Monday, 24 April 2023

ስለእመቤታችን ስዕለ አድኖ

 አንባቢያን ልታስተውሉት የሚገባው እጅግ በምስጢር ከተሞላው የእመቤታችን ስዕለ አድኖ እኔም እናንተም በጥቂቱ እናውቅ ዘንድ በማሳጠር በአጭር አማርኛ የፃፍኩት እና ሌሎች ትርጓሜዎችም ያሉት መሆኑን ልትረዱ ይገባል!! በተጨማሪ ቀስት ከቀስት ለይታችሁ ተመልከቱ!



#ሀ > አክሊለ ብርሃን ሲሆን ይህም በሁሉም ቅዱሳን አናት ላይ ተደርጎ የሚቀመጥ ሲሆን ቅዱስነታቸውን፤ መንፈስ ቅዱስ ያደረባቸው መሆኑን ያመለክታል!

#ለ > የእመቤታችን ከውስጥ የምትለብሰው ቀይ ልብስ ፤ አረጋዊ ስምዖን በነፍስሽ ሰይፍ ያልፋል እንዳላት ጌታን ከፀነሰች ጀምሮ ከእርሱ ጋርም የደረሰባትን ሀዘን፤ ጭንቁን፤ መከራዋን ሁሉ የሚያመለክት ሲሆን አንድም እሳተ መለኮትን በውስጧ የተሸከመች መሆኗን ያመለክታል!!

#ሐ > በእመቤታችን በስተ ቀኝ ትከሻዋ ላይ ያለው ኮከብ ጊዜ ወሊድ ድንግል መሆኗን ያመለክታል!

#መ > የጌታ ሁለቱ ጣቶች ሁለቱን የጌታ ልደታት ማለትም 1) ቅድመ ዓለም ከአብ ያለ እናት፤ 2) ድኅረ ዓለም ያለ አባት ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለዱን ያመለክታል!

#ሠ > እመቤታችን በእጇ የምትይዘው መሐረብ ወይም ሰበን ለቶማስ የስጠችውን እና አባቶች በእጅ መስቀላቸው ላይ የሚይዙት የሰበኗ ምሳሌ ነው!

#ረ > እመቤታችን ከላይ የምትለብሰው ሰማያዊ ልብስ አንድም እንደ ሰማያዊያን በፍፁም ቅድስና የተገኘች እና አንድም ሰማይና ምድር የማይወስኑትን አምላክ በማህፀኗ የተሸከመች ዳግሚት ሰማይ መሆኗን ያመለክታል!

#ሰ > የእመቤታችን ሁለቱ ጣት በነፍስም በሥጋም በሁለት ወገን ድንግል (ድንግል በክልኤ) መሆኗን ያመለክታል!

#ሸ > ከእመቤታችን ከእራስ ላይ ያለው ኮከብ ቅድመ ወሊድ ድንግል መሆኗን ሲያመለክት በተመሳሳይ ጌታ በተቀመጠበት በስተ ግራዋ አቅጣጫ ትከሻዋ ላይ ባማይታይ ከውስጥ አንድ ኮከብ አለ፤ እርሱም ድኅረ ወሊድ ድንግል መሆኗን ያመለክታል!

#ቀ > በእመቤታችን እራስ ላይ ያለው ዘውድ አባቷ ዳዊት " የወርቅ ልብሷን ተጎናፅፋና ተሸፋፍና ንግስቲቱ በቀኝህ ትቆማለች " እንዳለ ጌታን በመውለዷ የሰማይም የምድርም ንግስት መሆኗን ያመለክታል!

#በ > በእምቤታችን በልብሶቿ ላይ ያለው የወርቅ መጎናፀፊያ ቀድሞ በብሉይ ታቦተ ፅዮን በወርቅ ትለበጥ እንደነበረ፤ አማናዊት ታቦት እመቤታችን በንፅህና እና በቅድስና ያጌጠች የተለበጠች መሆኗን ያመለክታል!

#ተ > በጌታ እጁ ላይ ያለው መፅሐፍ ጌታ እየዞረ ያስተማረው የወንጌል ምሳሌ፤ አንድም ቸር እውነተኛ መምህርም እርሱ መሆኑን የሚያመለክት ነው!!

 .                              

No comments: