👉Neway Kassahu's View (መ/ር ንዋይ ካሳሁን)
ነነዌ
ወቅቱ በቤተክርስቲያናችንን አስተምህሮ በቀናት አነስተኛ የሆነችው ጾም፤ ጾመ ነነዌን የምንጾምበት ወቅት ነው፡፡ ቀኑ እንጂ ተግባሩና ትምህርቱ ግን ሰፊ ነው። ነነዌን ብዙ ጊዜ ከምንሰማውና ካስተማርነው በላይ ትልቅ ምስጢራዊና ታሪካዊ ከተማ ናት፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያና ነነዌን የምናነጻጽርበት ብዙ ገጽታ አለን፡፡
ነነዌ የአሦራውን ጥንታዊ ከተማ ስትሆን በላዕላይ መስጴጦምያ በአሁኑ አጠራር በሰሜናዊ ኢራቅ የምትገኝ ከተማ ናት፡፡ ከተማዋን ሶርያ ቱርክ ኢራን ያዋስኗታል፡፡
ከክርስቶስ ልደት በፊት በ 1800 ዓ.ዓ በኩሽ ልጅ ናምሩድ የተቆረቆረች ከተማ እንደሆነች መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ ዘፍ. 10፣ 11
በወቅቱ በአሦራውያን ግዛት ትልቋ የዓለም ከተማ ስትሆን በወቅቱ ታላቅ የሃይማኖት መዲና እንዲሁም የአሶራውያን አማልክት (ኬሽታር) ማማለኪ ስፍራ ተገንብቶባትም ነበር፡፡ ከተማዋ በተደጋጋሚ መሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ሲገጥማት የማምለኪያ ስፍራው ቢወድምም ከተማዋ እንደገና በ2260 ዓ.ዓ አካዲን በተባለው ንጉስ በድጋሚ ታንጻለች፡፡
ነነዌ በመጀመሪያ ስሟ የተጠቀሰው በዘፍጥረት 10፡11 ላይ ሲሆን የአሦር ግዛት ዋና ከተማ ነበረች፡፡ በንጉሡ ሕዝቅያስ ዘመን የይሁዳ ነቢይ የነበረው ኢሳይያስ የኖረባት፤ ሰናክሬም በ705 - 681 ዓዓ የገዛት፤ በኋላም በሁለት ልጆቹ አድራማሌቅና ሶርሶር በተባሉ ልጆቹ የተገደለባት ከተማ ናት፡፡ ኢሳ 37፡37-38
ነነዌ በአሁኑ አጠራር በሰሜናዊ ኢራቅ ከተማ ሞሱል (Mosul) በሚባል ስም ትጠራለች፡፡ በወቅቱ መቶ ሃያ ሺኽ ሰው ያኽል ይኖርባት የነበረ ሲሆን ከተማዋን ትንንሾቹን መንደሮች ጨምሮ ዞሮ ለመጨረስ ሶስት ቀን ይፈጃል።
ነነዌ በበደል ምክንያት እግዚብሔር ተቆጥቶ ሊያጠፋት ይኽንንም እንዲውቁ ዮናስን እንዲያስተምር አዘዘው፡፡ ሕዝቧ ሩህሩህ ስለነበር ከንጉሡ እስከ ሕዝቡ ሕጻናት እንስሳት ሳይቀሩ የእግዚአብሔርን ፊት ፈለጉ፣ ንሰሐ ገቡ እግዚአብሔርም ራራላቸው ይቅርም አላቸው፡፡ ነቢዩ ዮናስና ናሆም የነበረውን ታሪክ ጽፈው አቆዩልን፡፡ ነቢዩ ዮናስና ነቢዩ ዳንኤል መቃብር በዚያ የነበረ ሲሆን በአክራሪው እስልምና ISIS ሰራዊት ፈራርሷል፡፡
ምዕራፍ አንድ
ትንቢተ ዮናስ በነገረ መለኮታዊ ትንታኔ
ቅዱስ ዮናስ የብሉይ ኪዳን ነቢይ ሲሆን ቁጥሩ ከደቂቀ ነቢያት መካከል ነው። የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን ማወቅ ሐዲስ ኪዳንን ለመረዳት መሠረት ነው። በብሉይ ነቢያቱን የላከ በሐዲስ ኪዳን ሐዋርያቱን የላከ እግዚአብሔር አንድ ነው። ነቢያትን ትንቢት ለመጻፍ ያንሳሳ መንፈስ ቅዱስ ነው ሐዋርያቱንም ወንጌልን መልእክታትን እንዲጽፉ ያነሳው ያው መንፈስ ቅዱስ ነው “በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል” ኤፌ.2:20
ዮናስ ማለት በእብራይስ ቋንቋን ርግብ ማለት ሲሆን የኖረው ከ786 – 746 ዓመተ ዓለም አካባቢ እንደሆነ የመጽሐፉ ይዘት ያስረዳል። ዮናስ በንጉሡ በዳግማዊ ኢዮርብአም ዘመን የነበረ ነቢይ ሲሆን በገሊላ ከምትገኘው ጋትሔፌር የሆነውው የአማቴ ልጅ መሆኑን መጽሐፉ በመግቢያው ነግሮናል።
ዮናስ ትንቢት የተናገረው ከጌታ መወለድ በፊት በ8ኛው ምእተ ዓለም በፊት ሲሆን የነቢያት ዋና ተግባር ሕዝቡ በአንድ አምላክ እንዲያምኑ፣ ንሰሐ እንዲገቡ፣ ስለሚመጣው መሲህ እንዲረዱ መናገር ነው። ሰው እንዴት ንሰሐ እንደሚገባ መሲህ እንዴት ይመጣል የሚል ትምህርት ነው። የዮናስ ትንቢት ዓላማ ነነዌን ወደ ንሰሐ መመልስ ነው። የእግዚአብሔር ርኅራኄና ፍቅር እንክብካቤ ግልጽ ሆኗል።
ዮናስ በብዙ መልኩ የተለየ ነቢይ ነው። አይሁዳዊ ነው። የተላከው ግን ወደ አሕዛብ አሦራውያን ሲሆን በጣም በጠላትንነት የሚተያዩ ሕዝቦች ነበሩ። አሦራውያን እስራኤላውያንን ገዝተዋቸው ነበር። ነነዌ የታላቋ የአሦራውያን ዋና ከተማ ነበረች። በወቅቱ በጣም ጠንካራ ሕዝቦች ነበሩ። እግዚአብሔር ሕዝቡ ንሰሐ የሚገባ ልብ እንዳላቸው ስለሚያውቅ ስለሆነም የራሱን ሰው ነቢዩ ዮናስን ላከው። ዮናስ ግን አሦራውያንን ስለሚጠላቸው አይሁድ ወዳልሆኑት መሄድ እንቢ አለ። “የእግዚአብሔርም ቃል ወደ አማቴ ልጅ ወደ ዮናስ እንዲህ ሲል መጣ፦ተነሥተህ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፥ ክፉታቸውም ወደ ፊቴ ወጥቶአልና በእርስዋ ላይ ስበክ “ አለው።
ዮናስ ተልእኮውን ሲሰማ ግራ ተጋባ ተበሳጨ።
እግዚአብሔር የሚፈልገውን ተልእኮ ነው የሚሰጠን እንጂ እኛ በፈለግነው አገልግሎት ብቻ እንዳንሰማራ ትምህርት ነው። በደመቀበት ጭብጨባ ባለበት ብቻ ሳይሆን እርሱ ባሰማራንም መሄድን ያስረዳናል። እግዚአብሔር ከለመድነው ከምንፈልገው ውጪም ተልእኮ አለው። እግዚአብሔር ወደራሱ ሊመልሳቸው ፈለገ። ጳውሎስ አይሁድን ብቻ ሊያስተምር ነበር ይደክም የነበረው እግዚአብሔር ግን ወደ አሕዛብ እንዲሔድ ነገረው። ጳውሎስ በመጀመሪያ ብዙም ባይደሰትም በኋላ ግን ወደ አሕዛብ በመሄድ መክሊቱን መቶ እጥፍ አድርጎ በአገልግሎቱ የተሳካለት የአሕዛብ ሐዋርያ ሆኗል።
ዮናስ ለነነዌ ስበክ ተባለ። የሰዶም ገሞራ ሰዎች እንደ ነነዌ ሰዎች እድል ተሰጥቷቸው ነበር። ነገር ግን አልጠቀሙበትም ነነዌ ሰዎች ግን የንሰሐ ብርሃን እንደመጣላቸው ያወቁ ሰዎች ናቸው። አገልግሎት ማለት በራሳችን ሃይማኖት ውስጥ ብቻ ላሉት አይደለም። አይመስሉንም ይጠሉናል ለምንላቸው ሁሉ መሆን አለበት። የኔን ስላልተከተልክ ብሎ ጥላቻ፣ ንቀት፣ ስድብ ይኽ የእግዚአብሔር ሰው መሆን መለኪያ አይደለም። ለነሱ የእግዚአብሔር ፍቅር ማሳየት ተገቢ ነው። እግዚአብሔር በማያምኑትም ዘንድ ይድኑ አላማ አለው።
ዮናስ አሦራውያን ሕዝቦችን አይወዳቸውም ነበር። በመሆኑም አገልግሎቱን እንቢ አለ። የሕዝቡን መዳን እንቢ አለ። ተልእኮውን መቀበል አልፈለገም። ይልቁንም ከአገልግሎቱ መሸሽን መረጠ። ሰውን የምትጠላ ከሆነ ክርስቲያን መሆን አልጀመርክም። የእግዚአብሔርንም ሐሳብ አትከተልም ማለት ነው። ፍቅር የእግዚአብሔር ባሕርይ ነው። የአገልግሎት መሠረቱ ያንተ ፍላጎት ሳይሆን ፍቅር ነው።
“ዮናስ ግን ከእግዚአብሔር ፊት ወደ ተርሴስ ይኰበልል ዘንድ ተነሣ፤ ወደ ኢዮጴም ወረደ፥ ወደ ተርሴስም የምታልፍ መርከብ አገኘ፤ ከእግዚአብሔርም ፊት ኰብልሎ ከእነርሱ ጋር ወደ ተርሴስ ይሄድ ዘንድ ዋጋ ሰጥቶ ወደ እርስዋ ገባ።እግዚአብሔርም በባሕሩ ላይ ታላቅ ነፋስን አመጣ፥ በባሕርም ላይ ታላቅ ማዕበል ሆነ፥ መርከቢቱም ልትሰበር ቀረበች” ቁ.3
የሰዎቹን ንሰሐ መግባት አልወደደም፤ በመሆኑም ወደ ተርሴስ መሄድን መረጠ። ከእግዚአብሔር ፈቃድ ስትወጣ ወደ አደጋ ትቀርባለህ፤ አደጋው ደግሞ ላንተ ብቻ ሳይሆን በዙሪያህ ላሉ ሰዎች ሁሉ ይተርፋል። በዚኽ መልክ በእኛ ዙርያ ያሉ ብዙ ነፍሳትን እንጎዳለን አደጋ እንጋርጥባቸዋለን። እንዲህ ያለ ጉዳይ ብዙ ሰውን ይረብሻል።
“መርከበኞቹም ፈሩ፥ እያንዳንዱም ወደ አምላኩ ጮኸ፤ መርከቢቱም እንድትቀልልላቸው በውስጥዋ የነበረውን ዕቃ ወደ ባሕር ጣሉት፤ ዮናስ ግን ወደ መርከቡ ውስጠኛው ክፍል ወርዶ ነበር፥ በከባድ እንቅልፍም ተኝቶ ነበር።”
በመርከብ ውስጥ ያሉት ሁሉ መጸለይ ጀመሩ። ከችግሩ ሊያመልጡ ብዙ ሞከሩ። ጸሎት ትልቅ መፍትሄ መሆኑን የተረዱ ሰዎች ናቸው። መርከቢቱን ከሸክሟ ሊያቀሉ እቃቸውን ወደ ባሕር ጣሉ። ዮናስ ግን ምንም ማድረግ አልፈለገም፤ ወደ መርከቢቱ ታችኛው ክፍል ገብቶ ተኛ። ምክንያቱ ደግሞ ከእግዚአብሔር “ስላመለጠ” ነው። እግዚአብሔርን አኩርፏል፤ ተደበቀ። ግዴለሽ ስትሆን እንዲኽ ነው።
ዮናስ ለዚኽ ሁሉ ምክንያት እርሱ እንደሆነ እያወቀ ንሰሐ መግባት አልፈለገም፤ ይልቁንም መሸሽን መረጠ። መጸለይ እንኳ አልፈለገም። ተኝቶ ያንኮራፋ ነበር። ምንም እንዳልተፈጠረ ሆነ። አንዳንዴ ቤተ ክርስቲያንን ራሳችን እንደበጠበጥን እያወቅን እና ስለተጠቀምን ብቻ ስለ ብዙዎች መጥፋት መጎዳት ምንም የማይመስለን አለን። ዮናስን እንመስለዋለን። ምእመናን ቁም ስቅል ሲያዩ እና ሰራሁላቸው የምንል። ሌላው ወንድሙ ተጨንቆ የታባቱ የሚል ግብዝ ብዙ ነው። ይቅርታ ማለትን ተጸይፎ ፍርድ ቤት የሚያንከራትት አገልጋይም አለ።
ትልቅ ጥፋት ሰርተን ምንም እንዳልተፈጠረ ማሰብ እንሞክራለን። ትርምስ ሲፈጠር ምክንያቱ እኔ ነኝ ማለት አንፈልግም። ቤተሰብ ሲበጠበጥ ባል በሚስቱ ሚስት በባል ትደፈድፍና ራሷን ንጹሕ ታደርጋለች እንጂ እኔ ነኝ ምክንያቱ አትልም። እሱም እንዲሁ።
“የመርከቡም አለቃ ወደ እርሱ ቀርቦ፦ ምነው ተኝተሃል? እንዳንጠፋ እግዚአብሔር ያስበን እንደ ሆነ ተነሥተህ አምላክህን ጥራ አለው” ቁ.6
ለነቢዩ ድምጽ ከአሕዛቡ የመርከብ አለቃ መጣ። አንተ አስተማሪ ነኝ ብለህ ነገር ግን አልሰማ ካልክ እግዚአብሔር የመሳሪያ ችግር የለበትም። “ተነስተህ አምላህን ጥራ አለው” ጸልይ ብሎ አዘዘው። ይህንን ማስተማር የነበረበት ዮናስ ቢሆንም አልሰማ ስላለ አስተማሪ ተላከበት። ከጸለየ ንሰሕ ትገባለህ የእግዚአብሔር ፈቃድ የቱ ነው ብለህ በግልጽ ታያለህ።
የእግዚአብሔር መልእክት ከሁሉም አቅጣጫ ወደ ዮናስ መጣ። በብዙ ነገር ይቀሰቅሰው ነበር። ከማዕበሉ ከነፋሱ ከመርከብ አለቃው መል እክት መጣበት። መጨረሻ ደግሞ እጣ እንጣል አሉ።“እርስ በእርሳቸውም፦ ይህ ክፉ ነገር በማን ምክንያት እንዳገኘን እናውቅ ዘንድ ኑ፥ ዕጣ እንጣጣል ተባባሉ። ዕጣም ተጣጣሉ፥ ዕጣውም በዮናስ ላይ ወደቀ”
የሚገርም ልብ ነው። እጣ የሚጥሉት ጸጥ ባለ ማዕበል ሳይሆን መርከቢቱ ልትሰበር ቀርባ በማዕበል ውስጥ ነው። ዕጣው እውነቱን መሰከረ። ሁሉም ተፈጥሮ የእውነት ምስክርነት ሰጡ። ዮናስ ግን አልሰማም አለ። እጣው ምክንያቱ አንተ ነህ ንሰሐ መግባት አለብህ ይለው ነበር። ዮናስ ግን ምንም እንዳልተፈጠረ ቆጠረ። ምስቅልቅል እየተፈጠረ እያዩ ምንም እንዳልተፈጠረ ማሰብ ከተጥያቂነት አይስመልጥም። ሁሉንም መልእክት አቃለለ ናቀ።
ሰዎቹ የሚችሉትን ሁሉ የድርሻቸውን ተወጡ። ስለ ራስህ ንገረን አሉት ጠይቁት። ዮናስ ምንም ሳይሸሽግ ሁሉንም ነገር ስለራሱ ነገራቸው። ዮናስ የዋኅ ሰው ነው ያሰኘው ይኽ ነው። ዮናስ እየሸሸ ቢሆንም ስለ እግዚአብሔር ግን መሰከረ። ስለ ራሱም አልሸሸገም፤ የማመልከውም ሰማይና ምድርን የፈጠረውን እግዚአብሔርን ነው አለ። እርሱንም እንደሚያገለግል ተናገረ። ተሸሽጌያለሁ ብሎ አልዋሸም። እግዚአብሔርን ሰበከላቸው። “እርሱም፦ እኔ ዕብራዊ ነኝ፤ ባሕሩንና የብሱን የፈጠረውን የሰማይን አምላክ እግዚአብሔርን አመልካለሁ አላቸው”
ሐጢአት ሰርቻለሁ ነገር ግን እግዚአብሔር ባዘዘኝ ሐሳብ አልተስማማሁም አለ። አሁን ነገሮችን ደግሞ ማሰብ ጀመረ። ወደ ልቡ ተመለሰ። እሱ የሁሉም ነገር ምክንያት ነበር። ተስፋ መቁረጥ ተሰምቶታል፤ ተሰላችቷል ነገሮች ሁሉ አስጠልተውታል። እንዲኽ በመሰልቸት የሚያገልግል ብዙ ነው። ያለ እግዚአብሒር መንፈስ ውስጡ ተረብሾ እንዲሁ የሚቆም አለ የቀዘቀዘ አገልግሎት ከባድ ነው። በርዶህ መደሰት አትችልማ። ያለ እግዚአብሔር መንፈስ በቀሚስ ፋሽን መደሰት አይቻልማ። ውጭው አምሮ ውስጡ ሲደርቅ አይጣል ነው ወዳጄ። የደረቀ ነገር መሰበሩ አይቀርም መጀመሪያ ውስጥህ ይሙቅ። ፈረጂያ ቀሚስ ብቻ ሕይወት አይሆንም ቆብ ብቻውን አገልግሎት አይሆንም ዝና ብቻውን ሰው አይለውጥም።
ዮናስ ተነስቶ ከመጸለይ ይልቅ ሞቱን የመረጠ አሳዛኝ ነቢይ ነው። ከምጸልይ ሞት ይሻለኛል አለ። “እርሱም፦ ይህ ታላቅ ማዕበል በእኔ ምክንያት እንዳገኛችሁ አውቃለሁና አንሥታችሁ ወደ ባሕር ጣሉኝ፥ ባሕሩም ጸጥ ይልላችኋል አላቸው” የራሱን ታሪክ ነገራቸው ተናዘዘ፤ ጥሪውን መናቁንም አመነ። እነርሱም የምትነግረን ነገር ከምታምነው ጋር አንድ አይደለም አሉት። እንዴት ሰማይና ምድሩን የፈጠረው አመልካለው እያልክ ለምን ትተኛለህ? ለምን አትጸልይም አሉት። እግዚአብሔርን እያመለከ ይኽንን ማድረጉ ተደነቁ። እያገለገለ ለጸሎት የሰነፈ ሰው መጨረሻው ውድቀት ነው።
ዮናስ የነገራቸውን አመኑ፤ ነቢይነቱን ተቀበሉ፤ አልጠሉትም። በእሱ ጥፋት ላይ ሳይሆን ዮናስ በሚድንበት ነገር ላይ አተኮሩ። አንተ ምክንያት ሆነህ በአንተ ምክንያት መስጠም የለብምን አንተም መዳን አለብህ አሉ። አንተ ደግሞ እግዚአብሒርን የምታውቅ ከሆነ ምን እንደምናደርግ ምራን አሉት “ባሕሩንም ሞገዱ አጥብቆ ያናውጠው ነበርና፦ ባሕሩ ከእኛ ዘንድ ጸጥ እንዲል ምን እናድርግብህ? አሉት።
እርሱም፦ ይህ ታላቅ ማዕበል በእኔ ምክንያት እንዳገኛችሁ አውቃለሁና አንሥታችሁ ወደ ባሕር ጣሉኝ፥ ባሕሩም ጸጥ ይልላችኋል አላቸው” ዮናስ በደለኛ እኔ ነኝ ብሎ በራሱ ፈረደ። በራሱ የፈረደ ሰው ተጨማሪ ክስ የለበትም። ወቃሽም የለበትም። ራስህን ለመከላከል ስትል ነው ሁሉም በማስረጃ የሚሞግትህ። ያኔ መግቢያ ታጣለህ። በራስ እንደመፍረድ ጥሩ ነገር የለም። የዮናስ የዋኅነቱ በራሱ መፍረዱ ነው። እውነቱን ተናገረ ጥፋቱ እኔጋ ነው አለ። እኔን ወደ ባሕር ጣሉኝ ሁሉም ነገር መፍትሔ ያገኛል አለ። አቤት የዋኅነት። ጳጳሱ፣ ቄሱ፣ መሪው፣ ሚኒስቴሩ፣ ፖለቲከኛው በእኔ ጥፋት ነው ሀገር የሚታመሰው በኔ ምክንያት ነው ሰው የሚሞተው ብሎ ቢፈርድና ቢጸጸት ሀገር ይድን ነበር። ሁሉም እኔ የለሁበትም ባይ ነው። "በአንዳንድ አካላት" እያሳበበ ይኖራል።
መርከበኞቹ ጥሩ ልብ ነበራቸው። ዮናስን ለምማትረፍ ብዙ ደከሙ። ለዮናስ ጸለዩለት “ሰዎቹ ግን ወደ ምድሩ ሊመለሱ አጥብቀው ቀዘፉ፤ ዳሩ ግን ባሕሩ እጅግ አብዝቶ ይናወጥባቸው ነበርና አልቻሉም። ስለዚኽ ወደ እግዚአብሔር ጮኸው፦ አቤቱ፥ እንደ ወደድህ አድርገሃልና እንለምንሃለን፤ አቤቱ፥ ስለዚህ ሰው ነፍስ እንዳንጠፋ ንጹሕም ደም በእኛ ላይ እንዳታደርግ እንለምንሃለን አሉ” በእርሱ ነፍስ እንዳይጠየቁ ጸለዩ። እንዴት ያለ ጥንቃቄ ነው?እግዚአብሔር በነቢዩ ደም እንዳይጠይቃቸው ተጠነቀቁ።
ዛሬ የሰው ነፍስ ለማጥፋት ጥንቃቄ የለም። የሰው መዳን ግድ የማይሰጣቸው አገልጋዮች ሕዝቡን የሚፈልጉት ለደሞዛቸው ብቻ የሆኑ አገልጋዮች ያሳዝናሉ። ለምታገለግላቸው ሰዎች ትጸልያለህ? ስለ በደሉህ ሰዎች ትጸልያለህ። ባንተ ምክንያት ስላዘኑ ሰዎች ትጸልያለህ? ሁሉ ይቅርና ጸልይልን ላሉህ ሰዎች ትጸልያለህ? ወይስ መኝታ ብቻ ነው።
ዮናስ ወደ ባሕር ሲጥሉት ችግሩ ቀለለ። የችግሩ ምክንያት ተገኘ አስወገዱት። አንዳንዴ እንዲኽ ይሆናል። ችግሩ አገልጋዩ ከሆነ በንጽሕና ተጠንቅቆ ማስወጣት ተገቢ ነው። አገልጋይ ነውና እንደ ፈለገኝ ልፈንጭ አይባልም። ተጠንቅቀህ በጸሎት ዞር አድርገው። በትህትና አሰናብተው። “ዮናስንም ወስደው ወደ ባሕሩ ጣሉት፤ ባሕሩም ከመናወጡ ጸጥ አለ።” አበቃ።
በነሱ ዓይን ዮናስ ሞቷል። በባሕር ቀብረውታል። ለእሱ ሕይወት ሲባል ዮናስ ወደ ባሕር ልብ ገባ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዚኽ ነው ዮናስን በምሳሌ የጠቀሰው። “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል፥ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም” ማቴ.16:4 አለው።
ዮናስ በባሕር ልብ ውስጥ በአሳ ተዋጠ። የጌታ ወደ መቃብር መግባት ምሳሌ ሆነ። የዮናስ ወደ ባሕር መጣል የመርከበኞቹ መዳን ሆነ። የጌታ መሰቀልና መሞት ለአዳም ዘር ሁሉ መዳን ሆነ። ባሕሩ ጥምቀትን ይወክላል። በመጠመቃችን የጌታን ሞትና ትንሳኤ እንሳተፋለን እንመስለዋለን። “በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችሁ፥ በጥምቀት ደግሞ፥ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አሠራር በማመናችሁ፥ ከእርሱ ጋር ተነሣችሁ” ቆላ.2:12
አይሁድ ጌታን ሰቅለው ሲቀብሩት በቃ አለቀ ደቀቀ ተገላገልን ብለውት ነበር። በአይሁድ ልብ ጌታ ሞቶ ይቀራል ብለው ነበር። ነገር ግን ከመቃብር በኋላ ሕይወት አለ። ዮናስ አልሞተም በባሕር ውስጥ ተቀብሮ ነበር። ከሶስት ቀን በኋላ ሌላ ታሪክ ይጀምራል።
መርከበኞቹ ዮናስን ከጣሉት በኋላ ማዕበሉ ጸጥ አለ። በሆነው ነገር እግዚአብሔር አከበሩ። ዮናስ ሳያስበው በሕይወታቸው ላይ ተጽዕና አሳደረ። ትክክለኛውን እግዚአብሔርን አወቁት። እነርሱ የሚያመልኩት ነፋስና ባሕርን ነበር። አሁን ለእግዚአብሔር መስዋዕት አቀረቡ። “ሰዎችም እግዚአብሔርን እጅግ ፈሩ፥ ለእግዚአብሔርም መሥዋዕትን አቀረቡ፥ ስእለትንም ተሳሉ” ምዕ.1:16
ምዕራፍ ሁለት
ትንቢተ ዮናስ በነገረ መለኮታዊ ትንታኔ
ምዕራፍ ሁለት የሚያስረዳ የዮናስን ጸሎትና ኑዛዜ ነው።
“እግዚአብሔርም ዮናስን የሚውጥ ታላቅ ዓሣ አሰናዳ፤ ዮናስም ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት በዓሣው ሆድ ውስጥ ነበረ” የሶስት ቀን ጉዳይ ለጌታችን ሞትና ትንሣኤ ምሳሌ ሆኖ መቆየቱን ጌታ ጠቅሶታል። ዮናስን መርከበኞቹ ሊያድኑት ብዙ እንደጣሩ ጲላጦስ ጌታ ሊያተርፈው እንደሞከረ የሚያሳይ ነው። ዮናስ ከዚህ የሶስት ቀን መከራ ተርፎ እንደገና ወደ አገልግሎት ይመለሳል። ይኽ የጌታን ትንሣኤ ያሳያል። ከጌታ ወገኖች ሳይቀር ብዙዎች ጌታን ከሞት ይነሳል ብለው አላመኑም ነበር። ጌታ ግን እንደተናገረው በሶስተኛው ቀን ተነሣ። ሰዎች ዮናስ ሶስት ቀን በአሳ ሆድ መቆየቱን ላያምኑ ይችላሉ። እንደውም ታሪኩ ለሕጻናት የሚነገር አፈ ታሪክ ይመስላል። ነገር ግን እውነት ነው። አሳው ግዙፍ በመሆኑ ለዮናስ በቂ ክፍል ነበረው። የቆየው በእግዚአብሔር ተአምር ነው።
በነዚኽ ቀናት ዮናስ እየጾመ እየጸለየ በራሱ ሕይወት ዙሪያ ሰፊ ትንታኔ እየሰጠ ቆየ። ብዙውን ጊዜ በምንኖርበት ዓለም ውስጥ ጥቂት ሰዎች በሕይወታቸው ወሳኝ በሆኑ ውሳኔዎች ከመወሰዳቸው በፊት በገለልተኛ ቦታ በመሆን የራሳቸውን ሕይወት ይተነትናሉ፣ ሱባኤ ይገባሉ። የእግዚአብሔር ፈቃድ በሕይወታቸው ምን እንደሆነ መርምረው ለማወቅ ይጥራሉ። ዮናስ በነዚኽ ቀናት ይበልጥ የእግዚአብሔርን ባሕርይ ዶግማ ተማረ ተረዳ። ለአገልግሎት የጠራው ማን እንደሆነ ተረዳ። የአገልግሎቱን ጥሪ ሳያውቅ የሚያስተምረው ስለማን እንደሆነ የማያውቅ አገልጋይ ሽቱ ተቀብቶ ወደ ንብ ቀፎ እንደሚሄድ ጅል ሰው ነው።
ዮናስ በእስራኤል ከተማ ሳለ አልጸለየም፣ ወደ አገልግሎት ሲላክም አልጸለየም፣ ለመሸሽ መርከብ ውስጥም ቢሆን መጸለይ አልፈለገም። ከዚያ ይልቅ ታችኛው የመርከቧ ክፍል ተኝቶ ነበር። ይኽ ሁሉ ዮናስ ጥፋቱ ነበር። አሁን ግን የሚጸልይበት ጊዜ ደረሰ “ዮናስም በዓሣው ሆድ ውስጥ ሆኖ ወደ አምላኩ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፥ እንዲህም አለ፦” እግዚአብሔር አንዳንድ ጊዜ በተለያየ ምክንያት ወደ ጸሎት ይገፋናል። መጸለይ ባቆምንበት ጊዜ ግዴታ የሆነ አስገዳጅ ጸሎት ውስጥ ይከተናል። ከጸሎት ውጭ ምንም ማድረግ በማንችልበት መንገድ አጣብቂኝ ውስጥ ከቶ እግዚአብሔርን እንድናስታውስ ያደርጋል። በለአም የእግዚአብሔርን መልአክ ያየው ከነ አህያው አጣብቂኝ ውስጥ ከቶት መሆኑን አስብ። እግርህን ሰብሮ ሆስፒታል ውስጥ ተኝትህ እንድትጸልይ ሊያድርግ ይችላል። ሥራ ሥራ እያልክ ቢዚ ስትሆንን ለጸሎት ሰዓትና ጊዜ ስታጣ አጣብቂኝ ውስጥ ይከትህና በል ለጸሎትም ጊዜ ይኑርህ ያንተ ልፋት ብቻ የትም አያደርስህም ይላል።
ዮናስ በዚህ ጊዜ አሳ ሆድ ውስጥ መጸለይ ጀመረ። አሁን የእግዚአብሔር ሰው ወደሚያደርገው ተግባሩ ተመለሰ። ያለ ጸሎት አገልጋይነት ያለ ጸሎት የእግዚአብሔር ልጅነት የለም። በጸሎት የእግዚአብሑር ልጅ መሆንህን ትገልጻለህ። ወላጁን የዘነጋ ልጅ ከንቱ ነው። ዮናስ ጸሎት ሲጀምር በሕይወቱ ለውጥ ማየት ይጀምራል።
ጸሎቱንበእግዚአብሔር መንፈስ መጸለይ ጀመረ። ሲጀምር ደግሞ በተስፋ ነበር “በመከራዬ ሳለሁ ወደ አምላኬ ወደ እግዚአብሔር ጮኽሁ፥ እርሱም ሰማኝ፤ በሲኦልም ሆድ ውስጥ ሆኜ ጮኽሁ፥ ቃሌንም አዳመጥህ” ጸሎትህን በማማረር አትጀመር ተስፋ ይታይህ። ሁሉም ሰው የዮናስን የጸሎት መመሪያ ሊከተል ይገባዋል። ሲኦል ማለት ጥልቅ ጉድጓድ ማለት ነው። ሲኦል ቦታ አይምሰልህ ኁኔታ (state) ነው። ይህንን ትምህርት ለብቻው እመለስበታለሁ። ሲኦል ብዙውን ጊዜ መቃብር ለሚለው አቻ ሆኖ የገባ ቃል ነው። አስፈሪ ሁኔታ ማለፉ ያለበትን ዓለም እንዲገነዘብ ያስቻለው ከመሆኑም በላይ ነዛዜውን እንዲያቀር አደረገው።
ስንጸልይ እግዚአብሔር እየሰማን መሆኑን ማወቅና ማመን ከሁሉም ነገር ይቀድማል። እየቀደሰ እየዘመረ “እግዚአብሔር ግን ይሰማኝ ይሆን” ብሎ የጠየቀ አማኝ እየጸለየ አይደለም። በጸሎታችን እርግጠኝነት ሊሰማን ይገባል። ምክንያቱም እግዚአብሒር የምህረት አምላክ ነውና። መስማት ብቻ ሳይሆን አዳምጦ መልስ ይሰጠናል። ንሰሐችንን ይቀበላል።
ዮናስ ጸሎቱን ሲጀምር ምንም ያየው ነገር የተለወጠ ነገር የለም። ግን እንደሚቀየር አመነ። እግዚአብሔር እየሰማው መሆኑን አመነ እርግጠኛ ነበር። አሁን እምነቱን ቀይሯል።
በባሕር ጥልቅ ውስጥ መሆኑ ምን ያክል አስፈሪ መሆኑን እንገንዘብ። ጨለማ ክፍል ውስጥ ነው። ጥቅጥቅ ያለ ዋሻ። ሶስት ቀን በአሳ ሆድ ውስጥ ምን ተሰምቶት እንደሆነ አናውቅም። እንዴት አሳለፈው? የመከራ ቀኖች እንዲህ በቀልሉ አይገፉምና ያውም ቀን ይሁን ማታ በማያውቅበት ሁኔታ ላይ። "ወደ ጥልቁ ወደ ባሕሩ ውስጥ ጣልኸኝ" ይላል።
አንድ ሰው ጥፋት ሲሰራ የሚሰማው ጥልቅ ውስጥ እንደገባ ሰው ይሰማዋል። በጣም ጨለማ ክፍል ለማንም ቢሆን ይስፈራል። ይኽ ሁኔታ በራሱ ወደ ጸሎት ይመራል። ዮናስ በዚህ ማዕበል ማለፍ የድንገት የተፈጠረ ነገር አይደለም። የእግዚአብሔር እጅ ነበር። ማስተማሪያው መንገድ ነው። እግዚአብሒር ዮናስን ሊያድን የወሰድበት መንገድ መሆኑ ገብቶታል።
በአሳ ሆድ ውስጥ ሆኖ ማዕበሉ ይሰማው ነበር “ፈሳሾችም በዙሪያዬ ነበሩ፤ ማዕበልህና ሞገድህ ሁሉ በላዬ አለፉ” ማዕበል በባሕርዩ ሰላም ይነሳል። ዮናስ አርፎ መተኛት አይችልም ማረፍ አይታሰብም ነበር። በዚህ ሁኔታ መቆየት ቀላል አይደለም። ዮናስ የጥልቁን ኑሮ ቀመሰው ተሰቃየ። “እኔም፦ ከዓይንህ ፊት ተጣልሁ፤ ነገር ግን ወደ ቅዱስ መቅደስህ ደግሞ እመለከታለሁ አልሁ” እግዚአብሔር በእርሱ እንዳዘነ ተረዳ። እኔም አልታዘዝኩም አውቃለሁ። ነገር ግን አሁንም ትወደኛለህ አለ። በትኅትና ሆኖ ጸለየ ይቅር በለኝ እንደገና መቅደስህን እንዳይ አድርገኝ ወደቀደመ ማንነቴ አገልግሎቴ መልሰኝ ሲለው ነው። በዚኽ አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ እየተናዘዘ ነው።
ዮናስ አሳ ሆድ ውስጥ ቢሆንም በውኃ ከመጥለቅለቅ አላመለጠም “ውኆችም እስከ ነፍሴ ድረስ ከበቡኝ፤ ጥልቁ ባሕር በዙሪያዬ ነበረ፤ የባሕሩ ሣር በራሴ ተጠምጥሞ ነበር” ሲል ይገልጸዋል። አስገራሚ ነው። አሳ ሆድ ውስጥ ሆኖ በጨለማ ውስጥ በውኃ በስብሶ ነበር። ቅዝቃዜ በራሱ አጥንቱን ተሰማቶታል። ሰውነቱን ረብቾታል። አሳው ጢሻ ለጢሻ የወሰደው ይመስል ሳሩ፣ ሐረጉ ሁሉ አንገቱን ጠምጥሞ መተንፈስ ከለከለው። እንዴት ምቾቱ እንዳሳጣው ተመልከት።
አሳው ወደ ባሕሩ የመጨራሻው ክፍል ገብቶ ስለነበር “ወደ ተራሮች መሠረት ወረድሁ፤ በምድርና በመወርወሪያዎችዋ ለዘላለም ተዘጋሁ” አለ። ከአሳ ሆድ ውስጥ ሆኖ አሳው ተራራ ግርጌ እንደሚመዘግዘግ ታወቀው። ከባሕር በታች ያሉ ተራሮችን በምናቡ አየ።
ዮናስ ማንም ሰው ወደ እርሱ ሊመጣ እንደማይችል አውቋል። በምድር ላይ ዮናስ ያለበትን ስሜት የሚረዳ የለም ብሎ አስቧል። እርሱ የገባበት ቦታ የገባ የለም አለ። እዚኽ መጥቶ ሊያድነኝ የሚችል የለም። ከእግዚአብሔር ውጭ ማንም ሊደርስ በማይችል ቦታ ወሰደው። አንዳንዴ የሚገጥሙን መከራዎች ብር፣ ሀብት፣ ዝና፣ ዘመድ፣ ሥልጣን፣ ጎሳህ የማይደርሱበት ቦታ አለ። አንተ የራስህ በምትለው እገዛዋለሁ እንደፈለኩ አደርገዋለው በምትለው ግዛት ውስጥ ብቻህን ወስዶ ልክህን ያሳይሃል። ትንሿን ነርቭህን ተጭኖ የሚረዳህ ስታጣ ያኒ ትጸልያለህ። ጣትህ ላይ ትንሽ ቁስል ወጥታ ሙያህ ሊፈውሳት አቅቶት እንቅልፍ ትነሳሀለች። ስንቶችን ስታንበረክክበት የነበረ ገንዘብ አንተ ጋር ሲደርስ አንተን ማዳን አልችልም ይልሃል። ያኔ ሊደርስልህ የሚችለው እግዚአብሒር ብቻ እንደሆነ ታውቃለህ። ከጸሎት ውጭ ምንም ማድረግ የማትሽልበት ቀን አለ። ያ የእግዚአብሔር እቅድ ነው።
ዮናስ እኔ አሁን ከሁሉም ዓለም ሩቅ ነኝ፤ ያለሁበትን ቦታ እንኳ የሚያወቅ የለም ከዚኽ ጥልቅ አድነኝ አለ። ይኽ ስሜት በምቹ አልጋ ላይ ሆነን እንኳ ሊሰማን ይችላል። አልጋውን አሳ ያደርገዋል። ሌሊቱን የረዘመ ይመስልሃል። ወደ ጥልቁ ሲገባ መቀበሩን አውቋል። ከጉድጓዱ አውጣኝ አለ። “አንተ ግን፥ አቤቱ አምላኬ፥ ሕይወቴን ከጕድጓዱ አወጣህ” ዮናስ ትንሣኤ ሙታንን አሳሰበን።
“ነፍሴ በዛለችብኝ ጊዜ እግዚአብሔርን አሰብሁት፤ ጸሎቴም ወደ አንተ ወደ ቅዱስ መቅደስህ ገባች” በጥልቁ ሳለ በጣም ተክዟል። ደክሟል፣ ተሰላችቷል። እኔ ተስፋ ቆርጫለሁ ጥቅም የለሽ ነኝ ይሁን እንጂ የኔን ደካማነት አላይም አንተ እንደ እኔ አይደለህም። ማሰብ የምፈልገው ያንተን መሐሪነት ደግነት ነው የሚወደውን አምላክ አሰበ። ከምንም በላይ ድካሜን የምታውቅ አነተ ነህ አለ።
“ጸሎቴም ወደ አንተ ወደ ቅዱስ መቅደስህ ገባች” በጥልቁ ውስጥ ሆኖ ጸሎቱን በቤተ መቅደስ እንደሚጸልየው ሆኖ ታሰበው። አንድ ቀን ዳግም ወደ ቤተ መቅደስ ሄዶ እንደሚጸልይ አመነ። ዛሬ ያልሔድክበትን መቅደስ እንዲህ ትናፍቀዋለህ። ይኽ የዮናስ የባሕር ውስጥ ተሞክሮ ነው። ዮናስ የራሱን ልብ በመከተሉ ተጎዳ፣ተሳሳተ። እግዚአብሔር የሚወደው እስራኤላውያንን የርሱን ሕዝቦች ብቻ ይመስለው ነበር። አሁን ግን ሁሉንም እንደሚወድ ተረድቷል። ሰይጣን ምንም ጥሩ ነገር ቢነግርህ፣ ተአምር ቢያሳይህ አትመነው ሊያጠምድህ ነው። ቤትህን እሳት ቢያቃጥልብህ ከሰይጣን ውኃ አትዋስ ያልኩህን አስታውስ “ከንቱነትንና ሐሰትን የሚጠብቁ ምሕረታቸውን ትተዋል ” ዝም ብለህ ኢየሱስ ክርስቶስን ተከለል። እውነት እሱ ብቻ ነው። ትጉህ እረኛ እርሱ ነው።
ዮናስ በስተመጨረሻ ሙሉ ተስፋ አሳደረ። ወደ ቤተ መቅደስ እንደሚመለስ መስዋዕትም እንደሚሰዋ አሰበ። ተስፋው ብርዱን ውርጩን አስረሳው። ከመከራው ይልቅ ተስፋው በለጠበት። ምንም ውስጥ ብትሆን ዓይንህን ጨፍነህ ተስፋን እያት። ሰላም ከሌላ ቦታ አትፈልግ አስተሳሰብህ ውስጥ ናት። እግዚአብሒር ከልብህ በላይ ላንተ ቅርብ ነው። በትኅትና ሆኖ ጸልየ “እኔ ግን በምስጋና ቃል እሠዋልሃለሁ፤ የተሳልሁትንም እከፍላለሁ። ደኅንነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው” ኃጢአቱን ተናዘዘ አሁን ጥሪውን ሊፈጽም ተዘጋጅቷል። ምድሪቱን ዳግም እንደሚያይ እያሰበ ነው። ከሕዝቡም ዳግም ሊገናኝ መሆኑ ታየው። ደግሜ ከአንተ ፊት አልጠፋም የትም ቢልከው እንድሚሄድ ተልእኮውን እንደሚፈጽም ወሰነ። የተሳልኩትን ሁሉ እፈጽማለሁ ብሎ ማረጋገጫ ሰጠ። መዳኑን እየጠበቀ ነው ወደ ወደብ መድረሱ ታወቀው “ደኅንነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው” እግዚአብሔር ተአምር እንዲያደር ጠበቀ። ሞቶ ነበር ዳግም ሊኖር ናፈቀ። ልሙት እንጂ አልጸልይም ያለው ዮናስ ጸሎት ሕይወቱ እንደቀየረው ተረዳ። ጸሎት ይቀይራል። የሞትና የትንሣኤን ምስጢር አስረዳን። ጥምቀትን አሳየን። ከጸሎቱ ከተስፋው ከእግዚአብሔር ምህረት የተነሳ ማንም እንዲጠፋ አይፈልግም። ሁሉም እንዲድኑ የእግዚአብሔር ፈቃድ መሆኑን አወቀ።
በምስቅልቅል ጊዜ እንጸልይ፣ ስንጸልይ እንናዘዛለን። እንመን፣ ከልብ እንጸልይ በሌላው አናላክክ ስንጸልይ ሁሉም ይለወጣል፣ ተአምር ይደረጋል፣ የተለየ ሕይወት ይሰጣል። ዮናስ ባይጸልይ ኖሮ አሁን የምናነበውን ትንቢተ ዮናስ አናገኘውም ነበር። በጸሎት አዲስ ቀን እናያለን “እግዚአብሔርም ዓሣውን አዘዘው፥ እርሱም ዮናስን በየብስ ላይ ተፋው” ይላል። አሳው በባሕርይው ከዋጠ አይተፋም ቀረጣጥፎ ያስቀር ነበር። ከነቢዩ ይልቅ አሳው የእግዚአብሔርን ፈቃድ በመረዳት ምላሽ ሰጠ። ዮናስን አጓጉዞ በወደብ ደረቁ ሥፍራ ተፋው።
No comments:
Post a Comment