ገሀድ :
➢. ገሃድ የቃሉ ትርጉም መገለጥ መታየት ነው፡፡ በጥምቀት መገለጥ መባሉ ሰው የሆነው አምላክ በዓለም ሲኖር እስከ 30 ዓመት እድሜው ድረስ ሰዎችን ለማዳን የመጣ መሲህ ሰው የሆነበት፣ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ እሱ መሆኑን ሳያውቁ ከኖሩ በኃላ በ 30 ዓመት እድሜው በባሕረ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ እጅ ሲጠመቅ አብ በደመና ሆኖ ‹‹የምወደው ልጄ ይህ ነው›› በማለቱ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል በራሱ ላይ ሲያርፍ በመታየቱ ነቢያት ይወርዳል ይወለዳል ይሰቀላል ይሞታል ይነሳል ብለው የተናገሩለት መሲሕ እርሱ መሆኑ ተገልጦአልና እንዲሁም ሦስቱ አካላት በአንድ ጊዜ ታይተዋልና ምስጢረ ሥላሴ የተገለጠለት በመሆኑ ገሃድ ይባላል፡፡(ማቴ 3፡13-17)
ይህን በማሰብ ይምንጾመው ጾም “የገሃድ ጾም” ይባላል፡፡ ቀኑም ጥር 10 ቀን ለ 11 አጥቢያ ነው፡፡ስለዚህ ጥር 10 ቀን ከ ሰባቱ አጽዋማት አንዱ የሆነው የገሀድ ጾም ነው ማለት ነው!
ከተራ
ከተራ ከበበ ካለው የግእዝ ግሥ የወጣ ነው፡፡ ፍችው ውኃ መከተር፣ መገደብ ማለት ነው፡፡ የጥምቀት ዋዜማ ታቦተ ሕጉ ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ውኃ ባለበት አካባቢ ስለሚያድር የየአጥቢያው ሕዝብ እየተሰበሰበ በወንዝ ዳር ወይም በምንጭ አካባቢ ድንኳን ይተከላል፡፡ ድንኳንም ከሌለ ዳስ ሲጥል ይውላል፡፡ የምንጮች ውኃ ደካማ በመሆኑ እንዲጠራቀም ይከተራል ጉድጓድ እየተቆፈረ ውኃው እንዳይሄድ ይገደባል፡፡
➢• በበዓለ ጥምቀት የታቦታቱ ወደ ወንዝ መውረድ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በእደ ዮሐንስ ለመጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ በዋዜማው የመኼዱ ምሳሌ ነው፡፡ ታቦቱ የጌታችን፣ምሳሌ ሲኾን ካህናቱ የመጥምቁ ዮሐንስ ምሳሌ ሲኾን መዘምራኑና ሕዝቡ ደግሞ ዮሐንስ ያጠመቃቸው ሕዝቦች ምሳሌዎች ናቸው፡፡
➢• በባሕረ ጥምቀቱ ላይ በሚንሳፈፍ ነገር መብራት መደረጉ በርግብ አምሳል ለወረደው መንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ነው፡፡ "የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦትና ሌዋውያን ካህናት ተሸክመውት ባያችሁ ጊዜ፥ ከሰፈራችሁ ተነስታችሁ ተከተሉት። " ኢያሱ 3:3
በዓለ ጥምቀት
➢ የጥምቀት በዓል አከባበር በኢትዮጵያ የተጀመረው የክርስትና እምነት እንደገባ መሆኑ ይታመናል። እስከ ስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ ግን የጥምቀት በዓል የሚከበረው አሁን በሚከበርበት ሁኔታ አልነበረም።
➢ በዓለ ጥምቀትን በሜዳና በውኃ አካላት ዳር ማክበር የተጀመረው በዓፄ ገብረ መስቀል ዘመነ መንግስት (530 - 544 ዓ.ም.) እንደሆነ ይነገራል። ይህም ከማኅሌታይ ቅዱስ ያሬድ (505 - 572 ዓ.ም.) ዜማ መስፋፋት ጋር ይያያዛል። ታቦታቱ በየዓመቱ ጥር 11 ቀን ጠዋት ወደ ወንዝ ወርደው ማታ ወደ መንበረ ክብራቸው እንዲመለሱ ይደረግ ነበር።
➢ ጻድቁና ጠቢቡ ንጉሥ ላሊበላ (1140 - 1180 ዓ.ም.) ሁሉም አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ለየብቻቸው በሚቀርባቸው ቦታ በተናጠል ሲፈጽሙት የነበረውን ክብረ በዓል አስቀርቷል። በምትኩም በአንድ አካባቢ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት በአንድነት ተሰባስበው በአንድ ጥመቀተ ባሕር እንዲያከብሩ ትእዛዝ አስተላልፏል። ይህም ተግባራዊ በመሆኑ የበዓሉ አከባበር ሥነ ሥርዓት ቅንጅት እና ድምቀት እንዲኖረው ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።
➢ ከዚህም ባሻገር በቅዱስ ላሊበላ ዘመነ መንግሥት በኢትዮጵያ ምድር እየተመላለሱ በብሕትውናና በስብከተ ወንጌል ተግተው ያገለግሉ የነበሩ ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በአክሱም፣ በመቀሌና በመርጡለ ማርያም እየተዘዋወሩ ባሕረ ጥምቀቱን ባርከዋል።
➢ በዐፄ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት (1260 - 1275 ዓ.ም.) በጻድቁ አቡነ ተክለሃይማኖት (1203 - 1304 ዓ.ም.) አሳሳቢነት የተጀመረው ሥርዓተ በዓል ተጠናክሮ እንዲቀጥል በዐዋጅ ትእዛዝ አስተላልፈዋል። ታቦታቱም በሕዝብ ጥበቃና ክብካቤ ተደርጎላቸው በየጥምቀተ ባሕሩ እንዲያድሩ ወስነዋል። በዚህም ምክንያት የበዓሉ አከባበር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋና አድማሱ ብሔራዊነትን እየያዘ መጣ።
➢ በመንፈሳዊነታቸውና በደራሲነታቸው መጻሕፍትን ጽፈው፣ ሥርዓትን ሠርተው ለቤተ ክርስቲያን ያበረከቱት ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ (1426 - 1460 ዓ.ም.) ታቦታቱ ወደ ወንዝ ወርደው ዕለቱን እንዳይመለሱ፣ በዚያ ፈንታ በጥምቀት ዋዜማ ጥር 10 ቀን ከሰዓት በኋላ ወደ ባሕረ ጥምቀቱ ወርደው እንዲያድሩ፣ አገሩን በኪደተ እግር ይባርኩም ዘንድ በሄዱበት መንገድ እንዳይመለሱ በዐዋጅ ወሰኑ።
➢ ይህን ታሪክ በመከተል ዐፄ ናዖድ (1486 - 1500 ዓ.ም.) ማንኛውም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ምእመን ታቦተ ሕጉ ወደ ባሕረ ጥምቀቱ በሚወርድበትና ከባሕረ ጥምቀቱ ወደ ቤተ መቅደሱ በሚመለስበት ጊዜ አጅቦ አውርዶ፣ አጅቦ መመለስ እንዳለበት በዐዋጅ አስነግረው ነበር። ሕዝቡም ታቦታተ ሕጉን በሆታ እና በእልልታ ከቤተ መቅደስ አጅቦ ካወጣ በኋላ በባሕረ ጥምቀት ከትሞ ማደር ጀመረ። ሊቃውንቱም እንዲሁ ለበዓሉ የሚስማማውን ቃለ እግዚአብሔር እያደረሱ ያድሩ ጀመር!!!
መልካም በአል።
No comments:
Post a Comment