ከዓመት እስከ ዓመት - ፍሬን ሳላፈራ - ደረቅ እንደሆንኩኝ
በራድ ወይም ትኩስ - ሁለቱንም ሳልሆን - እንዲያው ለብ እንዳልኩኝ
አለሁኝ በቤትህ - ለሙን መሬትህን - እያጎሳቆልኩኝ
አውቃለሁ አምላኬ - ፍሬዬን ለመልቀም - እንዳመላለስኩህ
ዛሬም ሳላፈራ - እሾህን አብቅዬ - ደርቄ ጠበቅሁህ
ያልተደረገልኝ - ያላፈሰሰክብኝ - ያልሰጠኸኝ የለም
ነገር ግን ይህ ሁሉ - አላርምህ አለኝ - አልለየኝም ከዓለም
የማትሰለቸኝ ሆይ - ተነሥቼ እስክቆም - እባክህ ታገሠኝ
የእኔን ክፋት ተወው - መልአክህን ሰምተህ - ይህችን ዓመት ተወኝ!
አውቃለሁ ታውቃለህ - ቀጠሮን ሰጥቼ - እንደማላከብር
ብዙ ጊዜ አቅጄ - ብዙ ጊዜ ዝቼ - በወሬ እንደምቀር
‹ዘንድሮስ…!› እንዳልኩኝ - አምና ይሄን ጊዜ - ሰምተኸኝ ነበረ
ምንም ሳልለወጥ - ‹ዘንድሮዬ› አልፎ - በአዲስ ተቀየረ
ፍሬ የማይወጣኝ - እኔን በመኮትኮት - እጆችህ ደከሙ
እኔ ግን አለሁኝ - ዛሬም አልበቃኝም - በኃጢአት መታመሙ
የቃልህን ውኃ - በድንጋይ ልጅህ ላይ - ሳትታክት ስታፈስስ -
ዘመን ተቆጠረ
ወደ ልቤ ሳይሰርግ - ሕይወቴን ሳይለውጥ - እንዲያው ፈስሶ ቀረ
ቃልህን ጠግቤ - እያገሳሁት ነው - ሌሎች እስኪሰሙ
በቃልህ መኖር ግን - አልያዝህ አለኝ - ከበደኝ ቀለሙ
ብዙ ጥቅስ አገኘሁ - ከቅዱስ መጽሐፍህ - ገልጬ አይቼ
ከራሴ ላይ ብቻ - አንድ ጥቅስ አጣሁኝ - በበደል ተኝቼ
ውጤቴ ደካማ - ትምህርት የማይሠርጸኝ - ተማሪ ብሆንም
ይህችን ዓመት ተወኝ - ደግሞ ትንሽ ልማር - ታገሠኝ አሁንም!
እባክህ አልቆረጥ - በቅዱስ መሬትህ - ልቆይ ፍቀድልኝ
ያፈሩት ቅዱሳን - የፍሬያቸው ሽታ - መዓዛ እንዲደርሰኝ
የተሸከምከኝ ሆይ - ዛሬም ተሸከመኝ - አትሰልቸኝ አደራ
ማን ይታገሠኛል - ጠላት እየሆንኩት - አይሠሩ ስሠራ!
አታውጣኝ ከቤትህ - ብዙ ቦታ አልይዝም - ፍሬ ስለሌለኝ
ስፍራ የማያሻኝ - ቤት የማላጣብብ - ፍሬ አልባ በለስ ነኝ!
ቦታስ የሚይዙት - ባለ ምግባሮቹ - ቅዱሳንህ ናቸው
ልክ እንደ ዘንባባ - የተንዠረገገ - ተጋድሎ ጽድቃቸው!
ከሊባኖስ ዝግባ - እጅጉን የበዛ - ገድል ትሩፋታቸው!
እኔ አይደለሁም - ቦታስ የምትይዘው - የአንተው እናት ናት
ሥሮቿ በምድር - ጫፎቿ በሰማይ - ሲደርሱ ያየናት
ይሀችን ዓመት ተወኝ - ከሥርዋ እሆናለሁ - ባፈራ ምናልባት!..
ይህችን ዓመት ተወኝ - እባክህ አምላኬ - አንድ ዓመት ምንህ ናት
ሺህ ዓመት አንድ ቀን - አይደለም ወይ ለአንተ - ዓመት ኢምንት ናት!
ይሄ ዓመት አልፎ - ዳግም ‹ዓመት ሥጠኝ› - እስከምልህ ድረስ
እባክህን ጌታ - ይህችን ዓመት ተወኝ - የወጉን እንዳደርስ!
ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
---
No comments:
Post a Comment