አምሓራ ሳይንት ለብዙ ዓመታት “ወንዝ የሚሻግራት” መሪ አጥታ ቆይታለች። የአመራር ድክመቶች ሁሉ ምንጭ የመሪ ጉድለቶች ብቻ የሆነ አድርገን መውሰድ ይቀለናል። እኛ ተከታዮች ወይም ተመሪዎች (followers) ከመሪ ያላነሰ ተጠያቂነት አለብን። መሪዎቻችን ለአመራር ስኬት ብቸኛ ተወዳሽ መሆን እንደሌለባቸው ሁሉ ለአመራር ጉድለት ብቸኛ ተጠያቂ መሆን የለባቸውም። የመሪው ጉድለት መኖሩ ብናረጋግጥ እንኳን መሪው ብቸኛ ተጠያቂ ላይሆን ይችላል። ለአምሓራ ሳይንት ኋላቀር እድገት መሪና ተመሪውም ናቸው።
“በበግ የሚመራ የአንበሶች ሠራዊትን አልፈራም፤ በአንበሳ የሚመራ የበጎች ሠራዊትን ግን እፈራለሁ” የሚለው ታላቁ አሌክሳንደር በዚህ ዘመን ላይ ትክክል ባይሆን ፤ መሪ የሚወጣው ከተከታዮች ነውና ከመጀመሪያውኑ አንበሶቹ፣ እውነተኛ አንበሶች ከሆኑ በበግ መመራት አይፈቅዱም። የታላቁ አሌክሳንደር ምሳሌያዊ አነጋገር የመሪን ሚና አጋኖ ከመግለጽ ያለፈ ተግባራዊ ፋይዳ ያለው አይደለም። በተግባር እንደሚታየው በጠንካራ ተከታዮችን ያልተደገፈ መሪ (በግሉ የቱን ያህል ጠንካራ ቢሆንም እንኳን) ውጤታማ መሆን አይችልም። የደካማ ተከታዮች መሪ ውሎ አድሮ ራሱ ደካማ መሆኑ አይቀርም። ንቁ ተከታዮች መሪያቸውን ያነቃሉ፤ ትጉህ ተከታዮች መሪያቸውን ያተጋሉ። ጠንካራ ተከታዮች የአመራሩ ምሰሶ ናቸው። መሪያቸው ጠንካራ ጎኖቹን ይበልጥ እንዲያጎለብት፤ ደካማ ጎኖቹን እንዲያሻሽል ማድረግ ይችላሉ። ጠንካራ ተከታዮች መሪያቸው ብቃት ከጎደለው በጊዜ በሌላ የተሻለ ሰው እንዲተካ ማድርግ ይችላሉ። ደካማ ተከታዮች ግን ጠንካራውን መሪ ያደክማሉ። በአንፃሩ ደግሞ ትጉሁን መሪ የሚያሰናክሉ፤ ጠንካራውን መሪ የሚያዳክሙ ተከታዮች አሉ።
ተስማምቶ አዳሪ ተከታዮች “እሺ ሰዎች” (the yes-people) ናቸው፤ ሁሌ ከመሪያቸው ጎን ይቆማሉ፤ የታዘዙትን ይፈጽማሉ፤ ሆኖም ግን ለትንሹም ለትልቁም ”መመሪያ“ እንዲሰጣቸው ይፈልጋሉ፤ በራሳቸው አቅደው የሚሠሩት የለም።ጠንክረው አይጠይቁም።
“ተስማምቶ አዳሪዎች” ራሳቸውን የሥራ ሰው አድርገው ሲገልጹ ይሰማሉ። “የኔ ኃላፊነት የታዘዝኩትን መፈፀም ነው፤ ማቀድ፣ ማሰብ፣ ማለም የመሪዬ ተግባር ነው” ይላሉ። የአመራር ድክመት ቢኖር እነሱ የሚጠየቁበት አንዳችም ጉዳይ ያለ አይመስላቸውም፤ እንዲታሰብላቸው እንጂ እንዲያስቡ፤ እንዲታቀድላቸው እንጂ እንዲያቅዱ የተፈጠሩ አይመስላቸውም።
“ተነጂ ተከታዮች” መሪያቸውን ከመውደድና ከመከተል በስተቀር ስለሚሠሩት ነበር አይጨንቃቸውም፤ የመሪዓቸውን ድምጽ መስማት፤ እዋለበት መዋል፤ አደረበት ማደር ያነቃቃቸዋል። በዚህ ባህሪያቸው ምክንያት ተነጂ ተከታዮች “በጎች” (sheep) በሚል መጠሪያ ይታወቃሉ። “በጎች” ተከታዮችን ወደ ሥራ ማሠማራት፤ ጭንቀት ውስጥ በገቡት ጊዜ ሁሉ “አይዞዓችሁ” “ይሰራል” ወዘተ እያሉ ማባበል ለመሪው ራሱን የቻለ ትልቅ ሥራ ነው።
የዚህ አጭር እይታ ለአምሃራ ሳይንት ኋላ ቀር እድገት ዋናው ችግራችን "የመሪ እጦት ነው" የሚል ዓይነት ድምዳሜ መስማት የተለመደ ነው። ብዙ ሰዎች ምንም እንኳን ትክክል ቢሆኑ ወረዳዋን ከችግሮችዋ ማውጣት ያልቻልነው በመሪና በመልካም አስተዳደር እጦት እንደሆነ በእርግጠኝነት ይናገራሉ። እኛ ተከታዮች ህዝቦች ለወረዳዋ እድገት ደጋግመን እንጠይቅ እንኳኳ ። ለወረዋ ለውጥ አመራር መሪ ብቻውን የሚፈጥረው ነገር አይደለም። አመራር መሪ እና ተመሪ ተባብረው የሚፈጥሩት ነገር ነው። ስኬታማ አመራር በመሪ ብቃት ብቻ አይገኝም። በሀገራችን ስኬታማ አመራር እንዲኖር እኛም – ማለትም ተከታዮች (ተመሪዎች) – ኃላፊነት አለብን።
No comments:
Post a Comment