳይተኛ አርባ ዓመት ያህል ከተዘጋጀ በኋላ በአውሮፕላንና በናፓል ቦንብ በመታገዝ እንደገና ሊወረን መጣ። በአጭር ጊዜ ውስጥም ድልን በመቀዳጀት ብዙ ቦታዎችን ተቆጣጠረ። በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የተማሩና አገራቸውን ለማሳደግ አዲስ ስትራቴጂ ለመቀየስ ደፋ ቀና ይሉ የነበሩትን ኢትዮጵያውያን ኃይሎችን ጨረሳቸው። ይሁንና ግን ጀግናው የኢትዮጵያ ህዝብና መሪዎቹ አንበገርም በማለት በየጫካውና በየተራራው በመመሽግና በአዲስ መልክ በመደራጀት ለጠላት አንድም ፋታ ሳይሰጡ ከአምስት ዓመት የመረረ ጦርነት በኋላ ድልን ተቀዳጁ። በአዲስ አበባ ከተማ የኢትዮጵያ ባንዲራ ተውለበለበ።

ቀደም ብለው የነበሩ ጦርነቶች፣ የአድዋና የማይጨው ጦርነት ድሎች እነዚህ ሁሉ ለኛ ከፈተኛ ትርጉም አላቸው። አባቶቻቸን በዚያን ጊዜ ባይዋደቁና ድልን ባይቀዳጁ ኖሮ ዛሬ ኢትዮጵያ የምትባለውን አገር ማየት ባልቻልንም ነበር። ስለዚህም አባቶቻችንና እናቶቻችን በውጭ ጠላቶች ላይ የተቀዳጁት ድል ለኛ ከፈተኛ ትርጉም አላቸው። ከዚህ አንፃር ስንነሳ ይህንን ታላቅ ድል በየዓመቱ ማክበር ተገቢ ነው።

ለመሆን የአድዋ ድል ትርጉሙ ምን ላይ ነው?

በእኛ በኢትዮጵያውያን ዘንድ አባቶቻችን በአድዋ ላይ የተቀዳጁትን ድል አስመልክቶ በሚገባ ግንዛቤ ውስጥ የተገባ አይመስለኝም። በመጀመሪያ ደረጃ አፄ ምኒልክ ከሞቱ በኋላ በተከታታይ ስልጣንን የተረከቡት ነገስታት፣ በተለይም ደግሞ አፄ ኃይለሥላሴ የድሉን ትርጉምነት በመገንዘብ አገራችን እንደገና እንዳትደፈር ሁለ-ገብ የዕድገት ፈለግ ለመከተል አልቻሉም። በጊዜው አፄ ኃይሥላሴ ስልጣን ከመረከባቸውም ሆነ ከተረከቡ በኋላ በአገራችን ምድር የጠነከረ፣ የነቃና የተማረ ህብረተሰብአዊ ኃይል እንዲሁም ደግሞ ኢንስቲቱሽናዊ አደረጃጀት ባለመኖሩ አገራችን ለውጭ ጠላት የተጋለጠች ነበረች። በ1928 ዓ.ም ጣሊያን ለሁለተኛ ጊዜ ሲወረን የአገራችን የህብረተሰብ አወቃቀር ፊዩዳላዊ የነበረና ህብረተሰቡም እጅግ ወደ ኋላ የቀረና ራሱንም ለመከላከል የሚችል አልነበረም። የቴክኖሎጂ መሰረት የሌለንና ከተማዎችም በስነስርዓት የተገነቡና ህዝባችንም በልዩ ልዩ የስራ ዘርፎች በመሰማራት ህብረተሰብአዊ ሀብትን ለመፍጠር ደፋ ቀና የሚል ኃይል ስላልነበረ የውጭ ጠላት አገራችን ውስጥ ሰተት ብሎ ለመግባት አመቺ ሁኔታ ተነጥፎለት ነበር።

በመጀመሪያ ደረጃ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ- ከሳይንስና ከህብረተሰብአዊ አገነባብ ታሪክ አንፃር- አፄ ምኒልክና የጦር አዝማቾቻቸው በአድዋ ላይ ድል ከተቀዳጁ በኋላ የተከተሉት የኢኮኖሚ ግንባታ በአነስተኛ ደረጃ ሲታይ የመጀመሪያው የህብረ-ብሄር (Nation-State) መሰረት ነው። ይሁንና ግን በጊዜው በነበረው በጣም የደከመ የውስጥ ኃይል አሰላለፍ፣ ዕውነተኛ ሊበራሊዝምና ሁለ-ገብ ዕድገት ሊያመጣ የሚችል ህብረተሰብአዊ ኃይል ባለመኖሩ በመጀመሪያ የተጣለው የህብረ-ብሄር ምስረታ እዚያው በዚያው ለተወሰነ ዘመናዊነትና ለአዲስ ዐይነት የፊዩዳል ኢኮኖሚ የህብረተሰብ ግኑኝነት መሰረት የጣለ ነው። በሌላ አነጋገር በጊዜው በነበረው እጅግ አስቸጋሪ የህብረተሰብ አወቃቀር የተነሳ ውስጠ-ኃይሉ ከፍ ላለና ዕውነተኛ ለውጥን ለሚፈልግ የህብረተሰብ ክፍል መንገዱን የከፈተ ሳይሆን ለፊዩዳላዊ የኢኮኖሚ ግኑኝነት (feudal relationship) ሁኔታውን ያመቻቸ ነው ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። ይህ አዲስ የተፈጠረው ሁኔታ ከፊዩዳል የእርስ በርስ ሽኩቻና ተንኮል ጋር ተደምሮ ኢትዮጵያችን ጃፓን የተከተለችውን በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሁለ-ገብ የህብረ-ብሄር ግንባታ ልታራምድ አልቻለችም። በዚህም ምክንያት ለጊዜው የህዝብ አስተሳሰብና አመለካከት ወደ ማዕከላዊ መንግስቱ ጋ ቢሆንም በተዝረከረከ መሰረት ላይ የተነጠፈው ኢኮኖሚያዊ ክንዋኔ ህዝቡን እንደ አንድ የጠነከረ ኃይል ሊያሰባስበው አልቻለም።

እንደሚታወቀው አንድ ህዝብና አመራር ከውጭ የሚመጣበትን ጠላት መክቶ የሚመልሰው እጁን አጣጥፎ በመቀመጥ ለሌላ ጦርነት መዘጋጀት ሳይሆን ቶሎ ቶሎ ብሎ ሰፊ መሰረት ያለውና የጠነከረ ኢኮኖሚ በመገንባት እንደ አንድ ነፃ ህዝብ በመታየት ተከብሮ ለመኖና ለተከታታዩ ትውልድ አስፈላጊውን ቅድመ-ሁኔታዎች አንጥፎ ለመሄድ ይችል ዘንድ ነው። ከዚህም በላይ የተሻለ የጦር መሳሪያ በማምረትና ከውጭ ኃይል ነፃ የሆነ ወታደራዊ ኃይል በማቋቋም የድሮውም ሆነ አዲስ ወራሪ ኃይል ሲመጣ በዘመናዊ የጦር ስልት በመደራጀት ጠላቱን ለማባረርና እንደገና እንዳይቃጣ ቀጥቶ ለመመለስ ነው። በዚህ ረገድ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን ለማምረትና ተደራጅቶ ለመገኘት የግዴታ ሳይንሳይና ቴክኖሎጂ የሚጫወጡት ከፍተኛ ሚና አለ። በሳይንስና በቴክኖሎጂ ያልተደራጀ፣ እርስ በርሱ የተያያዘ ኢኮኖሚ የሌለውና፣ ከተማዎች በተለያዩ የመገናኛ መስመሮች ተያይዘው የማይገኙበት አገርና ውስጠ-ኃይሉም የተዳከመ ህብረተሰብ፣ እንዲሁም ደግሞ በሳይንስ በሚገለጽ ባህል ያልዳበረና ያልበለጸገ ህዝብ የግዴታ በውስጥም ሆነ በውጭ ኃይሎች መጠቃቱ የማይቀር ነው። ከዚህ ስንነሳ አገራችን ከአንዴም ሆነ ከዚያ በላይ መወረሯና ዛሬም ያለችበት የውስጥ መዳከምና መቦርቦር ዋናው ምክንያት በውስጥ የሰለጠነ ህብረተሰብአዊ ኃይል ብቅ ማለት ባለመቻሉ ነው።

የአድዋ ድል ለህብረ-ብሄርና ለህብረተሰብ ግንባታ 

የመጀመሪያው ደረጃ ቢሆንም ይህንን ድል በጸና መሰረት ላይ ለማቆምና በየጊዜው እያደሱ በመሄድ ተከታታይነት እንዲኖረው ለማድረግ የሚችል ብሄራዊ ባህርይ ያለው አገር ወዳድና የሰለጠነ ኃይል ኢትዮጵያችን ልታፈራ አልቻለችም። በመሆኑም የሶስት ሺህ ዓመት ታሪክ አለን ብንልም፣ የወጭ ጠላትን እየደጋገምን መክተን ለመመለስ ችለናል ብለን ብንዝናናም፣ በሌላ ወገን ደግሞ የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት እኛን የሚያዝናናን አይደለም። ድህነትና ረሃብ፣ መሰደድና መዋረድ፣ በራስ አለመተማመንና የውጭ ኃይሎችን መለማመጥ፣ እንዲሁም ደግሞ ወደ ውስጥ ህብረተሰቡን የሚሰበስብ ዕውነተኛ ህብረተሰብአዊ ለውጥ እንዳይመጣ በተለያዩ መልኮች ተንኮል መስራትና እንቅፋት መሆን፣ ለውይይትና ለዲሞክራሲያዊ ክርክር ዝግጁ አለመሆን፣ ከዚህም በላይ ሳይንስና ቴክኖሎጂን መጥላት ዋናው መለዮቻቸን በመሆንና ርስ በርስ በመጠላለፍ የምንታይና የዓለም ህዝብ የሚሳለቅብን አገር ለመሆን በቅተናል። ከ125 ዐመት ታላቅ ድል በኋላ የተከበርን ሳንሆን የሚሳቅብንና የምናፍር ሆነናል።

ከሌሎች አገሮች መማር የነበረብን ጉዳይ!

በታሪክ ውስጥ እኛ ብቻ ሳንሆን በጊዜው ከውስጥ ጠንካራ የኢኮኖሚ መሰረትና የነቃ የህብረተሰብ ኃይል የሌላቸው አገሮች በሙሉ ከአንዴም ሁለቴም በውጭ ኃይሎች በመወረርና በመዳከም የመጨረሻ መጨረሻ ከስህተታቸው ትምህርት በመቅሰም እንደገና ጠላት እንዳያጠቃቸው አስፈላጊውን ሳይንሳዊ እርምጃ ለመውሰድ ተገደዋል።

ጀርመን

ጀርመን ወደ አንድ ህብረ-ብሄር ከመጠቃለሏ በፊት፣ በስዊድን፣ በዴንማርክ፣ በአውስትሪያና በፈረንሳይ በመወረር ግዛቶቿ በሙሉ በእነዚህ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ነበሩ። በጊዜው የነበሩ መሳፍንታዊና ፊዩዳላዊ አገዛዞች ከራሳቸው ጥቅም ባሻገር ማየት ባለመቻላቸው ጀርመን እየደጋገመች የምትጠቃ አገር ነበረች። በ18ኛው ክፍለ-ዘመን ትንሽ ጠንከር ብሎ ይታይ የነበረውና ዘመናዊነትን ለማምጣት ከፍተኛ ፍላጎት የነበረው የፕረሽያ አገዛዝ ይህንን ውስጣዊ ድክመት ከተገነዘበ በኋላ የወሰደው እርምጃ በአካባቢው በሳይንስ ላይ የተመሰረተ ጥገናዊ ለውጥ ተግባራዊ በማድረግና አልገበርም ያሉትን ኃይሎች ደግሞ በማስገደድና በማሸነፍ ኃይሉን ካጠናከረ በኋላ የኋላ ኋላ በአውስትሪያና በፈረንሳይ ላይ ድልን ለመቀዳጀት ቻለ። አገዛዙም በዚህ ሳይዝናና በእልክና በዕውቅ ወደ ውስጥ ሁለ-ገብ የአገር ግንባታ ማካሄድን ዋናው ተግባሩ አድርጎ ወሰደ። በዘመኑ ስልጣን ላይ የነበሩት ታላቁ ፍሬድሪክ ሁለተኛው በጊዜው ሰፍኖ ከነበረው የባህልና የኢኮኖሚ ድክመት ለመውጣት ምክር ይጠይቁ የነበረው እንደነ ቮልቴር ከመሳሰሉት ፈላስፋዎች ነበር። ፈላስፋው ቮልቴርም ታላቁን ፍሬድሪክ ሁለተኛውን የመከራቸው ሳይንስንና ጥበብን በማስገባት ነው ወደ ሁለ-ገብ ዕድገት ማምጣት ይቻላል ብሎ የመከራቸው። በዚህም መስረት አገዛዙ የውስጥ ገበያን ለማዳበርና በጠንካራ መሰረት ላይ ለመገንባትና ህዝቡም ብሄራዊ ስሜት እንዲኖረው ጥበባዊ ከተማዎችንና መንደሮችን ነው መገንባት የጀመረው። ይህ ዐይነቱ በመንግስት የተደገፈ የአገር ግንባታ አዳዲስና ጠንካራ ኃይሎችን በመፍጠር በራሱ ኃይል እንዲንቀሳቀስ በሩን ከፈተለት። መንግስት ባነጠፈው ሁለ-ገብ የኢኮኖሚና የህብረተሰብ ግንባታ ከመንግስት ቁጥጥር ውጭ የወጡ አዳዲስ ኃይሎች በመፈጠርና በውድድር ዓለም ውስጥ በመሽከርከር ለፈጠራ ስራ አመቺ ሁኔታን አዘጋጁ። ቴክኖሎጂዎችን በመኮረጅና የምርምርና የዕድገት እንዲሁም ደግሞ የሳይንስ አካዳሚ በማቋቋም ካፒታሊዝም በጸና መሰረት ላይ እንዲገነባ ተደረገ። ጀርመን ወደ ህብረ-ብሄርና ወደ ተሳሰረ የኢኮኖሚና ህብረተሰብ እንድትሸጋገር አስፈላጊው እርምጃዎች ቀስ በቀስ በአገር ደረጃ ተወሰዱ። የፊዩዳል አስተሳሰብ የነበራቸው ኃይሎች በተፈጠረው አዲስ ሁኔታ በመሸነፍ ሳይወዱ በግድ የህብረ-ብሄርን መሰረተ ሃሳብ በመቀበል ጀርመን በ1871 ዓ.ም በአንድ አገዛዝና ባንዲራ ስር ልትገዛ ቻለች። ይህ ሁኔታ በማያሻማ መልኩ የጀርመንን ዕድገት አፋጠነው። ጀርመን በአጭር ጊዜ ውስጥ እንግሊዝንና ፈረንሳይን ቀድማ ለመሄድ ቻለች። ለጀርመን የሁለ-ገብ ዕድገት የሚያመቹ እንደ ፍልስፍና፣ ጥበብና ወደ ብሄራዊ ቲአትር የሚሸጋገር ድራማዎች ቀደም ብለው በታላላቅ ምሁራን ተዘጋጀተው የሚሰራጩ ስለነበር አዲስ ብቅ ላለው የከበርቴው መደብ ሁለ-ገብ ዕድገትን ለማምጣትና ከክልሉ ወጣ ብሎ ለማሰብ የሚያስቸግረው ምንም ነገር አልነበረም።

ጃፓን 

ከዚህ የአገር ግንባታ ትምህርት የቀሰሙት ራሽያና ጃፓን አስፈላጊውን ቅድመ-ሁኔታዎች በማነጠፍ ነው ከውጭ የሚመጣባቸውን ጠላት ለመከላከል የቻሉት። በ19ኛው ክፍለ-ዘመን ጃፓን በወጭ ኃይሎች የተከበበች ስለነበር ከዚህ ውርደት ለመላቀቅ በጊዜው ስልጣኑን የተቀዳጀው የሜጂ ዲናስቲ የተከተለው የኢኮኖሚ ፖሊስ በተለይም ከጀርመንና ከአሜሪካን የአገር አገነባብ ስልት በመቅሰም በነሱ መሳሪያ እነሱን መልሶ መዋጋት ያስፈልጋል በሚለው ስልቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ የቴክኖሎጂ ባለቤት በመሆን የቅኝ ግዛት ሰለባ ከመሆን ተረፈ። በዚህም መሰረት ጃፓን በአጭር ጊዜ ውስጥ በቴክኖሎጂ በማደግ ዛሬ የደረሰችበት የዕድገት ደረጃ ለመድረስና የተከበረች አገር በመሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ በቴክኖሎጂዎች ሌሎችን አገሮች ለመወዳደር የምትችል አገር ለመሆን በቃች።

ራሽያ

የራሺያንንም ሁኔታ ስንመለከት አካሄዱ ሙሉ በሙሉ እንደጃፓኑ ባይሆንም ዋናው ዓላማው ቀስ በቀስ ለህብረ-ብሄር የሚያገለግል የኢኮኖሚ መሰረት መጣልና ራስን መቻል ነበር። በመጀመሪያ ደረጃ ራሽያን ዘመናዊ የማድረጉ ጉዳይ በታላቁ ፔተርና በታላቋ በንግስት ካታሪና ሁለተኛዋ የተጀመረ ሲሆን፣ በዚያን ጊዜ በተወሰደው የዘመናዊነት ፖሊሲ የተነሳ አያሌ የሊትሬቸርና የሙዚቃ እንዲሁም በማቲማቲክስ የሰለጠኑ ምሁራንን ማፍራት ተቻለ። ይህ በራሱ ብሄራዊ ስሜትን በማዳበር ለቲአትርና ለክላሲካል ሙዚቃ በሩን በመክፈት ራሺያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ትልቅ አገር ለመሆን ቻለች። ይሁንና ግን ራሺያ በስፋት በጣም ታላቅ አገር በመሆኗና፣ ይህ የጥገና ለውጥ ለከበርቴው መደብ መዳበር መንገዱን የከፈተ ለመሆን ባለመቻሉ ካፒታሊዝም በሚያረካ መልክና ወደ ውስጥ የውስጥ ገበያን ሊያዳብር በሚችል መልክ ሊስፋፋ አልቻለም። በዚህም ምክንያት የተነሳ ዘመናዊነትና ፊዩዳል ሪሌሽን ሺፕ እዚያው በዚያው የነበሩ የህብረተሰብ ግኑኝነቶች ነበሩ። ይህ ዐይነቱ ውስጣዊ የህብረተሰብ ቅራኔ መኖርና ራሺያ ወደ ሊበራሊ ዲሞክራሲ ለመሸጋገር አለመቻል የግዴታ ለኦክቶበር አብዮት በሩን መክፈት ቻለ ማለት ይቻላል። በሌላ አነገጋር የኦክቶበር አብዮት በጊዜው ታሪካዊ ግዴታ ነበር ማለት ይቻላል። ወደ ውስጥ ድህነትንና ኋላ-ቀርነት ለማስወገድ የሚችልና ዘመናዊነትን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሊያደርግ የሚችል ኃይል በአጭር ጊዜ ውስጥ ብቅ ለማለት ባለመቻሉ የኦክቶበር አብዮት መካሄድ ታሪካዊ ግዴታ ሆነ።

ራሺያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተከፈተባት የመጀመሪያው ዓለም ጦርነት በኋላ እነ ሌኒን ከስህተታቸው በመማር ተግባራዊ ያደረጉት ለገበያ ኢኮኖሚ የሚያመች አዲስ ባለ አምስት ነጥብ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነበር። ይሁንና ግን ሌኒን ከሞተ በኋላ በእነስታሊን የተወሰደው በኃይል ላይ የተመሰረተ የእርሻ አደረጃጀት ሂደት በተለይም በገበሬው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል ችሏል። በተጨማሪም ስታሊን የውጭ ስላዮች ጋር ተባብረው ይሰራሉ ያላቸውን ምሁራንና የትግል አጋሮችን እንደገደለ ለዚህ ጸሀፊ ግልጽ ነው። ስታሊን በወጭ የስለላ ድርጅቶች አማካይነት በተሰነዘረበት ፕሮፖጋንዳ በመደናገር ወዳጁን ከጠላቱ ለመለየት ያልቻለበት ጊዜ ነበር። ያም ሆነ ይህ የእነ ስታሊን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ዋና ዓላማው በኮሌክቲቫይዜሽን አማካይነት ራሺያን በፍጥነት ወደ ኢንዱስትሪ አገርነት መቀየር ነበር። በዚህም መሰረት በተለይም በ1930ዎቹ ዓ.ም ውስጥ ራሺያ ከፍተኛ የኢንዱስትሪ ግንባታ በማካሄድና ከተማዎችን በመገንባት ራሷን ከውጭ ጣለት ለመከላከል የሚረዳትን መሰረት ጣለች። ይህንን የተመለከቱት የውጭ ጠላቶች ሌላ እነሱን የሚቀናቀን ኃያል መንግስት እንዳይነሳ በጦርነት ለመጥመድና ድምጥማጡን ለማጥፋት ስትራቴጂ ቀየሱ። በተለይም የአሜሪካና የእንግሊዝ የስለላ ድርጅቶችና እንዲሁም ታላላቅ ኩባንያዎች ሂትለር በራሺያ ላይ ጦርነት እንዲከፍት በመደገፍ ራሺያን ወደ ዲንጋይ ዘመን ለመለወጥ የሚያስችል ስትራቴጂ ቀየሱ። በእነስታሊን የሚመራው ጦርና አገር ወዳዱ የራሺያ ህዝብ ግን ይህንን ከውጭ የመጣበትን ጠላት ለመቋቋም ቆራጥ ትግል አካሄደ። የመጨረሻ መጨረሻም ራሺያ በአጭር ጊዜ ውስጥ አንድ ሺህ ታንኮች በማምረትና በጦርነት ላይ በማሰማራት የወራሪውን የጀርመንን ጦር አወደመቺው። ከሁለተኛ ዓለም ጦርነት በኋላ እነስታሊን የወደሙ ከተማዎቻቸውን በአጭር ጊዜ ውስጥ መልሰው መገንባት የቻሉት ባዳበሩት የአደረጃጀት ልምድና ውስጣዊ የአገር ፍላጎት ጋር በማጣመር ነው። ይህ የሚያሳየው ምንድን ነው? ተከታታዩ የራሺያ መሪዎች ለአንድ አገር ዋናው መሰረትና አንድ አገር እንደ አገር እንዲጠራና ህዝቡም እንዲከበር ከተፈለገ ጠቅላላው አገር በጸና ቴክኖሎጂያዊ መሰረትና ከተማዎች ላይ መገንባት እንዳለበት ነው። ስለሆነም በ1950ዎቹና መጨረሻና በ1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ ሶቭየት ህብረት ለሳይንስ ቁልፍ ቦታን በመስጠት ከካፒታሊስት አገሮች ቀድማ በመሄድ የሰውን ልጅ ህዋ ላይ ለመላክ ቻለች። ከዚያ በኋላ ነው አሜሪካ በመደናገጥ ያለ የሌለ ኃይሏን በማንቀሳቀስና በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ሳይንቲስቶችን በማሰማራት ተንኮርኳሪ ኃይል በመስራት ወደ ህዋ ለመብረር የቻለችው። ሰሞኑን The Hidden Figures በሚለው ፊልም እንዳየነው በተለይም ጥቁር አሜሪካዊያን ሴቶች ለቴኮኖሎጂ ዕድገትና ለበረራው መሳከት ከፍተኛውን ሚና እንደተጫወቱ እንረዳለን።

ቻይና

ወደ ቻይናም ስንመጣ ተመሳሳይ ታሪክን እንመለከታልን። ቻይና በጃፓን መወረሯ ብቻ ሳይሆን ቻይናን ከውስጥ ለማዳከምና የህብረተሰቡን መንፈስ ለመበረዝና ጠንካራ ባህል እንዳይኖረውና ታላቅ አገር አንዳይገነባ በተለይም እንግሊዝ የኦፕየም ጦርነት በማወጅ አስቸጋሪ ሁኔታ ፈጥራ ነበር። ይሁናን የኋላ ኋላ በታላቁ መሪ በማኦ ሴቱንግ የሚመራው የኮሙኒስት ፓርቲ በመደራጀትና የተቀነባበረ የጦር ትግል በማካሄድ በ1949 ዓ.ም የጃፓንን ወራሪ ኃይል ለማባረርና ነፃ አገር ለመመስረት ችለዋል። በመሀከሉ አያሌ ስህተቶች ቢሰሩም ቻይና ሌሎች አገሮችን ሳትበዘብዝና ችግር ሳትፈጥርባቸው ወደ ውስጥ ያተኮረ ግንባታ በማካሄድ የኋላ ኋላ ለተካሄደው የገበያ ኢኮኖሚ ጥገናዊ መሰረት ልትጥል ችላለች። ብዙ ጥናቶች እንደሚያረጋግጡት ከሆነ በኮሚኒስት ፓርቲ የሚመራው የቻይና መንግስት ከ1950-70ዎች ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ ውስጥ ድርጅታዊ ስራዎችን ባይሰራና ህዝቡን ለአገር ግንባታ ስራ ባያንቀሳቅስ ኖሮ የኋላ ኋላ በገበያ ኢኮኖሚ ላይ የተመሰረተ ጥገናዊ ለውጥ ለማድረግ አይችልም ነበር። ይሁንና ግን በ1950ዎቹ ዓ.ም የተሰሩት ስህተቶችና የባህል አብዮት የሚባለው መካሄድ ከፍተኛ ህዝባዊ እልቂትን ማስከተሉ የማይካድ ሀቅ ነው። እንደዚህ ዐይነቱ ህዝባዊ ዕልቂት በተለያየ መልክ በካፒታሊስት አገሮችም የተካሄደ ጉዳይ ነው።፡ ማንኛውም የካፒታሊስት አገር እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰው የትምህርት ቤት የኢኮኖሚክስ መጽሀፍ ለማሳመን እንደሚሞክረው በረቀቀው የሰው እጅ (Invisble Hand) አማካይነትና በጠያቂና በአቅራቢ መሀከል ባለው የኢኮኖሚ ግኑኝነት ላይ በመመስረት ሳይሆን ህዝብን ለታላላቅ ስራዎች በማሰማራትና ገበሬውን ከቀየው በማፈናቀልና ወደ ኢንዱስትሪ ስራተኛነት በመቀየር ነው። በዚህ መልክ ካፒታሊዝምን እንደ ኢኮኖሚ ቅንጅት ለማዳራጀትና አገራዊ ባህርይ እንዲኖረው ለማድረግ በተለያዩ የምዕራብ አገሮችና በአሜሪካን ምድር ከፍተኛ የሆነ ብዝበዛ ተካሂዷል። ለካፒታሊዝም አጠቃላይ የሀብት ክምችትና ዕድገት በተለይም የአፍሪቃና የላቲን አሜሪካ አገሮችም ከፍተኛ አስተዋፅዖ አበርክተዋል። ከዚህ ስንነሳ በማንኛውም አገር በአፍላው ወቅት እንደሚባለውና ለማሳመን እንደሚሞከረው ካፒታሊዝም በፈቃድና በህግ የበላይነት ላይ በመመርኮዝ የተገነባ ስርዓት ሳይሆን በኃይል አማካይነት እንደሆነ ብዙ ኢምፔሪካል ጥናቶች ያረጋግጣሉ። እጅግ ብልህነት በተሞላበት መንገድ አጭሩን መንገድ የተከተሉት ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ ብቻ ናቸው ማለት ይቻላል።

ከሀገሮች የምንማረው ነጥብ

ያም ሆነ ከነዚህ አገሮች መወረርና ወድቆ መነሳት የምንማረው አንድ ሀቅ ነገር አለ። ጠንካራና የተገለጸለት እንዲሁም ደግሞ አገር ወዳድ መሪ ወይም አመራር የሌለው አገር አስር ጊዜ ጠላትን መክቶ ቢመልስም የመጨረሻ መጨረሻ ተዝረክርኮ ነው የሚቀረው። በተለይም ደግሞ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሰፋ ያለ የውስጥ ገበያ የሌለው አገር እየደጋገመ በውጭ ጠላት እንደሚጠቃ ነው። በቀጥታ ባይወረርም የመጥፎ ባህል ሰለባ በመሆን እየተሽመደመደ እንዲኖር ይገደዳል። የፈለገውን ያህል የተፈጥሮ ሀብት ቢኖረውም የፖለቲካ ኢኮኖሚክስን ህግ በደንብ ያልተገነዘበ ወይም ሊገነዘብ የማይችል ኃይል ቢያንስ እንኳ ለህዝቡ መሰረታዊ የሆኑ ነገሮችን፣ እንደመጠለያ፣ ንጹህ ውሃ፣ የተሟላ ምግብ፣ ህክምናና መሰረታዊ ትምህርት የመሳሰሉትን ሳያዘጋጅ ነው የሚያልፈው። ማኦ ሴቱንግ እንዳሉት ለሁለተኛ ጊዜ የኢትዮጵያ ህዝብ ጣሊያንን ድል ቢያደርገውም ትክክለኛ አመራር ለማግኘት ባለመቻሉ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ አገራችን በቀላሉ የኢምፔሪያሊስት አገሮች ሰለባ ለመሆን በቃች። ቀስ በቀስ የምትቦረበርና የምታደከም አገር ሆነች።

በአፄ ኃይለሥላሴ አገዛዝ ዘመን የተሰሩ ስህተቶች!!

አፄ ኃይለሥላሴ ከስደት ከተመለሱና ስልጣናቸውን ካደላደሉ በኋላ ጣሊያን በገነባው ላይ ከመቀጠል ይልቅ የኋሊት ጉዞ ነው የጀመሩት። የተንኮታከተውን የፊዩዳል ስርዓት መልሶ በመገንባት አገራችን የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት እንዳትሆን አደረጉ። ዘመናዊና ለሁለ-ገብ ግንባታ የሚያመች ትምህርት ከማስገባትና ከማስፋፋት ይልቅ የተዝረከረከ ትምህርት በማስፋፋት ብሄራዊ ስሜቱ የተኮላሸና ዕድገትን የሚቀናቀን ብቻ ሳይሆን ሰፊውንም ህዝብ የሚንቅ ቢሮክራሲያዊና ቴክኖክራሲያዊ፣ እንዲሁም ለውጭ ኃይሎች የሚያጎበድድ ህብረተሰብአዊ ኃይል ብቅ እንዲል አደረጉ። 

ማርክስ የሚለው የማቴሪያሊስት ቲዎሪ እዚህ ላይ ነው በደንብ የሚሰራው። ምክንያቱም ማንኛውም ብቅ የሚል አዲስ የህብረተስብ ክፍል መሬት ላይ ከተነጠፈው የማቴሪያል ሁኔታዎች ባሻገር ሊመለከትና ሊያስብ በፍጹም አይችልም። ሰፋ ያለ የማቴሪያል መሰረት የሚጣልለት ህዝብና ከዚያ የሚፈልቀው አዲስ የህብረተሰብ ክፍል ልክ እንደ ምዕራብ አውሮፓ፣ የኋላ ኋላ እንደ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ ኢንደስትሪየስ ይሆናል። በስራና በዲሲፕሊን የሚያምን፣ በስራ አማካይነት ብቻ ዕውነተኛ ህብረተሰብአዊ ሀብት የሚፈጠር መሆኑን ስለሚገነዘብ ሳይወድ በግድ አስፈላጊውን በአገር ውስጥ የሚገኙ የተፈጥሮ ሀብትንና የሰውን ኃይል ሊያንቀሳቅሱ የሚችሉ ኢንስቲቱሽናዊና ሌሎች ቅድመ-ሁኔታዎችን ይወስዳል። በዚህም መሰረት ለብሄራዊ ኢኮኖሚ ግንባታ የሚያመቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል። ያልታደለችው አገራችን ግን ይህንን ዕድል ለማግኘት በፍጹም አልቻለችም። አገዛዙ ከዚህም በላይ ለሁለ-ገብ የአገር ግንባታ የማያመች የኢኮኖሚ ፖሊስ በመከተሉ የተነሳ በከተማና ከሰማንያ በመቶ በላይ በሚቆጠረው በሰፊው የገጠር ኗሪ ህዝብ መሀከል ልዩነት እንዲፈጠር አደረገ። ፖሊሲው የአገርን የሰውንና የተፈጥሮን ሀብት ለማንቀሳቀስ የማይችልና ዕውነተኛ ብሄራዊ ሀብት እንዳይፈጠር የሚያግድ በመሆኑ ድህነትን አስፋፋ። ፖሊሲው የባሰውኑ ለተዝረከረከ የኢኮኖሚ ክንዋኔ መንገዱን በማመቻቸት ይህ በራሱ የፈጠራ ስራ እንዳይኖር አገደው። ራሱ በከተማ ውስጥም ያለው ልዩነት ከፍተኛ በመሆኑ ከተማዎች የሴተኛ አዳሪዎችና የማጅራት መቺዎች መፈልፈያ ለመሆን በቁ። ከዚህም በላይ በራሳቸው ጥረት ለማደግ የተነሳሱ ግለሰቦች ርዳታና ምክር ባለማግኘታቸው የግዴታ ወደ አቀባባይ ከበርቴነት እንዲሰማሩ ተገደዱ። በዚህም ምክንያት የተነሳ አዲስ የአመራረት ስልትና ሳይንሳዊ ግኝትን ከማዳበር ይልቅ የፍጆታ አጠቃቀም በመስፋፋቱ የተነሳ እጅግ በውስን ደረጃ ይገኝ የነበረው የውጭ ምንዛሬ ባልባሌ ቦታ ላይ እንዲባክን ተደረገ። በተጨማሪም በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን አንድ ባህላዊ ከተማ እንኳ መገንባት ባለመቻሉ አገራችን በባህል እድገት ሊኖራት የሚችለው እምርታ ተቀጨ። በአንፃሩ ግን ጣሊያን አምስት ዓመት ያህል ጠቅላላውን ኢትዮጵያ ሲወርና ሲገዛ በአምስት ዓመት ውስጥ እንደ ጂማ የመሳሰሉትን ሁሉንም ነገር ሊያሟሉ የሚችሉ ከተማዎችን መገንባት ችሏል። አብዛኛው ባህል የሚባለው ነገር በተወሰነ ደረጃ አዲስ አበባ የተወሰነ አካባቢ ብቻ የሚሽከረከር ነበር። በዚህም ምክንያት የተነሳ ህዝባችን እንደ አንድ ህዝብና ውስጠ-ኃይሉ እንደ ጠነከረ ኦርጋኒዝም ሊተሳሰርና ብሄራዊ ስሜቱ ሊዳብር አልቻለም። በአገዛዙና በቢሮክራሲው እንክብካቤ የማይደረግለትና የሚናቅ ህዝብ እንዴትስ አድርጎ ብሄራዊ ስሜቱ ሊዳብር ይችላል? በጊዜው የነበረው ድህነትና የአገራችን ወደ ኋላ-መቅረት ያሳሰባቸው አንዳንድ ባለስልጣናት የጥገና ለውጥ እንዲደረግ ለአፄው ምክር ቢያቀርቡም ከሳቸው የሚሰጠው መልስ ”ህዝባችንን እናውቀዋለን“ የሚል ነበር። በሌላ አነጋገር ባለው ሁኔታ ተደስቶ የሚኖርና ለውጥን የሚሻ አይደለም ማለታቸው ነበር። በአንፃሩ በ19ኛው ክፍለ-ዘመን መጀመሪያ ላይ ፕረሽያን ይገዙ የነበሩት ታላቁ ፍሬድሪክ ሁለተኛው ለዚህ ታላቅ ህዝብ ምን ላድርግለት? እያሉ ነበር የሚጨነቁት። በሁለቱ ንጉሶች መሀከል ያለውን የአስተሳሰብ ልዩነት ተመልከቱት። በዚህ መልክ ነው አገራችን ጠንካራ አገር እንዳትሆን የተሸረበባት። የመጨረሻ መጨረሻ ምክርን የማይሰማ አገዛዝና መሪ አገርን አዳክሞና አውድሞ ነው የሚሄደው።

ከዚህም ባሻገር አፄ ኃይለሥላሴ የፀጥታውንና የወታደራዊውን ኃይል ለውጭ የስለላ ኃይሎች ክፍት አድርገው በመስጠታቸው ዛሬ እንደምናየው ለአገራችን መዳከምና መበታተን ሁኔታውን አመቻቹ። በተለይም ለአሜሪካን መንግስት የተሰጠው ሰፊ የኤምባሲ ግቢ መገንቢያና መኖሪያ ይህ ኃያል መንግስት የአገዛዙን የዋህነት በመገንዘብ ከውስጥ የአገራችንን ብሄራዊ ነፃነት ሊያዳክሙ የሚችሉ ኃይሎችን በመመልመልና የባህል ወረራ በማድረግ በሃምሳዎቹና በስድሳዎቹ ዘመን ብቅ ያለው ወጣት ትውልድ ዕውነተኛ የአገር ስሜት እንዳያድርበት ለማድረግ በቃ። ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ አሜሪካንን የሚናፍቅ ሆነ። በአገሩ እንዳይኮራና እየተሰደደ እንዲኖር መሰረት ተጣለለት። በመሰረቱ የአገራችን የውስጥ ለውስጥ መቦርቦርና መዳከም በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን የተዘጋጀና ከዚህም ሆነ ከዚያኛው ብሄረሰብ በተውጣጣ ቢሮክራሲያዊና ቴክኖክራሲያዊ ኃይል የተቀነባበረ ነው። በነፃነት ስም የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች በየቦታው እንደ አሸን መፍለቅ የስርዓቱ ነፀብራቆች እንጂ በመሰረቱ ለችግሩ ዋና ምክንያቶች አይደሉም። ሁኔታው ማጠፊያ እያጣ ሲሄድ ግን የነበራቸውን በጣም ዝቅተኛ የማሰብ ኃይል በመጠቀም የውድቀታችንን ሂደት ለማፋጠን ችለዋል። ራሳቸውም የህብረተሰባችን ውጤቶች በመሆናቸው ብሄራዊ ስሜትን አዳብረው ለአንድ አገርና ብሄራዊ ነፃነቱ ለተከበረ ህዝብ ከሌላው ጋር እጅ ለእጅ በመያያዝ ሊታገሉ የሚችሉ አልነበሩም። ስለዚህም የነሱ አካሄድ፣ የመገንጠልና አገርን የመበታተን ፍላጎት ከጭንቅላት አለመብሰል ጋር የተያያዘ ነው። ይህ ጉዳይ ደግሞ በጊዜው ከነበረው የማቴሪያል ሁኔታና ትምህርታዊ አሰጣጥ ጋር የተያያዘ ነው። ሪፑብሊካዊ አገዛዝ የሌለው አገርና፣ ነፃነቱን ተጠቅሞ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለመፍጠር የማይችል ህዝብ የግዴታ ጭንቅላቱ በመጥፎ አስተሳሰብ መጠመዱ የማይቀር ጉዳይ ነው። ስለዚህም በአንድ አገር ውስጥ በዕውነተኛ ሪፑብሊካዊ መንፈስ ላይ የተመረኮዘ አስተዳደር ከሰፈነና ተመጣጣኝ እኩልነትም ካለና ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል የማደግ ዕድል ለማግኘት የሚችል ከሆነ ልገንጠል የሚልበት ምክንያት በፍጹም አይኖርም። ስለሆነም በጊዜው የነበረው የተበላሸ ኢኮኖሚያዊ አገነባብ መንፈሳዊ አስተሳሰብ እንዲዳብርና ብሄራዊ ስሜት ጎልቶ እንዲወጣ የማድረግ ኃይል አልነበረውም። በመሆኑም ጠቅላላው ስርዓት ለዲሲፕሊን መጉደል፣ ለሽወዳ፣ ለአድርባይነት፣ ለህሊና መገዛት አለመቻል፣ ለታታሪነት ዕጦትና ኃላፊነትን አለመሰማት የሚያመች ነበር። የጭንቅላትን በተወሳሰበ መልክ ማደግና ሞራላዊና ስነምግባራዊ፣ እንዲሁም ህብረተሰብአዊ ባህርይ መያዝ በጀርመን ፈላስፋዎችና ሳይንቲስቶች በደንብ የተጠናና እነሱም ለአገር ግንባታ የተጠቀሙበት ስለሆነ የአገራችንን ምሁራን ድክመት ለመረዳት የእነዚህን ፈላስፋዎች ምርምር ማጥናቱ በጣም ጠቃሚ ነው። አንድን አገር በተራ የአካዴሚክስ ዕውቀት ለመገንባትና እንደ አገር ለማቆየት አለመቻል ከአገራችን ብቻ ሳይሆን ከተለያዩ የአፍሪቃና የተቀሩት የሶስተኛው ዓለም ተብለው ከሚጠሩት አገሮችም ማረጋገጥ እንችላለን። ስለዚህም ማርክስ የሚለው አጠቃላይ ምሁራዊነት (General Intellect) ሊያድግና ሊዳብር፣ እንዱሁም መስረት ሊይዝ የሚችለው ከውስጥ በማኑፋክቱር ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ግንባታ ሲካሄድ ብቻ ነው። በዚህ አማካይነት ብቻ ነው አንድ አገር አስፈላጊውን በልዩ ልዩ መልኮች ሊገለጹ የሚችሉ፣ ለረጅምና ለአጭር ጊዜ የፍጆታ ጠቀሜታዎች ሊያገለግሉ የሚችሉ ምርቶችን ለማምረት የምትችለው። የማሽንን ኃያልነት ለመረዳት የማይችል አገዛዝና ምሁር የመጨረሻ መጨረሻ በሁሉም መልክ የሚገለጽን ድህነት ነው አስፋፍቶ የሚያልፈው።

በአብዮቱ ጊዜ የተሰራው ከፈተኛ የታሪካዊ ወንጀል!!

በመጀመሪያ ደረጃ በአገራችን ውስጥ እንደዚያ ዐይነት መተላለቅ ሊፈጠር የቻለው ተራማጅ ነኝ የሚለው ኃይል የማርክሲዝምን ርዕዮተ-ዓለም በመከተሉ ሳይሆን በራሱ ጨቅላ አስተሳሰብ ነው። አንድም ቦታ ላይ ደም በመፋሰስ ብቻ ነው አብዮት መልክ ሊይዝና ህዝብም ነፃ ሊወጣ ይችላል ተብሎ የተፃፈበት ቦታ የለም። በሌላው ወገን ግን እያንዳንዱ አዲስ ትውልድ ልክ መጽሀፍ-ቅዱስንና ቁራንን ለስልጣን መወጣጫና ሀብት ለማካበቻ መጠቀሚያ አድርጎ እንደሚተረጉመው ሁሉ በኛ አገርም በጥቂት ግለሰቦች ማርክሲዝም በመጥፎ መንገድ በመተርጎሙ ወደ ደም መፋሰስ ሊያደርስ ችሏል። ለመሆኑ ስንቶቹ ታጋዮች ናቸው የማርክስን ዳስ ካፒታልና የስርፕለስ ቫልዩን መጽሀፎችንና እንዲሁም መስረታዊ ስራ (Ground work=Grundrisse) ያነበቡትና ያጠኑት? ይሁንና ግን አንዳንድ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን የተማሪው እንቅስቃሴ መሪዎች አልነበሩም ብሎ መናገር አይቻልም። እነዚህ በጊዜው ቀድመው የሄዱ ኃይሎች በየዋህነትና በአገር ወዳድነት ስሜት ብቻ በመነሳሳት የመጨረሻ መጨረሻ በወታደራዊው አገዛዝና በቢሮክራሲው እንዲመቱ ተደርገዋል። በውጭ የስለላ ኃይል በተቀነባበረ የከተማ ሸበርተኝነት አገራችን የደም አውድማ ለመሆን በቃች። ይህ ዐይነቱ አላስፈላጊ አካሄድና የወታደራዊው አገዛዝ የተከተለው የቀይ ሽብር የሚባለው ፋሺሽታዊ እርምጃ የህብረተሰብአችንን ገበና ከፈተው። አዳዲስ አሉታዊ ኃይል (Negative Energy) ያላቸው ኃይሎች በመፈጠርና ጓድ በመባባል አገሪቱን የወንድማማቾች መተላለቂያ መድረክ አደረጓት። በኃይማኖት ተሸፍኖ የነበረው ሞራል በመገርሰሱ በተለይም ንዑስ ከበርቴው አረመኒያዊ በመሆን በታዳጊው ወጣት ላይ በቀላል ቋንቋ ሊገለጽ የማይችል ፋሺሽታዊ እርምጃን ወሰደ።

ያም ሆነ ይህ በዚያን ጊዜ የተከሰተው አስቀያሚ ሁኔታ አብዮት ተካሂዶባቸዋል በተባሉ አገሮች ሁሉ የደረሰ አይደለም። በአንዳንድ አገሮች የተወሰነ መተላለቅ ቢኖርም የመጨረሻ መጨረሻ ራሳቸውን በራሳቸው በማግኘት ወደ ብሄራዊ ኢኮኖሚ ግንባታና ወደ መከበር ነው ያመሩት። በታሪክ ውስጥ እንደዚህ ዐይነቱ የዕልከኝነትና የርስ በርስ መጠላላት በሽታ የተናወጠው የአገራችንን ምሁር ብቻ ነው። ራሱን በራሱ ለማግኘት የማይችል ትውልድ በመፈጠሩ፣ የራሱን ዓለም በመመስረት ለአንድ ትውልድ ብቻ ሳይሆን ለሶስትና ለአራት ትውልድ የሚሆን ጠንቅ ጥሎ አልፏል።

ስለዚህም ያህ ሁሉ የጥገና ለውጥ ተካሂዶ እነሱን በጥሞናና በመማርና በማሰተማር ተግባራዊ ከማድረግ ይልቅ ሁሉም የየራሱን ቡድን በመፍጠርና በራሱ ዓለም ውስጥ በመሽከርከር አገርን ወደ ማጥፋት ነው ያመራው። የመሬት ላራሹ አዋጅ፣ የወዝ አደሩና የገበሬው መደራጀት፣ የሴቶች መደራጀትና ራስን ማግኘት፣ የብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ ፕሮግራም መዘጋጀትና መመሪያ እንዲሆን መቅረቡ፣ እነዚህ ሁሉ ቢታሰብባቸው ለአገር ግንባታ የሚጠቅሙ ነበሩ። ቀስ በቀስ በስህተትና በሙከራ ተግባራዊ ቢሆኑና፣ ሁሉም ቢተባበር ኖር ዛሬ የምናያትንና እንድናዝንና እንድናለቅስ የተገደድንበትን ሁኔታ ባላየን ነበር። የሚያሳዝነው ግን ሁሉም ከስህተቱ ለመማር አለመቻሉ ነው። ” ሰው ቀርቶ እንኳ ትንኝም ገድዬ አላውቅም“ የሚለው አነጋገር ጤናማ ጭንቅላት ካላቸው ሰዎች የሚወጣ ሳይሆን የናዚ አስተሳስብ ካላቸው ሰዎች ብቻ ነው። ጭንቅላት ያለውና ራሱን ጠይቆ ተሃድሶ ለማድረግ ከሚዘጋጅ ሰው የሚሰነዘር ነገር አይደለም። ራሱን ለመጠየቅ የሚችልና ወደ ውስጥ ራሱን የሚመለከት ሰው በፍጹም ወንድሙን ሊገድል አይችልም። እንደዚህ ዐይነቱ ድርጊት ሊፈጠር የሚችለው ራሳቸው ሰው መሆናቸውን በማያውቁና የኑሮን ትርጉም በማይረዱ ብቻ ነው። ስለሆነም በጥቂት ኃይሎች አማካይነት በወጣቱና በምሁሩ ላይ የተፈጸመው ወንጀል ይቅርታ የማይደረግለት ነው። የመጨረሻ መጨረሻ የአገርን አንድነት ያናጋ ነው። ብዙ ኃይልን የጨረሰ ነው። ታሪክን ያወደመ፣ ቤተሰብን ያፈራረሰና ወንድምን ከወንድም የነጠለና ያጋጨ በታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ትርጉም የሌለው ተግባር ነው። በአጭሩ በምንም ዐይነት ሎጂክ ሊደገፍና ሊገለጽ የማይችል ነው። የህብረተሰብንና የተፈጥሮን ህግ የሚጻረር እጅግ አደገኛ አካሄድ ነው። ጠቅላላው በአብዮት ስም የተካሄደው ፖለቲካ የሚባለው ፈሊጥ የአድዋን መልዕክት የሚጻረር ነው። ከአንድነት ይልቅ እንድንበታተንና እንዳንተማመን ያደረገ ነው። ለሁለ-ገብ ዕድገት እንቅፋት የሆነ እጅግ አደገኛ አካሄድ ነው።

የኢህአዴግ ስርአተ መንግስት ችግር

የወያኔ አገዛዝ ስልጣን ላይ ሲመጣ ዋና ዓላማው ደርግ ይከተላል የሚባለውን ”የናሺናሊስት ፕሮግራም“ ሙሉ በሙሉ ደምስሶ በገበያ ኢኮኖሚ ስም የአገራችንን አካሄድ ማሳሳትና ሀብትን የሚያወድም ፖሊሲ መከተል ነው። ስለሆነም የተወሰነውን የህብረተሰብ ኃይል አደልቦና በዓለም አቀፍ ሂራርኪ የስልጣን አወራረድ ውስጥ በማካተት ሙሉ በሙሉ አገራችንን መቆጣጠርና የህዝባችንንም ጭንቅላት መበረዝና መንፈሱን ማዳከም ነው። የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመባል የሚታወቀው ኢ-ሳይንሳዊ ፖሊሲ ዋናው ዓላማው የአገራችንን ዕውነተኛ ዕድገት ማጨናገፍና ህዝባችንን አሽመድምዶ ማስቀረት ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ አገዛዙን በስለላ ስልትና በአነጣጥሮ ተኳሽነት በማሰልጠን ፋሺሽታዊ ይዘት እንዲኖረው በማድረግ፣ ህዝባችንና ለዲሞክራሲና ለነፃነት የሚታገለው ጥቂቱ ምሁር ዘለዓለሙን እየፈራ እንዲኖር ማድረግ ነው። በዚህ ረገድና፣ አገራችንን በክልልና በቋንቋ በመከፋፈል ኢምፔሪያሊስት ኃይሎች በቀጥታ ወረራ ያላገኙትን ድል የኛን ምሁራዊ ድክመት ተመልክተውና የተወሰነውን ጉያቸው ውስጥ በመክተት ዛሬ እንደዚህ ዐይነቱ የሚያሳፍር ደረጃ ላይ ለመድረስ በቅተናል። በታሪካችን ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ ተዋርደናል። ህዝባችን በሁሉም ረገድ እንዲዳከምና አቅመ-ቢስ እንዲሆን ተደርጓል። ባጭሩ የውስጥና የውጭ ኃይሎች አንድ ላይ እጅና ጓንቲ በመሆን የአድዋን ድል ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዳናደርግና የሰለጠነች ኢትዮጵያን እንዳንገነባ ተደርገናል። ይህ ጉዳይ የወያኔን አገዛዝና ፖሊሲውን ለምንቃወመውና ለምንታገለው ኃይሎች የቱን ያህል ግልጽ ይሁን አይሁን በደንብ የሚታወቅ ጉዳይ አይደለም። ማለት የሚቻለው ግን በተለይም ግንባር ቀደምትነትን ይዣለሁ፣ ስለሆነም ስልጣን ለእኔ ነው የሚገባኝ ብሎ እዚህና እዚያ በሚሯሯጠው ኢትዮጵያዊ ዘንድ ይህ የውጭ ኃይሎች መተሳሰብና መረዳዳት፣ እንዲሁም ደግሞ የወያኔን አገዛዝ ማሽትና አገራችንን ማወደም ግልጽ የሆነ ጉዳይ ነበር።

ከዚህ ስንነሳ የአገራችን የወደፊቱ የነፃነት ጉዳይ እጅግ የሚያሳስብ ነው። የዛሬው አገዛዝ ራሱ በሚፈጥራቸው እጅግ የተምታቱ የሽወዳ ፖለቲካዎችና የህዝባችንን ፍላጎቶች ማሟላት አለመቻል ራሳችው አሽቀንጥረው እንደሚጥሉት የታወቀ ጉዳይ። በታሪክ ውስጥ አንድ አገዛዝ ህዝብን እያፈነ፣ እያሰቃየና እየገደለ፣ እንዲሁም ደግሞ ስትራቴጂ የሚባሉ የኢኮኖሚ መስኮችን በመቆጣጠር ህዝቡን መውጫ መግቢያ በማሳጣት ስልጣን ላይ የቆየበት ዘመን የለም። ስለሆነም የወያኔ አገዛዝ ትንሽ ጊዜ ይቆይ ይሆናል እንጂ አንድ ቀን ድምጥማጡ እንደሚጠፋ የታወቀ ጉዳይ ነው። እስከዚያ ጊዜ ድረስ ግን ከአለቆቹ ጋር በመሆን አገራችንን የባሰውኑ ያዳክማታል። ህዝባችንን የባሰውኑ አቅመ-ቢስ ያደርገዋል። በዚህም ምክንያት ግራ የተጋባው ኃይል አሁንም ቢሆን ይህንን የወያኔ አገዛዝ አደራጅተውና አስታጠቀው፣ እንዲሁም እያማከሩት እዚህ ያደረሱትን የውጭ ኃይሎች እንደገና መማፀኑ የማይቀር ጉዳይ ነው። ልንወጣ የማንችለው የዙሪያ ጥምጥም ውስጥ ነው የገባነው ማለት ነው። ያም ሆነ ይህ፣ ይህ ጉዳይ እኛን የሚያስፈራን መሆን የለበትም። ምክንያቱም ማንኛውም ኃይል የሚፈተንበትና የሚረጋገጥበት ነገር አለና። አንድ አገዛዝ ወይንም ኃይል የህዝብን ፍላጎት ማሟላት የማይችልና አገርንም በጸና መሰረት ላይ ለመገንባት የማይችል ከሆነ ዛሬ ወያኔን የሚታገለው ኃይል ራሱ ስልጣን ሲይዝ የሚጠየቅበት ጉዳይ ይኖራል። ከዚህም በላይ የዓለም ሁኔታ ይቀየራል። ማንኛውም ነገር ቆሞ የሚቀር አይደለም። የራሳቸው የኢምፔሪያሊስት አገሮች ሁኔታና ኃያልነትም ይቀየራል። አንድ ኃያል መንግስት ዘለዓለሙን ኃያል ሆኖ በፍጹም ሊቀር አይችልም። በተለይም አገሮችን የሚወሩና የደካማ አገሮችን ተፈጥሮአዊ ፍላጎት በሆነው ባልሆነው የሚያሰናክሉ የውጭ ኃይሎች አንድ ቀን መከስከሳቸው የማይቀር የታሪክ ግዴታ ነው።፡ ከዚህም ባሻገር በማንኛውም አገር አዳዲስ የህብረተሰብ ኃይሎች ይፈጠራሉ። የህበረተሰባቸውን ሂደት ለመጠየቅ ይገደዳሉ። በሌላ ወገን ደግሞ አገዛዞች ወደ አምባገነንነት የሚለወጡበት ሁኔታ ይፈጠራል። በዲሞክራሲ ስም ከተመረጡ በኋላ ለራሳቸው በሚስማማ መልክ የፖለቲካ ማትሪክሱን በመለወጥ አዲስ ህብረተሰብአዊ ቅራኔ ይፈጥራሉ። ስለሆነም ከህዝብ ጋር ስለሚፋጠጡ ኃይላቸው ቀስ በቀስ እየተሟጠጠ ይመጣል። ዛሬ ይህንን ጉዳይ በአሜሪካን ምድር የምንመለከተው ሀቅ ነው።

ስለሆነም የኛ ዝግጅት መሆን ያለበት ተስፋ መቁረጥ ሳይሆን የነገሩን አሳሳቢነት በደንብ ተመልክቶ ሁለ-ገብ ዝግጅት ማድረግ ነው። ለዚህ ደግሞ ከአረጀ አስተሳሰብ መላቀቅ ያስፈልጋል። በተለይም ወጣቱ ትውልድ ራሱን በራሱ ማግኘት አለበት። ዕውነተኛውን የዕድገት ቁልፍ ለማግኘት ሌት ተቀን መሰራት አለበት። ተጎታች ሳይሆን በራሱ ህሊና የሚገዛ መሆን አለበት። ጥያቄዎችን መላልሶ በመጠየቅ መልስ ለማግኘት የሚሻ ኃይል መሆን አለበት። በዚህ መልክ ብቻ ነው ታሪካዊ ተልዕኮውን ሊወጣ የሚችለው።

ከአድዋ ምን ተረፈን? የዛሬው የአገራችን ሁኔታ ምን ይመስላል?

የአድዋ ድል ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ያልሆነበትንና ብሄራዊ ነፃነታችንን ለማስከበር ያልቻልንበትን ምክንያቶች ከሞላ ጎደል ላይ ለማስቀመጥ ተሞክሯል። እንደሚታወቀው ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ደካማ አገሮችን የሚወሩትና የተለሙትን የዕድገት ፈለግ ለማጨናገፍ የሚጠቀሙበት ስትራቴጂ አገሮችን በቀጥታ በመውረር አይደለም። የሚሰጡት ምክንያት እንደሁኔታው የሚለያይ ነው። በተለይም አንዳንድ ደካማ አገሮች የናሺናሊስት አጀንዳ ይዘው የሚጓዙ ከሆነ አይ በውስጥ ኃይሎች የመንግስት ግልበጣ ሙከራ ይደረግባቸዋል። ወይም ደግሞ በተዘዋዋሪ እነዚህ አገሮች አካባቢ ካለ አገር ጋር ወደ ጦርነት ውስጥ የሚገቡበትን ዘዴ በመፍጠር አስተሳሰባቸው በጦርነት ላይ እንዲሆን በማድረግ ኃይላቸውን እንዲጨርሱ ይደርጋሉ። ስለሆነም አንዳንድ አገሮች አገራቸውን ለማሳደግ የናሺናሊስት አጀንዳ ከነደፉ በኋላ በውጭ ኃይሎች በተቀነባበረ ሴራ ይከሽፋል። ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ እየተስፋፋ የመጣው በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች በግልጽም የማይታወቀው ሴራ ምሁሮችን ማኮላሸትና በዚያ አማካይነት አገሮችን ከውስጥ መቦርቦርና ማዳከም ዋናው የኢምፔሪያሊስቶች አንደኛው ስትራቴጂ ነው። በተለይም በትምህርት ዘርፍና በርዕዮተ-ዓለም፣ በተጨማሪም በባህል ወረራ የተነሳ አገሮች በስንትና ስንት ትግልና ደም መፋሰስ የተቀዳጁት የፖለቲካ ነፃነት እንዳለ ይኮላሻል። ደካማ አገሮች ራሳቸውን እንዳይችሉ የተለያዩ መሰናከሎች ከውጭ ኃይሎች ብቻ ሳይሆን ተኮላሽቶ ስልጣን ላይ ከወጣው ምሁርና በተበላሸ ካሪኩለም አዳዲስ ተማሪዎችን በሚያስተምረው ምሁር አማካይነት እንደ ኢትዮጵያ የመሳሰሉት አገሮች በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ማህበረስብ እንዳይገነቡ ይደረጋል። ለዝንተ-ዓለማቸው በድህነት እንዲሰቃዩ በመደረግ ታሪክን እንዳይሰሩ ይደረጋሉ። ደሃ ህዝቦች የማሰብ ኃይላቸው በመዳከሙ የተነሳ የኑሮን ትርጉም እንዳይረዱት ይደረጋሉ። ለድህነትና በድህነት የተፈጠሩ ይመስል በስማቸው ይለመንባቸዋል። በዚህም ምክንያት እግዚአብሄር የለገሳቸው ተፈጥሮአዊ ነፃነታቸው በመገፈፉ የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው እንዳይወስኑና ቤተሰብና ማህበረሰብ እንዳይመሰርቱ መንገዱ ሁሉ ይዘጋባቸዋል። በተለይም ባለፉት 26 ዓመታት በአገራችን ጎልቶ የሚታየው ሀቅ ይህ ጉዳይ ነው። የውስጥና የውጭ ኃይሎች በማበርና ህዝባችንን በጦርነት እንዲጠመድ በማድረግ ተሽመድምዶ እንዲቀር ለማድረግ በቅተዋል። በተለያየ ሙያ የሰለጠኑ ኢትዮጵያውያን በፖለቲካውም ሆነ ከዚያ ውጭ ባሉ መስኮች በመሰማራት የአገራችንን ዕድገት በከፍተኛ ደረጃ አዛብተዋል። ለድህነትና ለውድቀት ዳርገውናል። ቡናና አበባ፣ እንዲሁም የሸንኮራ አደጋ ተካይ አድርገውናል። ከቴክኖሎጂ ይልቅ ወደ ውጭ በሚላክ የእርሻ ምርት ላይ በመሰማራት አገራችን ዘለዓለማዊ ጥገኛና ደሀ እንድትሆን ሁሉን ነገር አዘጋጅተዋል። የእዚህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አርቃቂዎች የፕሪንስተንና የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ምርቆች ናቸው። ብልጽግናን ከማምጣት ይልቅ ድህነትን የሚፈለፍሉ በመሰማራት በአገራችን ምድር የተዛባና ግራ የገባው ማህበረሰብ እንዲፈጠር አድርገዋል። ስለሆነም እነሱ በቪላ ቤትና በልዩ መዝናኛ ቦታዎች ሲንደላቀቁ ህዝባችን ሜዳ ላይ እንዲወድቅ ተደርጓል። ከቆሻሻ ቦታ እየለቀመ እንዲበላ ተገዷል። በዛሬው ዕለት ከቆሻሻ ቦታ ምግብና ሌሎች ነገሮችን ፈልገው ለመውሰድ በተሰበሱ ምስኪን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ላይ ክምሩ በመናዱ ቢያንስ ሃምሳ ስዎች ለሞት ተዳርገዋል። ይህ ነው እንግዲህ ከዚህ ሁሉ መዋደቅ የተረፈን። ይህ ነው ብዙ የተነገረለትና ተከታታይነት ያሳየው የኢኮኖሚ ዕድገት ትርጉም!!

ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት አፄውና ቢሮክራሲዎቻቸው የአንድን አገር ዕድገት መሰረተ-ሃሳብ ባለመረዳታቸው በጊዜው ሰፊ ውይይትና ክርክር ሳይደረግበት ለዕድገት የማያመች የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ ውስጣዊ ኃይላችን እንዲዳከም አድርገዋል። በአብዮቱ ዘመን በግርግርና በመበጣበጥ ምክንያት የተነሳ ምሁሩ ለአገራችን በሚበጀው የዕድገት ፖሊሲ ላይ ክርክር እንዳያደርግ ታገደ። በደፈናው በጊዜው በደርግ የተወሰዱት የኢኮኖሚ ፖሊስዎች እንዳሉ የዕዝ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ናቸው በሚልና አገሪቱ የሶሻሊስቱን መንገድ ነው እየተከተለች በማለት የኢምፔሪያሊስት ኃይሎች የውስጡን ኃይል በማስታጠቅና ከውጭ ደግሞ ወረራ እንዲደረግብን በማድረግ አገራችንን ትልቅ ውጥረት ውስጥ ከተቷት።

ከዚህ ሁሉ ሁኔታ ምን እንማራለን? የአድዋ አባቶቻችንና እናቶቻችስ አደራ ምንድነው?

በእኛ ኢትዮጵያውያን ምሁሮች ዘንድ ከፍተኛ ስህተት ይታያል።፡የታሪክን ሂደትና የአንድን ህብረተሰብ ግንባታና እንዲሁም ለሚቀጥለው ተከታታይ ትውልድ ማስተላለፍ ከፍተኛ የጭንቅላት ስራ እንደሚጠይቅ ግንዛቤ የተገባበት አይመስልም። የሁላችንም ግንዛቤ አንድን አገር በተራ አካዴሜክስ ዕውቀትና የህግ የበላይነት መርሆች ላይ ብቻ የሚገነባ ይመስለናል። ሁላችንም ወደ ኋላ ተመልሰን፣ ስዊዘርላንድ፣ አውስትሪያ፣ ስዊድንና ጀርመን፣ እንዲሁም ደቡብ ኮርያና ጃፓን እንዴት እንደዚህ ዐይነቱ የተወሳሰበ የህብረተሰብ ግንባታ ደረጃ ላይ ለመድረስ ቻሉ? ብለን ለመጠየቅ በፍጹም አንቃጣም። ስለሆነም የንቃተ-ህሊና መዳበርና ሞራላዊ ጥንካሬ ለአዲስ ህብረተሰብ ግንባታ ያላቸውን አስተዋፅዖ በፍጹም ለመመርመርና ለማጥናት አንቃጣም። እንዲያው ብቻ ተራ የዲሞክራሲያዊ መርሆች በመወርወርና አንዳንድ ንግግሮችን በማድረግና የምዕራቡን ዓለም በመለማመጥ ኢትዮጵያን እንደ አገር ለመገንባት የምንችል ይመስለናል። ዛሬ መቶ በመቶ ለማረጋገጥ እንደሚቻለው እስከዛሬ ድረስ የተከተልነው መንገድና የምንመራበት መርህ በሙሉ አንድም እርምጃ ወደፊት እንደማያራምደን ነው። አካሄዳችን በሙሉ ወደ ስልጣን እንድናመራ የሚረዳን እንጂ የጠነከረችና በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተገነባች ኢትዮጵያን ማየትና ለሚቀጥለው ትውልድ ማስተላለፍ አይደለም ዋናው ህልማችን። ዋናው ህልማችን በዚህም በዚያም ብሎ ስልጣን ላይ ቁጥጥ ለማለትና የድህነቱን ዘመን ለማራዘም ነው። ይህ ፍላጎታችን ባይሆንም፣ ከምንጽፈው፣ ከምንናገረውና ከምናደርጋቸው ድርጊቶች ማየት ይቻላል።

በመሰረቱ የኛ ችግር የተቆለፈበት ዐይነት ቁልፍ ነው። በቀላሉ መፍቻ የማይገኝለት ነው። ወደፊት የማያራምደን ነው። በተወሰነ ዓለም ውስጥ ብቻ የሚያሽከረክረን ነው። ሰፋ ላለና ለተወሳሰበና እንዲሁም እየበለጸገ ለሚሄድ ነገር የሚያመች አይደለም። እንደሚታወቀው አንድ አትክልት ጥሩ ፍሬ ሊሰጥና በተከታታይ ወራት ሊያብብና ሊያፈራ የሚችለው እንክብካቤ ሲያገኝ ብቻ ነው። የሰው ሰውነትና ጭንቅላትም እንደዚሁ ነው። ማንኛውም መጥፎም ሆነ ጥሩ ነገር ሊሰራ ወይም ሊፈጠር የሚችለው ባለን የጭንቅላት አወቃቀርና በየጊዜው ማደግ ነው። ማንኛውም ነገር ከጭንቅላትና ከአስተሳሰባችን ውጭ ሊሄድና ሊፈጠር አይችልም። ጭንቅላትና ከዚያ የሚፈልቀው አሰተሳሰብ ደግሞ የባህል ዕድገት ውጤቶች ናቸው። በተዘዋዋሪ ደግሞ ባህል የሚባለው በተለያየ መልክ የሚገለጸው ነገር ራሱ የራሳችን የማሰብና ያለማሰብ ኃይል ውጤት ነው። በሌላ አነጋገር፣ ብዙ ነገሮችን ማቃለል የምንችለውናው ስላምም ማስፈን የምንችለው በከፍተኛ ደረጃ የማሰብ ኃይላችንን ካንቀሳቀስን ብቻ ነው። ይህም ማለት ተንኮልን በመስራት ሳይሆን የሰውን ልጅ ኑሮ ለማቃለል ከሳይንሱና ከፍልስፍናው ዓለም ጋር የታረቅን እንደሆን ብቻ ነው።

እንደምናየው ዘመኑ የዞረብት ብቻ ሳይሆን የተወሳሰበ የቴክኖሎጂ ዘመን ነው። በዚህች ዓለም ላይ አገሮች እንደ አገር ሊቆዩ የሚችሉት ”ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ኑሪ“ በማለትና ባንዲራ በማውለብለብ ሳይሆን በሳይንስ በመመራትና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመፍጠር ሰፋ ያለ ኢኮኖሚ ስንገነባ ብቻ ነው። በመሰረቱ ቴክኖሎጂን እንደገና ልንፈጥረው አንችልም። የተዘጋጀና ያለቀለት ነው። ሁሉም ነገር መጽሀፍ ውስጥ አለ። ከኢንተርኔት ሁሉ መመሪያዎችን መኮረጅ ወይንም ማውረድ እንችላለን። በአካል ያለውንም መኮረጅና ከራስ ሁኔታ ጋር ማዋሃድና ማዳበር ይቻላል። ቁም ነገሩ ግን ለዚህ የተዘጋጀ ቆራጥና ተጋግዞ ሊሰራ የሚችል ኃይል መኖር አለበት። ይህ ብቻ ሲሆን ነው የታሪክን ግዴታ መወጣት የሚቻለው።

ስለሆነም አባቶቻችንና የዛሬው ህዝባችን ከኛ የሚጠብቁት የኛን መናቆርና መጠላለፍ ሳይሆን በአዲስ ሃሳብ ዙሪያ በመሰባሰብ ታሪክ መስራትን ብቻ ነው። እያንዳንዳችን አጭር ዕድሜ ነው ያለን። በዚህች አጭር ዕድሜያችን ግን አንዳንድ አገርን የሚጠቅም ስራ ሰርተን ማለፍ አለብን። ለዚህ ደግሞ ራሳችንን ቆም ብለን መጠየቅ አለብን። በመጠየቅና መልስ ለማግኘት በመጣጣር ብቻ ነው ለሁሉም ዜጋ የሚያመች አንድን ታላቅ አገር መገንባት የሚቻለው። የአድዋ መልዕክት ሌላ ሳይሆን ዲሞክራሲያዊ፣ የበለጸገችና ያማረች፣ እንዲሁም እያንዳንዱ ዜጋ በነፃነት የሚኖርባትን አገር መፍጠር ነው። የአድዋ መልዕክት ህዝባዊ ፍቅር፣ በወንድማማችነትና በእህትማማችነት ላይ የተገነባ ህብረተሰብአዊ መተሳሰር ይፈጠር ነው የሚለው። የአድዋ መልዕክት በሳይንስና በቴክኖሎጂ እየተመሩ በጀመሪያ ደረጃ የሰፊውን ህዝብ ፍላጎት በማሟላት አንድ ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባትና ለሚቀጥለው ትውልድ ማስተላለፍ ነው። የአድዋ መልዕክት ጥበብ፣ ቆንጆ ከተማዎችና መንደሮችን በመገንባት ህዝባችን በደስታ የሚኖርበትን ዓለም መፍጠር ነው። የአድዋ መልዕክት በእኛና በአገራችን መሀከል ያለውን ተፈጥሮአዊ መገናኘት በማደስ አዲስ ኢትዮጵያን መመስረት ነው። በአጭሩ፣ የአድዋ መልዕክት ህዝቦቿ በነፃነትና በመከባበር የሚኖሩባትን አገር መፍጠር ነው። የአድዋ መልዕክት መንግስት የሚባለው ፍጡር በታንክና በአውሮፕላን በመታጀብ ህዝብን የሚያስፈራራበትን አገር ማየት ሳይሆን መንፈሱ የታደሰና በራሱ የሚተማመን ዜጋ መኮትኮት ነው። 

መልካም ግንዛቤ!!


No comments: