Saturday, 12 February 2022

የ"ቶ" ፊደል ምስጢር እና ታሪክ

የ "ቶ" ፊደል የተፈጠረዉ አለም ሲፈጠር ነዉ። የሰዉ ልጅ የተፈጠረዉ በ"ቶ" ቀመር መሆኑ አጀብ ያስብላል። በግዕዝ የፊደል ስርአት መሰረት (ተ ቱ ቲ ታ ቴ ት ቶ) "ቶ" ሰባተኛዋ ፊደል ነች። ሰባት ቁጥር ብዙ ትርጉምና ምስጢር አለው፡፡ ሰባት ቁጥር በቤተክርስትያን ፍፁምነትን ይወክላል።

ለምሳሌ:-

📌7ኛው ዙፋን የጌታ እንደሆነ ፣

📌7ኛው ቀን ሰንበት እንደሆነች ፣

📌7ቱ ሰማያት

📌7ቱ ምስጢራተ ቤተክርስትያን

📌7ቱ የመላእክት አለቆች 

ከ"ተ" የፊደል ዘር "ቶ"ን ስንመለከት መልክአ ፊደሉ ሰው መሳይ ሲሆን ትርጓሜው ደግሞ አምላክ ሰው መሆኑን እናምናለን ማለት ነው። 7ቱ ባህርያትን መዋሐዱን ያመለክታል። የሰዉ ልጅ የተፈጠረዉ በ"ቶ" ቀመር መሆኑም አጀብ ያስብላል። 

የ"ቶ" ሰማያዊ ታሪክ:

ከመላእክቱ  ጋር እነሆ በሰማይ  ጦርነት ሆነ ... በሰማይ ሰልፍ ሆኖ ቅዱስ ሚካኤልና መላእክቱ ከሳጥናኤል ጋር ሲዋጉ ሁለት ጊዜ ተሸንፈዋል ለሶስተኛ ጊዜ ሊዋጉ ሲሄዱ ግን ቀስተደመናን ቀርፆ የ'ቶ" ቅርፅ ያለው መስቀል በየክንፋቸው ላይ ቀርፆላቸዋል 'ኤል' የሚለውንም ሚስጢራዊ ስም አትሞባቸዋል፡፡ ይህን ካደረገላቸው በኋላ ተመልሰው ወደ ውጊያው ቢሄዱ ሳጥናኤል ሀይላቸውን ሊቋቋመው አልቻለም ውድቀቱ ፈጠነ ሽንፈቱ የከፋ ሆነበት ፅልመትን አልብሰው ወደ በርባኖስ ውስጥ ጥልቅ ጨለማ ላይ

ወረወሩት። የአምላክ ክንድ ፅኑ መሆኗን ሳጥናኤል ያውቃልና በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስላሴን ስሉስ ቅዱስ እያለ እየተንቀጠቀጠ ይገዛል ይላል። ሆኖም ምግባር ስለሌለው ፅድቅን አያያትም። 

የቶ ሚስጥር በኢትዮጵያ:

ስንመለስ ቶ በእግዚአብሄር የጥበብ ገላጭነት ለኢትዮጵያዊው የሳሌም ንጉሥ መልከጼዴቅ(ጌራ) ተገለፀች፡፡ እርሱም ለኢትኤል ልጅ ኦቢዮር (ቢኦር) ጥበቡን አስተላለፈ፡፡ የኦቢዮር የንግሥና ምልክትም ናት፡፡  "ቶ" የህይወት ምልክት አድርገዉ የሚወስዱት ለኢትዮጵያዉያን ብቻ ነዉ።

የ'ቶ' ምስጢር በግብፅ:

የሚገርመዉ ደግሞ ይህ ምልክት አገልግሎት ላይ የዋለዉ ከክርስቶስ ልደት በፊት 3000 አመታት ቀደም ብሎ ጥንት ግብፃውያን ቶርኔተር (የፑንት ምድር) ብለዉ በሚጠሯት ሀገር ነዉ፡፡

ግብፃዉያን እንደሚሉት የፒራሚድ ግንባታ ጥበብን የተማሩት ከቶርኔተር (የአሁኗ ኢትዮጵያ) ሰዎች ነው። በ670 አ.አ በኢትዮጵያ ነግሶ የነበረዉ ንጉስ ቲርሀቅ እየሩሳሌም የኦሶር ንጉስ በሆነዉ በሰናክሬም ስትወረር ለእየሩሳሌም መከታ ሆኖ ሲዘምት ሀያላን ከሚባሉ ወታደሮች ጋሻ ላይ የ"ቶ" ምልክት እንደተቀረፀና ንጉሱም በ"ቶ" ቅርፅ የተሰራ መስቀል ማሰሩን የሚያስረዱ የድንጋይ ላይ ፅሁፎች ተገኝተዋል። 


የ"ተ" ፊደል ዘር ጠልሰማዊ ፍቾች 

ጠልሰም ማለት አምሳል ውክልና ማለት ሲሆን ስጋና ነፍስ የማያውቁት መንፈስ ግን የሚያውቀው የተለየ ሀይል፣ ጥበብ እና ምስጢር ያለው  ማለት ነው። 

"ተ" ማለት ምዕራብ ምስራቅ ሰሜን ደቡብ ቅርፀ አዳም ማዕከላዊ መስቀል በሁሉ ላይ የተሾመ ማለትነው።

"ቱ" ማለት አዳም ብቻውን እንዳይሆን ከግራ ጎኑ ሰው እንፍጠርለት ማለትን ያመለክታል።  ከአንድ ሁለት መሆንን ያሳያል።

"ቲ" ማለት ዲያቢሎስ በቀኝ የነበረውን አዳም በግራ ሊያደርገው መንቀሳቀሱን ማለትም የሄዋንን መሳሳት የሚጠቁም ነው።

"ታ" ማለትየአዳም እናየሄዋን በሰሩት ሃጢያት መፀፀትና ወደ ፈጣሪያቸው መመልከታቸውን ከግራ ወደቀኝ እንዲመልሳቸው መማፀናቸውን ያሳያል።

"ቴ" ጠልሰም እጅግ ትልቅ ሚስጥርን የያዘ ነው። ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን በሲኦል በዳቢሎስ ቀንበር ሲማቅቅ የነበረን ነፍስ ሁሉ ለማዳን "ቴ" ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሲኦል መውረዱን የሚያመላክት ነው። ይህ "ቴ" በተዓምረ ኡራኤል ላይ የሚነበብ ነው። ይህጠልሰም ጌታችንለአዳም የገባለትን ከ5500ዘመን በኃላ የሚፈፀመውን ከላይ የተገለፀውን የምህረት ስራ ከርቀት የሚያሳይ ነው።

"ት" ማለት ትህትና ነው። ጌታችን አዳምን ሁሉ ሊያድነው በቀራንዮ መሰቀሉን ያመለክታል። ትዕግስትም ነው። እንዲሁም በ"ታ" የተጸጸተው አዳም ከታች ወደ ላይ መነሳቱን እና በ"ቴ" መዳኑን ያሳያል።

"ቶ" ማለት ክርስቶስ ተነስቷል በአባቱም ቀኝ ተቀምጧል። አዳም ዳግም ወደ ክብሩ ተመልሷል። በስሙ ለሚያምኑት ለተጠሩት ልጅነትን ከኃይል ጋር ሰጣቸው። የሰማይናንና የምድርንም መክፈቻ ቁልፍ ሰጣቸው። በማለት አባቶች ያመሰጥሩታል። ይህንን ፊደል ግብጾች አንቅህ ሲሉትግዕዙ አንቅህ ህይወት ይለዋል። በእንግሊዘኛውም <Ankh> ብላችሁ ጎግል ላይ በመፈለግ ምስሎችን ማግኘት ትችላላችሁ። የ"ቶ" ጠልሠምነት (አምሳል መልክ ማለት ሲሆን ስጋና ነፍስ የማያውቁት ጥበብ ነው)ነው፡፡

No comments: