የአድዋ ድል የጥቁር ህዝቦችና የመላው አፍሪካ ኩራት ነው። ከዛሬ 125 ዓመታት በፊት ፋሺስቱ የኢጣሊያ ጦር ባህር ተሻግሮ፣ ድንበር ጥሶ በመጣ ጊዜ ጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን ለወሬ በማይመች መልኩ ውርደትን አከናንበው ሸኝተውታል። ባልዘመነ የጦር መሳሪያ ጠላትን ለመመከት አድዋ የዘመተው የኢትዮጵያ ጦር ታላቅ ነኝ ያለችውን ኢጣሊያን ያንበረከከው አቻ በሚባል የውጊያ ስልቱ አይደለም። የዛኔ በውስጡ ከሰነቀው አይበገሬነት በቀር በቂ የሚባል ትጥቅን አልያዘም።
ያለአንዳች መጫሚያ በባዶ እግሩ ተጉዞ በሶሎዳ ተራሮች ዙሪያ ሲተም እዚህ ግባ ከማይባል ኋላ ቀር መሳሪያውና ከጦርና ጋሻው በቀር ጠንካራ መከላከያ አልነበረውም። አባቶቻችን ትናንት በከፈሉልን መስዋዕትነት ዛሬ ላይ ቆመን የምንመሰክረውን አኩሪ ታሪክ ጽፈውልናል። በእነ እምዬ ምኒልክ ደምቆ የታተመው ጀግንነትም ከሀገራችን አልፎ ለጥቁር አፍሪካ ህዝብ የነጻነት ምልክት ሊሆን በቅቷል።
መላው አፍሪካ በቅኝ ግዛት ቀንበር በወደቀበት ዘመን ኢትዮጵያ «እምቢኝ» ስትል ታላቅ የተጋድሎ ዋጋ መክፈሏን ዓለም ያውቀዋል። ይህ መሆኑ ደግሞ ዛሬ እንደሌሎች ሀገራት የነጻነት ቀኗን ሳይሆን የድል በአሏን ለማክበር ግንባር ቀደም አድርጓታል። ይህን ተጋድሎ የውጭ ሀገራት ጸሀፍት ሳይቀሩ በበርካታ ታሪካዊ ድርሳናቸው ሲከትቡት ኖረዋል።
ከሁሉም በላይ ግን በተለያዩ የኪነ-ጥበብ ዘርፎች እየተዋዛ ሲቀርብ የቆየው የኪነ-ጥበብ አውድ ግዙፉን ታሪክ ይበልጥ አጉልቶ ለማሳየት ታላቅ አቅምን መፍጠር ችሏል።
አድዋ በሎሬት ጸጋዬ ብዕር ዋ! አድዋ
ከኪነጥበብ ማሳያዎች አንዱን ስናነሳ ደግሞ በዋናነት የሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህንን የስንኝ ቋጠሮ እናስታውሳለን። ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን አድዋን ባነሳበት ስንኙ የጦርነት ውሎውንና የተገኘውን አኩሪ ድል ለማሳየት ሞክሯል። የአድዋ ጦርነት የኋላ ታሪክ የእያንዳንዱ ኢትዮጵዊ አኩሪ ድል የሁሉ አፍሪካዊ ደማቅ ታሪክ ነው። ይህንን ሀቅ