ምዕራፍ1፡ የ666 እና የአውሬው ምንነት
📌 የ666 ትርጉም፡-
በመጀመሪያ ደረጃ፣ 666 ቁጥር ከክርስትና መጽሐፍ ቅዱስ የመጣ ነው። የዮሐንስ ራእይ 13:18 "ጥበብ ያለው ሰው አውሬውን ቁጥር ያስብ፤ ቁጥሩ ደግሞ የሰው ቁጥር ነውና፤ ቁጥሩም ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት (666) ነው።" በራእዩ ውስጥ፣ "አውሬ" የሚለው ቃል የሐሰት ነቢይ ወይም ፀረ-ክርስቶስ (AntiChrist) ማለት ነው። ስለዚህ 666 የፀረ-ክርስቶስ ምልክት ወይም "ቁጥር" ነው። ይህ ክፉ፣ ከእግዚአብሔር ጋር የሚቃረን ኃይልን ያመለክታል።
ከስሙ ትርጉም ስንነሳ፤ እነዚህ ሦስት ስድስቶች ምንድን ናቸው? በብዙ መልኩ ሊቃውንት አባቶቻችን ቢተረጉሙትም ለግንዛቤ ያህል ሁለቱን ጠቅሼ አልፋለሁ።
✔ 1ኛ... 666 ማለት፤ የመጀመሪያው 6 የሚወክለው የሰው ልጅ የተፈጠረበትን ቀን ነው። ይህም ስድስተኛው ቀን ነው። ሁለተኛው 6 የሚወክለው የቀትር አጋንንት (ማለትም የአየር ላይ አጋንንት) ከሰማይ ወደ ምድር የተበተኑበትን ሰዓት ይወክላል። ሦስተኛውና የመጨረሻው 6 ደግሞ የሚወክለው፤ መድሀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት፣ ጠላት ዲያቢሎስ ድል የተነሳበት፣ ነፍሳት ከሲኦል የወጡበት ሰዓት ስለሆነ በዋናነት እነዚህን ሦስት ስድስቶችን የያዙትን ጊዜአት እንደሚቃወም ለመግለፅ ራሱን በሦስት ስድስቶች (666) ወከለ በማለት ሊቃውንት አባቶች ያመሰጥሩታል።
✔ 2ኛ.... 666 ምንድን ነው ለሚለው ደግሞ፤ አባቶቻችን በጥንት መፅሐፍቶች ላይ ከትበውልን እንዳለፉት፤ ሦስት ስድስቶች የሆኑበትን ምክንያት 'ሥላሴን እቃወማለሁ' ማለት ነው ይላሉ። እንዴት ቢሉ፤ ሥላሴ ማለት 'ሠለሰ' ከሚለው የግዕዝ ግስ የወጣ ሲሆን 'ሦስት አደረገ፣ ሦስት' የሚል ትርጉም አለው። የሥላሴ ሦስትነት ምን አይነት ሦስትነት ነው ቢሉ መልሱ ልዩ ሦስትነት ነው። የስድስቶች ብዛት (666) ሦስት የሆነበት ምክንያት አንድም የሥላሴን ልዩ ሦስትነት እቃወማለሁ ሲል ነው ይላሉ።
በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ምሳሌያዊነት፡- ለምሳሌ 7 ፍፁም ቁጥር ሲሆን - መለኮታዊ ሥርዓት ያመለክታል። በሌላ በኩል 6 ቁጥር የሰውን አመጽን ይወክላል። ስለዚህ ቁጥር 6 ሦስት ጊዜ ሲደጋገም - 666 - ክፉ ፍጹምነት ወይም የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ላይ ያደረገውን አጠቃላይ አመጽ ያመለክታል።
ራዕይ 13፣ 18 ላይ ደግሞ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ሲጥፍ “አእምሮ ያለው የአውሬውን ቁጥር ይቁጠረው ቁጥሩ የሰው ቁጥር ነውና ቁጥሩም ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት (666) ነው፡፡” ብሏል፡፡ ይህም ማለት ብልህና አዋቂ አስተዋይም የሆነ ዕውቀት ያለው የሐሳዊ መሲሕን መጠኑን ያውቃል፡፡ በሰው ልክ መጠን ሦስት ክንድ ከስንዝር ቁመት ያለው ነው፡፡ ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት አስራው (ጅማቶች) ያሉት የዕለተ አርብ ፍጥረት (ሰብአዊ ፍጡር) ነው ማለት ነው፡፡
በሃይማኖት አባቶች ትምህርት የማንኛውም ሰው ጅማት (ሥር) 666 ነው፡፡ ይህንንም አክሲማሮስ የተባለው የቤተ ክርስትያናችን የሥነ ፍጥረት መጽሐፍ ያስረዳል፡፡ ስለዚህ ይህ አውሬ ተብሎ የተጠቀሰው ሐሳዊ መሲሕም ከሰው ወገን የሆነ በዕለተ ዓርብ የተፈጠረ የአዳም ወገን እንጂ ሌላ ፍጥረት አለመሆኑን ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ሲገልጽ “ቁጥሩም የሰው ቁጥር ነው” አለ፡፡ የ666 ትርጓሜ በአጭሩ ይሄን ይመስላል።
📌 የአውሬው ምንነት፡-
ከዚህ በመቀጠል ደግሞ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዩሐ. 8፣47 ላይ “ከእግዚአብሔር የሆነ ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ይሰማል፡፡” እንዳለ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትርጓሜውንና ምስጢሩን እንመለከታለን፡፡
የዮሐንስ ራእይ 13፣4 እና 16-18 የሚከተለውን ይላል፡- “ምድርም ሁሉ አውሬውን እየተከተለ ተደነቀ፣ ለዘንዶውም ሰገዱለት፣ ለአውሬው ስልጣን ሰጥቶታልና፤ ለአውሬውም፡- አውሬውን ማን ይመስለዋል፣ እርሱንስ ሊዋጋ ማን ይችላል? እያሉ ሰገዱለት፡፡… ታናናሾችና ታላላቆችም ባለ ጠጋዎችና ድሆችም ጌታዎችና ባርያዎችም ሁሉ በቀኝ እጃቸው ወይም በግምባራቸው ምልክትን እንዲቀበሉ፣ የአውሬውም ስም ወይም የስሙ ቁጥር ያለው ምልክት የሌለበት ማንም ሊገዛ ወይም ሊሸጥ እንዳይችል ያደርጋል፡፡ ጥበብ በዚህ አለ፡፡ አእምሮ ያለው የአውሬውን ቁጥር ይቁጠረው፤ ቁጥሩ የሰው ቁጥር ነውና፣ ቁጥሩም ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት ነው፡፡” ይላል፡፡ በራዕይ 13፣1 ላይ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ አውሬ ከባሕር ሲወጣ አየሁ አስር ቀንዶችና ሰባት ራሶች ነበሩት፤ በቀንዶቹም ላይ አስር ዘውዶች በራሶቹም ላይ የስድብ ስም ነበር፡፡” ይላል፡፡
🔵 ባሕር የተባለች ማን ናት? ዘንዶውስ ማነው?
✔ ባሕር፡- የተባለችው ይህች ተለዋዋጭና ብልጭልጭ ዓለም ናት፡፡ በባሕር ውስጥ የተለያዩ ፍጥረታት (የውሃ ውስጥ አውሬዎች) አሣ፣ ጉማሬ፣ አዞ፣ አሣ አንባሪ የመሳሰሉት ይኖራሉ፡፡ በምድር ላይም በተፈጥሮአቸው ሰብአዊ ሆነው በግብራቸው በሥራቸው ደግሞ የተለያዩ ሰዎች ይኖሩባታል፡፡ በቅድስና የሚኖሩ እንዳሉ ሁሉ በርኩሰትም የሚኖሩ አሉ፡፡ እንዲሁም በባህር ውስጥ ደጋግ ፍጥረታት እንዳሉ ሁሉ በምድር ላይ ደጋግ ሰዎች አሉ፡፡ ታድያ ባሕር ከማለት መሬት ማለት አይቀለውም? ቢሉ ባሕር የረጋ አይደለም፣ መሬትም በጦርነት በስደት፣ በረሃብ ስትታወክ የምትኖር ስለሆነ የረጋች አይደለችም፡፡
በመሆኑም “አውሬው ከባሕር ወጣ” ሲል፡- አውሬ የተባለው ሐሳዊ መሲሕ ነው፡፡ “ከባሕር ወጣ” ማለቱ ደግሞ የሐሳዊ መሲሕ ስልጣኑ በመጀመር የተረጋጋና የተደላደለ እንደማይሆን መግለጡ ነው፡፡ ስለ ክፉ ስራው (ግብሩም) አውሬ ብሎታል፡፡
🔵 አስር ቀንዶች የተባሉት ምንድን ናቸው?
✔ አሥር ቀንዶች፡ እዚህ ላይ ቀንድ ሲባል ቀንድ አይደለም፡፡ ምክንያቱም አውሬ የተባለው በቁሙ አውሬ ሳይሆን ሰው ነው ብለናልና፡፡ ቀንድ የሚያገለግለው ጠላትን ለመውጋት ነው፣ የሚበቅለውም ከጊዜ በኋላ ነው፡፡ እንዲሁም ይህ መሳቲ ከጊዜ በኋላ መንግስቱን ሲያደላድል በሥሩ የሚሾማቸው ባለሥልናት ናቸው አሥር ቀንዶች የተባሉት፡፡ እነርሱም እንደ ቀንድ የእርሱ ተቃዋሚዎችን እየወጉ ይጥላሉ፡፡ የሚታዘዙትና የሚያገለግሉትም እርሱን ብቻ ነው፡፡
🔵 ሰባት ራሶች የተባሉትስ እነማን ናቸው?
✔ 1ኛ ሰባት ራሶች፡- የተባሉት የአውሬው (የሐሳዊ መሲሕ) ዋና ተገዢ የሚሆኑ ሰባት ሀገሮች ናቸው፡፡ እነርሱም ፋርስ፣ ባቢሎን፣ ግሪክ፣ ሜዶን፣ ግብጽ፣ ሮምና ኢየሩሳሌም ናቸው፡፡ እነዚህም ሰባት አገሮች ሐሳዊ መሲሕ ቁጥጥር ሥር የሚሆኑና መላውን ዓለም በክሕደት ትምህርት በታላላቅ ምትሃታዊ ተአምራት የሚያስቱና የሚያናውጡ ናቸው፡፡
✔2ኛ ሰባት ራሶች፡- የተባሉት በእነርሱ ማለትም በሐሳዊ መሲሑ ዘመን የሚፈጸሙ ሰባቱ ዋና ዋና ኃጢአቶች ናቸው፡፡ እነዚህም ሰባቱ አርዕስተ ኃጣውዕ (የኃጢአት ራሶች) በመባል ይታወቃሉ፡፡
እነርሱም፡-
1. ኃጢአተ አዳም (የአዳም ኃጢአት)
2. ቅትለተ አቤል (የአቤል መገደል)
3. ጥቅመ ሰናኦር (የሰናዖር ህንፃ)
4. ኃጢአተ ሰዶም (የሰዶምና የገሞራ ሰዎች ኃጢአት)
5. ኃጢአተ እስራኤል (የእስራኤላውያን ኃጢአት)
6. ቅትለተ ዘካርያስ ካህን (የዘካርያስ ካህን መገደል)
7. ሞተ ወልደ እግዚአብሔር (የእግዚአብሔር ወልድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት) ናቸው፡፡
🔵 ዘንዶ የተባለው ማነው?
በራዕይ 12፣3 ላይ “ታላቅ ቀይ ዘንዶ” በማለት ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ስለዘንዶው ማንነት ይናገራል፡፡ ይህም ዘንዶ የተባለው አባታችንን አዳምና እናታችንን ሔዋንን ያሳተው ጠላታችን ዲያብሎስ ነው፡፡ “ታላቅ” መባሉ የቀድሞ ተፈጥሮውንና ክብሩን ለመግለጽ ነው፤ የመላእክት ሁሉ አለቃ ነበረና፡፡ “ቀይ” ያለበትም ምክንያት ደግሞ ተፈጥሮው እንደሌሎቹ ብርሃናውያንና እሳታውያን ቅዱሳን መላእክት ከእሳትና ከነፋስ ስለሆነ ነው፡፡ (መዝ. 103፣4 ፤ ዕብ. 1፣7 ፤ ሕዝ. 28፣14 ፤ ኢሣ. 14፣12)
🔵 ምድር ሁሉ አውሬውን ይከተላል (ራዕይ 13፣14)
መላው ዓለም በአውሬው የተመሰለው ይህ ሐሳዊ መሲሕ በሚያደርገው ምትሐታዊ ተአምር ይሳባል፣ ይደነቃል “እውነተኛ አምላክ ነው” እያለም ይከተለዋል ማለት ነው፡፡ በምትሀታዊ ተአምራቱ ሕዝቡን ሁሉ ያስገርም ዘንድ ሥልጣን ለሰጠው ለዘንዶውም ይሰግዱለታል፣ ይገዙለታል፡፡ አውሬውን “ማን ይመስለዋል? ማንስ ይስተካከለዋል? ብቸኛ ገናና አምላክ ነው” ብለው ያመልኩታል ማለት ነው፡፡ (ዘዳ. 13፣ 1-8 ፤ ማቴ. 12፣ 38-39
🔵አውሬው ተሳዳቢ ነው (ራዕይ 13፣ 5-7)
“አውሬው ታላቅንም ነገርና ስድብን የሚናገርበት አፍ ተሰጠው፤ በአርባ ሁለት ወርም እንዲሠራ ሥልጣን ተሰጠው፡፡” ይላል ራዕይ 13፣ 15፡፡ ይህ አውሬ (ሐሳዊ መሲሕ) በመጀመርያ እግዚአብሔርን ይሰድባል፡፡ እግዚአብሔር ማን ነው? የትስ አለ? እግዚአብሐየር እኔ ነኝ፤ አምላክ እኔ ነኝ ይላል፡፡ እውነተኛውን አምላክ ሰዎች እንዳይረዱና እንዳያመልኩት እርኩስ መንፈስ በልባቸው እያሳደረ ያስታል፡፡
ዛሬም ቢሆን ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ፍጡር፣ አማላጅ” የሚሉ አሉ፡፡ እነዚህ ለአውሬው ጥርጊያ መንገድ የሚያዘጋጁ ናቸው፡፡ ምክንያቱም በዮሐ. 1፣ 1-14 ላይ በመጀመርያ ቃል ነበር፤ ቃልም በእግዚአብሐየር ዘንድ ነበር፡፡ ቃልም እግዚአብሔር ነበር … ቃልም ሥጋ ሆነ፡፡” ተብሎ የተነገረለት እግዚአብሔር ወልድን ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስ ለይቶና አሳንሶ ፍጡር አማላጅ ማለት ይህ እግዚአብሔርን መሳደብ ነው፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ፈጣሪ እንጂ ፍጡር አይደለምና፤ ተማላጅ እንጂ አማላጅ አይደለምና፡፡
አውሬው (ሐሳዊ መሲሕ) ስድቡን በዚህ አያበቃም አርባ ሁለት ወር ሙሉ የወደደውን ምትሐታዊ ተአምር እየሰራ ራሱን ብቻ ከፍ በማድረግ የእግዚአብሔር ማደሪያን ይሳደባል፡፡ ይላል ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ በራዕይ 13፣ 6፡፡
🔵 የእግዚአብሔር ማደርያ ማን ናት?
📌 1ኛ የእግዚአብሔር ማደርያ ትሆን ዘንድ ከአንስተ ዓለም መርጦ የቀደሳትና ለተዋሕዶ የመረጣት እመቤታችን ወላዲተ አምላክ ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፡፡ (መዝ. 131፣ 13) ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጣትን የአማላጅነት ክብር፣ የአምላክ እናት መሆኗንና ዘለዓለማዊ ድንግልናዋን መጠራጠርና መካድ ይህ የእግዚአብሔር ማደርያ መሳደብ ነው፡፡ ነቢዩ ቅዱስ ዳዊት ግን “ልዑል ማደሪያውን ቀደሰ፡፡” በማለት ክብሯን እና ልዕልናዋን ተናግሮላታል፡፡ ልዑል የተባለው እግዚአብሔር ሲሆን ማደሪያው የተባለችው ደግሞ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናትና፡፡ (መዝ. 45፣ 4)
📌 2ኛ. የእግዚአብሔር ማደርያ የተባለችው ኢየሱስ ክርስቶስ በገዛ ደሙ የዋጃት፣ ቅዱስ ስሙ የሚጠራበት፣ የሚቀደስባትና የሚሠለስባት፣ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ የሚፈተትባት ቅድስት ቤተ ክርስትያን ናት፡፡ (የሐዋ. 20፣ 20፤ ማቴ. 21፣ 13፤ ሉቃ. 2፣ 49፤ የሐዋ. 5፣ 20)
በዘመናችን የእግዚአብሔር ማደርያ የሆነችውን ቅድስት ቤተ ክርስትያንን የሚነቅፉና የሚያቃልሉ አሉ፡፡ እንዲሁም በማድረግ ለአውሬው መንገድ እየጠረጉለት ነው፡፡
📌3ኛ. ሌላው የእግዚአብሔር ማደሪያ የተባለው ታቦተ ሕጉ ነው፡፡ የታቦት ትርጓሜው ማደሪያ፣ መታያ፣ መገለጫ ማለት ነው፡፡ ንጉሥ በዙፋኑ እንዲገኝ እንዲገለጡ ታቦትም የእስራኤል አምላክ መገለጫ ነውና፡፡ ይልቁንም ቃሉንና ሕጉን የያዘው የጽላት ማደሪያ ነውና፡፡ ዘጸ. 34፣ 12-18፡ 29 ፤ ዘጸ. 25፣ 8-22፤ ዘጸ. 27፣ 20-21፤ ዘጸ. 31፣ 1-7 8፤ ዘጸ. 33፣ 7-11፤ ዘጸ. 34፣ 1-5፡ 29፤ ዘጸ. 40፣ 20-21፤ ዘዳ. 9፣ 9-11)
ምዕራፍ 2፡ ኢሉሚናቲ - ከሚስጥራዊው ማህበረሰብ በስተጀርባ የተደበቀው እውነት
ክፍል 2 ይቀጥላል....





No comments:
Post a Comment