Friday, 5 February 2021

የሰርግ ስነ ስርዓታችንና አማራ ሳይንት

 

ጥር ወር በአብዛኛው የሀገራችን ክፍሎች የሰርግ ወቅት መሆኑ ይታወቃል፡፡ በገጠሩ የህብርተሰብ ክፍል ዘንድም ይህ ወር አድስ ቤተሰብ የሚመሰረትበት ወቅት ነው በአምሃራ ሳይንት ወረዳ ም በሰርግ ወቅት በሽማግሌዎች የሚመረቁ ምርቃቶችና ከሚዜሙ ዜማዎች መካከል በጥቂቱ ፡፡

ይህ ጋብቻ ስሩ ጠለቅ ጫፉ ዘለቅ ያለ ይሁን ፣ልጅቱንና ልጁን ያልምድልን፣ጋብቻውን የአብርሀምና የሳራ ጋብቻ ያድርግልን፣ ልጅ ወሎዶ ለመሳም፣እህል ዘርቶ ለመቃም ያብቃችሁ፣ ለእማ ለአባ ለመባል ያብቃችሁ፣ ለደጀ ሰላሙ ለስጋ ወደሙ ያብቃችሁ፣ እነዚህ የተጋቡ ልጆቻችሁ፣ለዘመድ ለወገን የሚተረፉ ያድርጋቸው፣ በቦታው ደግማችሁ ደግማችሁ ዳሩበት፣ ከውሀ ጢስ ከጢስ ቀልብ ይቀጥናልና ከዚህ እርግማን ይጠብቃችሁ፣ በወንድ ልጅ ተበከሩ በማለት በዕድሜ ባለጸጎች ይመረቃል ፣፡

ሌላው ደግሞ በሰርግ ጊዜ የሚዜሙ ዜማዎች ሲሆኑ አብዛኛውን ጊዚ ሙሽራውን ፤ ሙሽሪትን ና በጥቅሉ የሰርጉን ታዳሚዎች የሚያወድሱ ለጭፈራ የሚያናሳሱ ናቸው ፡፡ እነዚህም ግጥሞች በየጊዜው ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገሩ የመጡ ናቸው ፡፡



አረ ሚዜ ሚዜ ሚዜ አገረ ፈቱ

አይንቀሳቀስም ካልሞላ ቀፈቱ

እከልየ አቦሉ ቁሚ ተጠየቂ

የጠመቅሽው ጠላ ጠጅ ነው አረቂ

እኔማ ዘፈኑን ምን አውቅበት ብየ

ለእከልየ አቦሉ ደስ ይበለው ብየ

አረ ሚዜ ሚዜ ሚዜ ወለላው

በጀ ጠባቡ ላይ ይታያል ገላው

ተከልየ ሚዞች ይሻላል ሙጥሙጥ

ዶሮ ይጎትታል በኩለ ሌሊት

ከበሮውን ምችው አርገሽ ድንቧደንቧ እንደወለደች ላም አታሰኝው እንቧ

እስኪ በእጃችሁም አጨብጭቡበት

እስኪ በእግራችሁም አገልግሉበት

እስኪ ባአፋችሁም ተቀበሉበት

በጣም በምንወዳት በከልየ ሞት

አንሻቸው እንሻቸው እኛን ሁለቱን

የውሃ ላይ ሰርዶ የመሰሉትን

አረ ሚዜ ሚዜ ሚዜ ቀለበቴ

አሰርቸዋለሁ ለክቸ በጣቴ

እከልየ አንገትክን በምን ልመስለው በለጋው ሸንበቆ ያውም ባልበሰለው

ስንደ ቆሎ በገበታ ፣

ነቃ በይ ጋለሞታ

ስንደ ቆሎ በብርሌ፣

ነቃ በል ሽማግሌ

ስንደ ቆሎ በብርጭቆ ፣

ነቃ በይ የእኛ ቆንጆ

የእኛ ሙሽራ ሹራብ ሰሪ፣

ወሰዳት አስተማሪ

ሰንደ ቆሎ በሙዳይ፣

እረኛስ አንለይ

ምን ያለው አማቸ ነው የተክለፈለፈ

ማሩን ከቅቤው ጋር ደብልቆት አረፈ

ልበሽ ለበሽ በሞቴ

የከበረ ግንቦቴ

ጫጉላሽ አብቧል ዛሬ

ሆ! ሆ! ወንድምሽ ኮሬ

ወሶባየ ወሶባየ

የእገሌነው ዘመናየ

ወንድም አበባ ወንድም አበባ

ይዘህ በጊዜ ግባ

ግባ ግባ በከበባ

የከልየ ባለ አበባ

እንዳለሽ ፍርፋሪ

ደግመሽ ደግመሽ ዳሪ

እገልየ አቦሉ የእነ ሶረን ጌታ

በእንኳን በዋንጫና ቅዳው በገበታ

እንደምን ነው አጅባር የነገልየ ቤት

ቢያ በላ ቢያ ጠጣ እማያልቅበት

እኔስ ምን ፈቀደኝ ከደግ ተወልዶ ከደግ የተጋባ

ተደላደለ አንጅ ዛሬስ መች ተዛባ

እረ ወፌ ሆይ ላውርደሽ ወይ

እሜትየን ላሳይሽ ወይ

የት አሉ አባትሽ የት አሉ እናትሽ

ፍቅሬ ከአንች ጋራ ልመረቅልሽ

አስተናገደን እንጅ የኛ ባልደረባ

ሙሽሪትን ይዘን በጊዜ እንድንገባ

እከልየ አቦሉ ደስ ይበልህ ደስ

ፈረስ ያስጋልባል ያሰራኸው ዳስ ፣ወዘተ ይባላል


ጥር 28/2013 ዓ.ም

የአምሐራ ሳይንት የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት


No comments: