1. ንስሮች በከፍታ ለብቻቸው ይበራሉ፦ ንስር ፈፅሞ ከጥንብ አንሳ፣ ቁራና መሰል ትናንሽ አእዋፍት ጋር አብሮ አይበርም።📌 ንስርን በተፈጥሮ ከሚገዳደሩት የወፍ ዝርያዎች መካከል አንዱና ዋነኛ የሆነው ቁራ ነው። ቁራ በንስሩ ጀርባ ላይ በመፈናጠጥ የንስሩን አንገቱን እና ጀርባውን መንከስ ይጀምራል። በዚህን ጊዜ ንስሩ ለመከላከል ወይም ከላዩ ላይ ለማስወገድ የሚያደርገው አንዳችም ዓይነት ምላሽ አይኖርም። ጸብ ውስጥም አይገባም፣ ግጭትም አይፈጥርም።
ከቁራው ጋር እየታገለ ምንም ዓይነት ጊዜና ጉልበትንም አያባክንም። ነገር ግን አንድ ነገር ያደርጋል። ይህም ንስሩ ረዣዥም ክንፎቹን በመዘርጋት ከፍ ወዳለው ወደ ሰማየ ሰማያት መወንጨፍ ይጀምራል።
ከፍታው በጨመረ ቁጥር ቁራው አየር ንብረቱን መቋቋም ስለማይችል መተንፈስ አስቸጋሪ ይሆንበታል። በስተመጨረሻም በኦክስጂን እጥረት ምክንያት ቁራው ከጀርባው ላይ ይወድቃል። ከቁራዎች ጋር ጊዜያችሁን አታባክኑ።
ቀጥታ ወደ ከፍታ ውሰዷቸው። የዚያን ጊዜ መተንፈስ ስለማይችሉ አቅም በማጣት ተሸንፈው ይወድቃሉ። ግዜያችሁንና ጉልበታችሁን ከደካሞች ጋር በመላፋት አታባክኑ። ከፍታን ምረጡ!! እናንተ ከፍ ስትሉ ራሳቸው ይወድቃሉ እንጅ እነሱን ለመጣል ምንም ጉልበት አታባክኑ!!!
📌 አንሰው ከሚያሳንሱን፤በስሁት መንገድ ከሚነጉዱ፤ የአስተሳሰብ አድማሳቸውም ውስን ከሆኑ ሰዎች ራሳችንን እናርቅ። ንስር ከቁራ ጋር ማኅበር የለውም። ወዳጃችሁን አስምሩ፤ አዋዋላችሁን መርምሩ።
2. የንስር እይታ እንከን የለሽ ነው፦ ንስር እስከ 5 ኪ·ሜ ድረስ ጥርት አድርጎ፤ ዒላማውን አነጣጥሮ የማየት ፀጋን የታደለ ነው። ምንም ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙት እንኳን ታዳኙን እስኪይዝ ድረስ ካነጣጠረበት ዒላማው ላይ ዓይኖቹን ላፍታ ዘወር አያደርግም። .
📌 የፈለገ ያህል መሰናክል ቢያጋጥማችሁ እንኳን የታወቀ መዳረሻ ግባችሁን በውል አውቃችሁ እዚያ ላይ ትኩረት አድርጋችሁ እስከተንቀሳቀሳችሁ ድረስ ኅልማችሁን መኖራችሁ የተረጋገጠ ጉዳይ ነው። አስር ያባረረ አንድ አይዝም ነው ነገሩ።
3. ንስሮች ጥምብ አይበሉም፦ ንስር የበከተ ነገር አይመገብም፣ ራሱ ያደነውን ነገር ይበላል።
📌 በትናንት ስኬታችን ከመዘናጋት ይልቅ ወቅታዊና ስትራቴጂካዊ አዳዲስ አውዶች ጋር ለመጋፈጥና ሁሉንም እንደየአውዱ በድል ለመሻገር ወትሮዝግጁ መሆን ያሻል። ትናንትን ለትናንት በመተው ልምድ ቀስሞ መሻገሩ ተመራጭ ይሆናል።
4. ወጀብ ለንስሮች ፍስኃ ነው፦ ደመናት መሰባሰብ ሲጀምሩ ንስር ልቡ ሐሴትን ታደርጋለች። ንስሩ ወጀቡን ለክንፎቹ መንሳፈፊያና ወደ ከፍታ መመንደጊያ ይጠቀምበታል። ንስር ወደ ወጀቡ የሚወስደውን አውሎ ሲያገኝ በአውሎው ኃይል ከደመናው በላይ ከፍ ብሎ ለመውጣት ይጠቀምበታል። ይኼ ደግሞ ለንስሩ ክንፎቹን ያለ ድካም ዘርግቶ እንዲበር ምቹ ሁኔታን ይፈጥርለታል። ንስር ከደመና በላይ፤ ከወጀቡ በላይ በክብር ሲንፈላሰስ ሌሎች አእዋፋት በአንፃሩ የዛፍ ቅርንጫፎችን ከወጀቡ መጠጊያ መሸሸጊያ ለማድረግ ይራኮታሉ።
📌 ችግር በእዬዬና ዋይታ አይፈታም። ይልቅ ችግርህን ፊት ለፊት ተጋፈጠው። ችግርህን መጋፈጥ ቢያበረታህ እንጂ አይሰብርህም።ችግር የብልኃት መምህር ነው። እንዲያውም ያጋጠመህ ችግር ከገባህበት የትናንት አርንቋ ተመንጭቀህ እንድትወጣ ኃይልና ብርታት ይሆንሃል። ችግር ወደ ከፍታው መውጫ መንገድ ነው። የአሸናፊዎች ቦታቸው ከፍታ ነው። አሸናፊዎች በሚያጋጥማቸው ፈተናና ችግር ከመነፋረቅና መቆዘም ይልቅ ወደ ምቹ አጋጣሚ በመቀየር ነጋቸውን በአስተማማኝ መደላድል ለማቆም ለሚያደርጉት ጉዞ እንደመስፈንጠሪያ ይጠቀሙበታል።
5. ንስሮች ራሳቸውን ለልምምድና ሥልጠና ያዘጋጃሉ፦ ንስሮች በጎጇቸው የጎዘጎዙትን ለስላሳ የላባ ስጋጃና የሳር ዳውጃ አስወግደው ጫጩቶቻቸው ጎርባጣውን እንዲያውቁት፤ ሲጎርብጣቸውም ከጎረበጠው ጎጆ በመውጣት መብረር እንዲለማመዱ ያደርጋሉ። በእርግጥም በእሾሃማ ጎጆ ከመቀመጥ ወጥቶ መብረር ለጫጩት ንስሮች አማራጭ የሌለው ምርጫቸው ስለሚሆን በረራን መላመድ ግድ ይሆንባቸዋል። በዚያውም በረራን እንዲህ ይለምዳሉ።
📌 ከለመድኸው የምቾት አንቀልባ ውረድና በእግርህ ተጓዝ። ተንቀሳቀስ፤ እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል!
6. ንስር ራሱን ያድሳል፦ ንስር ዘመኑ በሄደና ባረጄ ጊዜ ወጀቡን የሰንጠቁ፤ ከደመና በላይ ያስቧረቁ አክናፋቱ መዛል ይጀምራሉ። ክንፎቹ ልቡ ባሰበበት ቦታ፥ በተመኘውም ጊዜ ማክነፍ ይሳናቸዋል። እንደልቡ ወደ ሰማይ ልብ ሰንጥቆ በመብረር ከፍታው ላይ ለመገማሸርም አያስችሉትም። በዚህ የተነሳም ንስሩ አቅመቢስነት እየተሰማው ሄዶ ሄዶ ለሞትም ይቃረባል። በዚህ ጊዜ ወትሮ ለአደንና ፈንጠዝያ ከሚፏልልበት ቦታ ሁሉ በመቅረት ወደ ረጅም አምባ፤ ማንም ወደ ማይደርስበት ተራራ ይመንናል። ያረጁና የበሰበሱ ላባዎችንም ነቃቅሎ ያራግፋል። ከቋጥኝ ጋር በማጋጨትም የተቆለመመ መንቆሩንና የዶለዶሙ ጥፍሮቹን ጨርሶ ያወላልቃል። ይኽም የሚቆጠቁጥ ቁስልና ከፍተኛ መድማትን ያስከትልበታል። አዲስ ላባ፣ የሾለ መንቆርና ስለታም ጥፍሮች እስኪበቅሉለት ድረስም ራሱን በነጠለበት የምናኔ ተራራው ደብቆ ያቆያል። እንዳዲስ ሲበቅልሉትም ራሱን አድሶ ከዚህ በፊት ይበርበት ከነበረው ከፍታ በላይ መብረር የሚያስችል አቅም ገንብቶ ይወጣል።
📌 ከተለመደው አሰስ ገሰስ ልምድ መላቀቅ ያስፈልጋል። ለዛሬያችንም ሆነ ለወደፊት መዳረሻችን እሴት የማይጨምሩ አስካሁን ይዘናቸው የነበሩ ልምዶች፣ አሰራሮችና አስተሳሰቦች ካሉ ለመተው ዝግጁ ልንሆን ይገባል።
ንስር እባብን መሬት ላይ ሆኖ አይዋጋውም። ይልቁንስ ወደ ሰማይ ጠልፎ ይዞት በመውጣት የፍልሚያውን መድረክ ይለውጠዋል፤ ከዚያም እባቡን በሰማይ ላይ ይለቀዋል።
እባብ በአየር ላይ ምንም ዓይነት የመቋቋም ኃይልም ሆነ ሚዛኑን የመጠበቅ አቅም የለውም። በመሬት ላይ እንዳለው ብርታትና ጥበብ በሰማይ ላይ የለውም። በምድር ላይ ብርቱ፣ ልባምና ገዳይ እንደሆነው ሳይሆን፤ በአየር ላይ ግን ረዳት የሌለው፣ የተልፈሰፈሰና በቀላሉ የሚጠቃ ይሆናል።
አንተም ውጊያህን በጸሎት ወደ መንፈሳዊው ከፍታ ውሰደው፤ በዚያ በመንፈሳዊው የውጊያ ዓውድ ስትገኝ፣ እግዚአብሔር የአንተን ውጊያ ሙሉ በሙሉ በኃይሉ ይመራል። ልክ ንስሩ እባቡን ከምድር ኃይሉ እንዳራቆተው፣ አንተም ጠላትን ከመንፈሳዊ ኃይሉ ታራቁታለህ።
ጠላት ምቾት በሚሰማውና ባሸነፈበት በሚመስለው መስክ፣ በራሱ የጥንካሬ ጎሬ ውስጥ አትጋፈጠው። እንደ ንስሩ የውጊያውን መድረክ ቀይርና፣ ከልብ በሆነ ጸሎትህ የእግዚአብሔር መለኮታዊ ክንድ ጣልቃ እንዲገባና የፊትህን ውጊያ እንዲዋጋልህ አድርግ።
ያኔ፣ ንጹሕና ፍጹም የሆነ ድል እንደምትቀዳጅ ፈጽሞ አትጠራጠር!! ድሉም የአንተ ሳይሆን፣ በአንተ በኩል የተገኘ የእግዚአብሔር ድል ይሆናል!



No comments:
Post a Comment