አንስጣስዮስ ከሮም ወደ ፍልስጤም በፈቃደ እግዚአብሔር ሄደ።በዚያም ከክቡራን መኳንንት፣ ከታላላቆች መሳፍንት መካከል አንዱ ነበር። ከፍልስጤም ዕጻ ከምትሆን ድያስ ከተባለች አገር ቴዎብስታ (አቅሌስያ) የምትባል ደግ ሚስት አገባ። የቴዎብስታ የስሟ ትርጓሜ ቤተ ክርስቲያን ማለት ነው። አቅሌስያም እንደ ስሟ የተቀደሰች፣ የተመሰገነች፣ የተባረከች፣ የተመረጠች በብርሃኑ ዓለምን ሁሉ ያበራውን የሰማዕታትን ኮከብ ይሸከም ዘንድ እግዚአብሔር ማህጸኗን የባረከላት ሴት ነበረች።እነዚህ ሁለት ደጋግ የእግዚአብሔር ሰዎችም ዘሮንቶስ (አንስጣስዮስ) እና ቴዎብስታ (አቅሌሲያ) በእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ ተጋብተው በህይወታቸው እግዚአብሔርን የሚያስደስት ተግባር ይፈጽሙ ነበር። ጥር 20 ቀን 277 ዓ.ም በሀገረ ፍልስጤም ልዩ ስሟ ልዳ በተባለ ስፍራ ደም ግባቱ ያማረ፣ መልከ መልካም ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስን ወለዱ። በተጨማሪም ማርታና እስያ የሚባሉ ሁለት ሴቶች ልጆችን አፈሩ።
ጊዮርጊስ ማለት ኮከብ ብሩህ፣ ሐረገወይን፣ ፀሐይ ማለት ነው። ቅዱስ ጊዮርጊስ የ10 ዓመት ልጅ ሳለ አባቱ አንስጣስዮስ ዐረፈ። ከዚህ በኋላ በቅዱስ ጊዮርጊስ አባት አንስጣስዮስ ፈንታ በፍልስጤም አውራጃ ሌላ አገረ ገዥ ደግ ክርስቲያን መስፍን ተሾመ። መስፍኑም ከአንድ ሴት ልጅ በቀር ሌላ ልጅ ስላልነበረው ቅዱስ ጊዮርጊስን ወደ ቤቱ ወስዶ እንደ ልጁ አድርጎ በእንክብካቤ ያሳድገው ዘንድ እናቱን ለመናት፤ ቴዎብስታ(አቅሌስያም) ፈቃዷ ሆነ። መስፍኑም እያስተማረ፣ የውትድርና ስልጠናም አሰለጠነው።
ቅዱስ ጊዮርጊስ 20 ዓመት በሆነው ጊዜ የቅዱሳት መጻሕፍትን ትምህርት እና ሌሎችን ጥበብ የሚሰጡ ትምህርቶችን መማር ፈጸመ። ደግሞም ፈረስ ግልቢያን፣ ቀስት መወርወርን፣ አውሬ ማደንን ተማረ። በሥራው ሁሉ ብርቱ ሰው፣ ጀግና ወታደርም ሆነ፤ በጦር ሜዳም መሪ ሆነ፤ በወታደር መካከልም፣ በሀገርም፣ በጀግንነቱና በተወዳጅነቱ የሚወዳደረው ማንም አልነበረም። የእግዚአብሔር ጸጋ አድሮበት ነበርና ከብርታቱና ከጀግንነቱ የተነሣ ያየው ሁሉ እስኪደነግጥ ድረስ ዘወትር በግርማ ላይ ግርማ፣ በኃይል ላይ ኃይል ይጨመርለት ነበር። ጦር ሜዳ ወጥቶ ከጠላቶቹ መሀል ገብቶ እኔ የክርስቶስ ወታደር ጊዮርጊስ መጣሁባችሁ ሲላቸው በፍርሀት ተውጠው፣ ደንግጠውና ተንቀጥቅጠው ይሸሹ ነበር። ጠላቶቹንም ዘወትር ያጠፋቸው እና ይማርካቸው ነበር። በሥራው ሁሉ እግዚአብሔር ይረዳው ነበርና።
ቅዱስ ጊዮርጊስ በዚህ ሁኔታ ላይ እያለ መስፍኑ የ15 ዓመት ልጁን አጋብቶ ሀብት ንብረቱን ለማውረስ አሰበ። ነገር ግን ንጹሕ፣ ድንግል፣ ሰማያዊ ሙሽራ ያደርገው ዘንድ መድኅኒ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ጋብቻ እንዳይፈጽም ለቅዱስ ጊዮርጊስ አመለከተው። መስፍኑም በዚህ አሳብ ላይ ሳለ በእግዚአብሔር ፍቃድ ዐረፈ። ከመስፍኑ ህልፈት በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤሩት ወደምትባል አገር ሄደ። በዚህችም ሀገር ትልቅ መኮንን ነበር። ሀገሪቷም በኢያሪኮ ዳር የተቆረቆረች ነበረች፤ በሮም አንጻር የተሰራ ቅጽር ነበራት፣ ግንቧም እንደ ሊባኖስ ግንብ፣ በሮቿም በባህር በኩል ነበር። ቅጽሯ ብርቱ ነበርና በየብስም ሆነ፣ በመርከብ ለመጣ ጠላት አይደፈርም ነበር። የቤሩት ሰዎች እግዚአብሔርን የማያውቁ አረመኔዎች ሲሆኑ ስሙ ደራጎን የሚባል መንፈሰ ሰይጣን ያደረበት ዘንዶ ያመልኩ ነበር። ደራጎኑም ሲያዩት እጅግ የሚያስፈራ እና እንደ ንስር ሁለት ክንፍ፣ እንደ ፍየል ጢም፣ እንደ አንበሳ ያለ እግርና ጥፍር፣ እንደ ውሻ ጆሮ፣ እንደ ዘንዶ ያለ ጅራት፣ እንደ አዞ ያለ ጥርስ ነበረው።
የቤሩት ሰዎችም ለደራጎኑ ሴቶች ልጆቻቸውን ይገብሩለት ነበር። ከብዙ ዘመን በኋላ የአገሪቱ ሴት ልጆች በአለቁ ጊዜ የአገረ ገዥው ሴት ልጅ ስሟ ቡርክታዊት የምትባል ቤሩታዊት ለደራጎን ምግብ ትሆነው ዘንድ ጫካ ውስጥ አኖሯት። የተመሰገነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ቤሩት ሀገር በደረሰ ጊዜ በጫካ ውስጥ ሲዘዋወር የአገረ ገዥውን ልጅ እያለቀሰች ብቻዋን ተቀምጣ አገኛት፤ ቅዱስ ጊዮርጊስም ከዚህ ምን ትጠብቂያለሽ? አላት። ለደራጎን እንደተሰጠችና ስለ ደራጎን ግብርም አስረድታ ፈጥኖ ከዚያ አካባቢ እንዲሰወር ነገረችው። ኀያሉ ቅዱስ ጊዮርጊስም ሰይጣን ያደረበትን ደራጎን እንደማይፈራውና አማልክትን ሁሉ የሚገዛ፤ ሰማይ እና ምድርን የፈጠረው አምላኬ አለ፤ ከዚህ ከተረገመ አውሬ እርሱ ያድነኛል አላት። ይህን ሲነጋገሩ ደራጎን ምድሪቱን እያናወጠ መጣና ቅዱስ ጊዮርጊስን ሊበላው ወደደ፤ ምላሱን አውለብልቦ መርዘኛ ትንፋሹን ሊረጭበት ፈለገ። ነገር ግን ቅዱስ ጊዮርጊስ የእግዚአብሔርን ኃይል መከታ አድርጎ በሥላሴ ስም በትእምርተ መስቀል ቢያማትብበት የደራጎኑ ጉልበት ራደ፣ ኃይሉ ደከመ። መርዙም ጠፋ።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ለደራጎን ተሰጥታ የነበረችውን የንጉሡን ልጅ ፈትቶ ደራጎኑን አስሮ እሷ እየጎተተች እሱ በፈረስ ሁኖ ከተማ በደረሱ ጊዜ የአገሩ ህዝብ ደራጎኑን ሲያዩ እጅግ በፍርሃትና በድንጋጤ ተዋጡ። ሊያስፈጀን ነው ብለው ይሸሹ ጀመር። ቅዱስ ጊዮርጊስን አምላካችንን ስለምን አመጣህብን አሉት፤ ይህ እራሱንም እንኳ ማዳን ያልተቻለው እንደምን ለእናንተ አምላክ ሊሆን ይችላል? አላቸው። አምላካችንን አንተውም አሉት፤ ካልተዋችሁትስ እንዲጨርሳችሁ ፈትቼ ወደ እናንተ እሰደዋለሁ አላቸው። ይህስ አይሁን ባይሆን ዘንዶውን ልትገድለው ከቻልክ አንተ በምታመልከው አምላክ እናምናለን አሉት። ከከተማ አውጥቶ ዘንዶውን በጦር ወግቶ ገደለው። ህዝቡም ሁሉ ይህን አይተው በእግዚአብሔር ስም አምነው ተጠምቀዋል። ደራጎኑን ከገደለበት ከተማም ሁለት አብያተ ክርስቲያናት ሠርተዋል።
በዚያን ጊዜ በሀገሩ ሁሉ ላይ ሥልጣን ያለው ስሙ ዱድያኖስ የተባለ የፋርስ ንጉሥ ነበር። እጅግ ብርቱ በነገሥታትም ላይ ሥልጣን የነበረው፤ ፈጣሪውን ሳይቀር የካደ እንደ ናቡከደነጾርም ልቡ የደነደነ ነበር። ክርስቲያኖችንና አብያተ ክርስቲያናትን በጽኑ ይቃወም ነበር። ዱድያኖስም ሰባ ነገሥታትን ሰብስቦ ሰባ ጣኦታት አቁሞ ይሰግድ ያሰግድ ነበረ። በዚያን ጊዜ ቅዱስ ጊዮርጊስም ወደ ንጉሥ ዱዲያኖስ ከተማ በመሄድ ከዓላውያን ነገሥታት የሰማዕትነት ተጋድሎውን ጀመረ።
ሰማዕትነት በቤተ ክርስቲያናችን አዲስ እንግዳ ነገር አይደለም። ዛሬም በእምነታቸው ምክንያት በሊብያ ወንድሞቻችን በሰይፍ ተሰይፈው፣ በጥይት ተመተው ሰማዕትነትን ተቀብለዋል፤ እየተቀበሉም ይገኛሉ። ዘመነ ሰማዕታት በቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ መሠረት የስደት ዘመን በመባል ይታወቃል። ሰማዕት የሚለው ቃል በሃይማኖታዊ አስተምሕሮ ስንመለከተው ስለ እግዚአብሔር፣ ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በአጠቃላይ ስለ ሃይማኖታቸው እውነትን በመመስከራቸው፤ ጀርባቸውን ለግርፋት፣ ሰውነታቸውን ለእሳት፣ አንገታቸውን ለስለት አሳልፈው ለሰጡ፤ በድንጋይ ተወግረው፣ በመንኮራኩር ተፈጭተው፣ በጦር ተወግተው፣ በግዞትና በስደት በዱር በገደል ተንከራትተው ለዐረፉ ቅዱሳን አባቶችና ቅዱሳት እናቶች የሚሰጥ ተጋድሏቸውን የሚገልጽ ቃል ነው። ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ስለሰማዕታት መራራ ተጋድሎ በሐሙስ ውዳሴ ማርያም “ሰማዕታት የዚህችን ዓለም ጣዕም በእውነት ናቁ፣ ደማቸውንም ስለ እግዚአብሔር አፈሰሱ፣ ስለ መንግሥተ ሰማያትም መራራ ሞትን ታገሱ” በማለት ገልጿል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ የአባቱን ምስፍና ተቀብዬ ልምጣ ብሎ እጅ መንሻ ይዞ ብላቴኖቹን አስከትሎ ቢሄድ ሃይማኖታችሁን ካዱ ለጣኦት ስገዱ ብሎ አዋጅ አውጆ ሕዝቡም ለጣኦት ሲሰግዱ አገኘ። እሱም ለአምልኮተ እግዚአብሔር ቀናዒ ነውና አዘነ። ያመጣውን እጅ መንሻ ለነድያን መጽውቶና ብላቴኖቹን አሰናብቶ ነገሥታቱ ከተሰበሰቡበት ቦታ ሂዶ “እኔ በኢየሱስ ክርስቶስ የማምን ክርስቲያን ነኝ” በማለት ስለ እግዚአብሔር በንጉሥ ዱድያኖስ ፊት መሰከረ። ዱድያኖስም የቅዱስ ጊዮርጊስን ማንነት ከተረዳ በኋላ በ10 አህጉር ላይ እሾምሃለሁ እኔ የማመልከውን አጵሎንን አምልክ አለው። ቅዱስ ጊዮርጊስም እኔ የማመልከው ሰማይና ምድርን የፈጠረውን፣ ሁሉን ማድረግ የሚችለውን የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔርን ነውና ሹመት ሽልማት አልፈልግም ሃይማኖቴን አልክድም በማለት በሃይማኖቱ እንደማይደራደር አስረግጦ ነገረው።
በአረመኔያዊ ንጉሥ ዱዲያኖስ ተበሳጭቶና ተቆጥቶ በቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ መከራ፣ስቃይና እንግልት አጸናበት፤በእንጨት አሰቅሎ ሥጋውን በመቃጥን አስተፈተፈው። ረጃጅም ችንካሮች ያሉበት የብረት ጫማ አጫምቶ እንዲጓዝ አደረገው። ደሙ ፈሰሰ፣ ሥጋው ተበጣጠሰ፣ አጥንቱ ደቀቀ። መጓዝ ተሳነው። እግዚአብሔር ቅዱሳንን የሚያጸና አምላክ ቅዱስ ጊዮርጊስን መከራውን ተቋቁሞ ተጋድሎውን እንዲቀጥል አደረገው። እንደገናም ዱዲያኖስ በሰባ ችንካር አስቸንክሮ፣ በእሳት አስተኩሶ፣ አናቱን በመዶሻ አስቀጥቅጦ በሆዱ ላይ የደንጊያ ምሰሶ አሳስሮ እንዲያንከባልሉት አደረገ። ቅዱስ ጊዮርጊስ የማይሞት ቢሆን ሥጋውን በመጋዝ አስተልትሎ ጨው ነሰነሰበት ሥጋው ተቆራርጦ ወደቀ። በዝግ ቤት ትተውት ሄዱ። እግዚአብሔር በእጁ ዳሶ አስነስቶ ገና ስድስት ዓመት ስለ ስሜ ትጋደላለህ ሦስት ጊዜ ትሞታለህ፤ በአራተኛው ታርፋለህ ብሎ በመከራው ጸንቶ የድል አክሊልን እንደሚቀዳጅ ቃል ገባለት።
ቅዱስ ጊዮርጊስም ሲነጋ ሄዶ ዱዲያኖስን አንተ ከሀዲ እፈር አምላኬ መድኃኒቴ ኢየሱስ ክርስቶስ አዳነኝ አለው። ዱዲያኖስም በጠንቋዩ አትናስዮስ አማካሪነት ለቅዱስ ጊዮርጊስ አንጀት ቆራርጦ የሚጥል መርዝ አስማተ ሰይጣን ደግሞ ቢሰጠው ስመ እግዚአብሔር ጠርቶ በጠጣው ጊዜ እንደ ጨረቃ ደምቆ፣ እንደ አበባ አሸብርቆ ተገኝቷል። ጠንቋዩም አምኖ ተጠምቆ ሰማዕትነትን ተቀብሎ ዐርፏል።
ቅዱስ ጊዮርጊስን መርዙ አልገድለው ቢል በመንኮራኩር አስፈጭቶ ከጥልቅ ጉድጓድ ጥሎት ደንጊያ አትሞበት ተመለሰ። ጌታ የተፈጨ ሥጋውን በእጁ ዳሶ መንፈሱን መልሶ አንስቶታል። ተነስቶም አህዛብን እያስተማረ፣ ከአረመኔው ንጉሥ ቀርቦ አምላኬ ከሞት አነሳኝ አለው። እንደገናም ተበሳጭቶ በብረት አልጋ አስቸንክሮ ከበታቹ እሳት አንድዶበታል። እሳቱም ደሙ ቢነጥብበት ጠፍቷል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ የኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት ይገለጥ ዘንድ ሙታንን አስነስቶ፣ የደረቁ ዕጽዋትን አለምልሞ፣ ብዙ ተአምራትን ቢያሳየው ንጉሥ ዱድያኖስ የሚያደርገው ግራ ገባው። በመንኮራኩር ፈጭታችሁ ከተራራ ላይ ወስዳችሁ ንዙት አለ። እንደታዘዙትም አደረጉ። ሥጋው ያረፈበት ሣር፣ ቅጠሉ፣ ደንጊያውና እንጨቱ ሁሉ ጊዮርጊስ ቅዱሱ ለእግዚአብሔር፤ ጊዮርጊስ ሰማዕቱ ለእግዚአብሔር እያሉ አመስግነዋል። እግዚአብሔርም ቃሉ ህያው ነውና ሦስተኛ ከሞት አንስቶታል። መከራ እና ስቃይ ያጸኑበት ጭፍሮችም የቅዱስ ጊዮርጊስን መነሳት አይተው ደንግጠውና ፈርተው ከእግሩ ስር ወደቁ። አምነውም ተጠመቁ።
ቅዱስ ጊዮርጊስም ተጋድሎውን በመቀጠል ንጉሡ ለጣዖቱ አጵሎን እንዲሰግድ ብሎ ወደ እልፍኙ ቢያስገባው ንግሥቲቱን እለስክንድርያን አስተምሮ አሳመናት። አጵሎንን በአደባባይ አዋርዶ አምላክ እንዳልሆነ ተናግሮ ምድር እንድትውጠው አድርጓል። ንግሥቲቱም የጊዮርጊስን ኃያልነት፣ የእግዚአብሔርን አምላክነት በአደባባይ መስክራ በሰማዕትነት ዐርፋለች። በዚህም የተነሣ ትምህርቱን ሰምተው፣ ተአምራቱን አይተው ብዙዎች አምነው ተጠምቀዋል። ሰማዕትነትንም ተቀብለዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስም ዓላውያን ነገሥታት ወደ እግዚአብሔር እንዳልተመለሱ ስለተገነዘበ ወደ እግዚአብሔር አመልክቶ በእሳት እንዲጠፉ አድርጓቸዋል።
በእምነታቸው ምክንያት ስደት፣ እስራት፣ ግዞት፣ ስድብ፣ ነቀፌታ ሲደርስባቸው መከራውና ስቃዩን፣ እንግልቱንና እስራቱን፣ ስደቱን በአኮቴት የሚቀበሉ ምእመናንን ጸዋትወ መከራ ለመግለጽ ቤተ ክርስቲያን እንደዚህ ያሉትን አማኞችን ሰማዕት ዘእንበለ ደም ትላቸዋለች። ምክንያቱም የእነዚህ መከራ አቀባበል በሰይፍ መሰየፍ፣ በእሳት መጣል ሳይሆን ከላይ የተገለጹትን ስለ እግዚአብሔር ብለው በትዕግሥት የሚቀበሉ ስለሆኑ ነው። በዚህም ተጋድሏቸው ስዎችንና ልዩ ልዩ ስቃያት የሚያደርሱባቸውን ኢአማንያን ጭምር ወደ ክርስትና እየጠሩ ለሰማዕትነት የሚያበቁ በመሆናቸው ነው።
ቅዱስ ጊዮርጊስም ገድሌን የጻፈ ያጻፈ፣ መታሰቢያዬን ያደረገ፣ በስሜ ቤተ ክርስቲያን ያነጸ፣ በመከራ ሁኖ በስሜ የተማጸነ ሁሉ በሥጋው ረድኤትን በነፍሱ ምህረትን የሚያገኝ ይሁን ብሎ እግዚአብሔርን በለመነው ጊዜ ምድር ተናወጸች፣ ሰማያት ተከፈቱ ጌታ መላእክቱን፣ ነብያትን፣ ሓዋርያትን አስከትሎ ሰላም ላንተ ይሁን ወዳጄ ጊዮርጊስ ሆይ የለመንከው ሁሉ ይሁንልህ ይደረግልህ ብሎ ከማኅበረ ሰማዕት መካከልም የሚመስልህ የሚስተካከልህ የለም ብሎ ቃል ኪዳን ገባለት። ቅዱስ ጊዮርጊስ ስለ ቤተ ክርስቲያን ፍቅር ሲል በሰይፍ ተቀልቶ፣ በመንኮራኩር ተፈጭቶ ወደ እቶን እሳት ተጥሎ ለአምዕሮ በሚከብድ መልኩ ብዙ ጸዋትወ መከራን ተቀብሎ በ27 ዓመቱ ሚያዚያ 23 ቀን ሰማዕትነትን ተቀብሏል።
እግዚአብሔርም ሰማዕታትን በደም፣ ቅዱሳንን በተጋድሎ ያጸና አምላክ ስለ ሰባት ዓመት ተጋድሎው ለቅዱስ ጊዮርጊስ ሰባት የክብር አክሊላት አቀዳጅቶታል። “በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው፤ ከተፈተነ በኋላ ለሚወዱት ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን የሕይወትን አክሊል ይቀበላል እንዳለው ቅዱስ ያዕቆብ። ቅዱስ ዮሐንስም በራእዩ ልትቀበለው ያለህን መከራ አትፍራ። እነሆ፥ እንድትፈተኑ ዲያብሎስ ከእናንተ አንዳንዶቻችሁን በወኅኒ ሊያገባችሁ አለው፥ አሥር ቀንም መከራን ትቀበላላችሁ። እስከሞት ድረስ የታመንህ ሁን የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ” እንዲል ቅዱስ ጊዮርጊስ የሕይወት አክሊልን ተቀዳጀ። (ያዕ 1፥12 ፣ ራእ 2፥10)
በአጠቃላይ እኛም ክርስቲያንኖች የቅዱሳን ወዳጆች፣ የሰማዕታት ልጆች ነንና በሃይማኖታችን ጸንተን በእምነታችን ምክንያት የሚመጣብንን ማንኛውንም መከራና ፈተና ተቋቁመን እስከመጨረሻው በሃይማኖት፣ በምግባር፣ በትሩፋትና በንስሃ እየተመላለስን መድኅኒ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ብሎ በመስቀል ላይ የቆረሰውን ቅዱስ ሥጋ እና ያፈሰሰውን ክቡር ደም ተቀብለን የስሙ ቀዳሽ የክብሩ ወራሽ እንሆን ዘንድ አምላከ ቅዱስ ጊዮርጊስ በረድኤቱ እንዲጎበኘን እንለምነው፥ እንማጸነው። የቅዱሳንን፣ የሰማዕታትን፣ የነቢያትን፣ የሐዋርያትን በዓልና ዝክር ስንዘክር ተጋድሏቸውን እያሰብን መትጋት ይኖርብናል።
ከሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ረድኤት፣ በረከት ያካፍለን፤ አማላጅነቱ አይለየን፡ አሜን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
ምንጭ:
ገድለ ጊዮርጊስ
መዝገበ ታሪክ
ሐመረ ተዋሕዶ ልዩ እትም 2002 ዓም.
No comments:
Post a Comment