Thursday, 6 January 2022

ልደተ ክርስቶስ


 ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለት ልደታት አሉት

ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለት ልደታት እንዳሉት ታምናለች ታሳምናለች፤ እነዚሁ ቀዳማዊ ልደትና ደኃራዊ ልደት ሲባሉ፤ ይኸውም ወልድ (ቃል) ቅድመ ዓለም ከአብ ያለ እናት ድኅረ ዓለም ከእመቤታችን ያለ አባት የተወለደው ልደት ነው፡፡ “ለእግዚአብሔር ልጅ ሁለት ልደታት እንዳሉት ልናምን ይገባናል፡፡ መጀመሪያ ከዘመን ሁሉ በፊት ከእግዚአብሔር አብ መወለዱ ነው፡፡ ዳግመኛም በኋላኛው ዘመን ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው መወለዱ ነው፡፡” ሲል ሊቁ አስረድቷል፡፡ (ሃይማኖተ አበው ባስልዮስ ዘቂሳርያ)

ቀዳማዊ ልደት
      ቀዳማዊ ልደት የምንለው ዓለም ከመፈጠሩ ዘመን ከመቈጠሩ በፊት እግዚአብሔር ወልድ ከእግዚአብሔር አብ የሰው ሕሊና በማይመረምረው ምሥጢር የተወለደው ልደት ነው፡፡ ልደቱም እንደ ሰው ልደት ሳይሆን፤ ከአብ ሲወለድ አብን አህሎ፥ አብን መስሎ፥ ማለት አካሉ አካሉን አህሎ፤ ባሕሪው ባሕርይውን መስሎ ባለማነው፣ ባለመብለጥ፣ ባለመለየት ባለመለወጥ ነው፡፡
      ዓለም ከመፈጠሩ በፊት ወልድ ከአብ መወለዱን መጻሕፍት ያስረዱናል፡፡ “አንተ ልጄ ነህ እኔ ዛሬ ወለድሁህ” (መዝ. 27) “ ከአጥቢያ ኮከብ አስቀድሞ ከሆድ ወለድሁህ” (መዝ. ፻93) ከአጥቢያ ኮከብ አስቀድሞ የሚለው ቃል ዓለም ከመፈጠሩ በፊት ወልድ ከአብ መወለዱን ያስረዳናል፡፡ ዓለም ከመፈጠሩ በፊት ሌላ የተወለደ የለምና ለሌላ ሊሰጥ አይችልም፡፡ በተጨማሪም “ተራሮች ገና ሳይመሠረቱ ከኮረብቶች በፊት እኔ ተወለድኩ” (ምሳ. 8፥፳5) በማለት የወልድን ቀዳማዊ ልደት መጽሐፍ ያስረዳል፡፡
      “ተራሮች ገና ሳይመሠረቱ ከኮረብቶችም በፊት እኔ ተወለድኩ” ያለው ስለራሱ ሳይሆን፤ እግዚአብሔር ወልድ የተናገረው መናገር ነው፡፡ ከዳዊት የተወለደው ዓለም ከተፈጠረ ተራሮች ከተመሠረቱ ከብዙ ሺህ ዓመታት በኋላ ነው፡፡ የወልድ ከአብ መወለድ እንዴት እንደሆነ እግዚአብሔር ለአባቶቻችን ገልጾላቸው ከአስተማሩን በላይ ልናውቅ አንችልም፡፡ ነገር ግን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እግዚአብሔር በፍጥረቱ ይታወቃል ብሎ ሮሜ. 1፥፳ እንደተናገረውና አባቶቻችንም በሥነ ፍጥረት ምሳሌ መስለው እንዳስተማሩን በፍጥረቱ እንረዳዋለን፡፡
      ከፍጥረቱም እንኳን መርምረን የማንደርስባቸው አሉና መርምረን የማንደርስባቸው ፍጥረታት ካሉ እነዚህን የፈጠረ እግዚአብሔር ተመርምሮ የማይደረስበት መሆኑን በፍጥረቱ ተምረናል፡፡ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ገባሬ መንክራት ስለ ቀዳማዊ ልደቱ በተናገረበት አንቀጽ የወልድ ከአብ መወለድ የማይመረመር መሆኑን እንዲህ ብሎ ያስረዳናል፡፡
      “የወልድ ከአብ መወለድ የማይመረመር ሊናገሩትም የማይቻል ነው፡፡ የማይመረመር ረቂቅ ስለሆነ. . .” ካለ በኋላ በሥነ ፍጥረት ሲያስረዳ ደግሞ “ከልብ የኅሊና መገኘት እንደምን ነው?. . .ከአንደበት የቃል መገኘትስ ምን ይመስላል? በእኛ ባሕርይ ያሉ እነዚህን ማወቅ ካልተቻለን ሕሊና የማይመረምሩት ያልተፈጠረ የፈጣሪን ምሥጢር እንደምን እናውቃለን” (ሃይማኖተ አበው ምዕ. 03 ኢሳ. ፵503 ሮሜ. 01፥፴3-5)
      እንግዲህ የወልድ ከአብ መወለድ የቃል ከአንደበት እንደመገኘት መሆኑን በሥነ ፍጥረት ምሳሌነት ብናውቀውም ሊቁ እንዳስረዳን ሕሊና (ሐሳብ) ከልብ፤ ቃል ከአንደበት መገኘታቸውን ነው እንጂ እንዴት እንደሚገኙ መርምረን ማወቅ እንደማንችል የወልድ ቀዳማዊ ልደቱንም መወለዱን እንጂ፥ እንዴት ተወለደ ብለን መርምረን ልናውቅና ልንረዳው አንችልም አባቶቻችንም ከገለጸላቸው በላይ አልተመራመሩም፡፡

ደኃራዊ ልደት


ደኃራዊ ልደት ዓለም ከተፈጠረ  5ሺህ 5 መቶ ዓመት ሲፈጸም እግዚአብሔር ወልድ ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው መወለድ ሁለተኛ ልደት ነው፡፡ “ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሐር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ” (ገላ. 44) ይህንንም ከመወለዱ በፊት አስቀድሞ በነቢያት አናግሮታል፡፡
      ጌታ ከመወለዱ ከ6፻፹8 ዓመታት በፊት የነበረው ነቢዩ ኢሳይያስ ግልጽ አድርጎ ሲናገር “ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች” (ኢሳ. 704) ይህን ደኃራዊ ልደቱ፥ ቀዳማዊ ልደቱን እንድናውቅ ያደረገን፤ በእመቤታችን አማካኝነት የተዛመደን ድንቅ ልደት ነው፡፡
      የሰውን ሥጋ ነሠ ስንልም ከወንድ ዘር ተከፍሎ አይደለም፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ እንዳለው በድንግልና ፀነሰችው እንጂ በቀደመ ልደቱ ያለ እናት ከአብ እንደተወለደ፤ በኋላም ጊዜ ከእመቤታችን ያለ አባት ተወለደ፡፡ ከእመቤታችን ያለ አባት መወለዱ ከአብ ያለ እናት መወለዱን ያስረዳል፡፡ “ልደት ቀዳማዊ ተዓውቀ በደኃራዊ ልደት” እንዲል ሃይማኖተ አበው፡፡
      የጌታችን ከእመቤታችን በድንግልናመወለድ የድኅነት ምልክት መሆኑም ነቢዩ ኢሳይያስ አስቀድሞ ተናግሯል፡፡ “ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች” የተባለውን የድኅነት ምልክት በጊዜው መፈጸሙን መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ለእረኞች “ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋል ይህም ምልክት ይሆናችኋል፡፡ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግም ተኝቶ ታገኛላችሁ፡፡” ሲል አስረድቷል፡፡ (ሉቃ.201-02)
      በዳዊት ከተማ በቤተልሔም እንደሚወለድም ቅዱስ ገብርኤል ከመናገሩ በፊት ነቢዩ ሚክያስ “አንቺ ቤተልሔም፥ የይሁዳ ምድር፥ ከይሁዳ ገዢዎች ከቶ አታንሺም፤ ሕዝቤን እስራኤልን የሚጠብቅ መስፍን ካንቺ ይወጣልና፡፡” (ሚክ. 52) ብሎ ተናግሯል፡፡ የጌታ መወለድንም ሆነ ሌላውንም የማዳን ሥራውን በትንቢት አስቀድሞ የመናገራቸው ምሥጢር በሥጋዊ ጥበብ ሊመረመር የማይቻል ነው፡፡ ምድራውያን ጠበብት እያለ የተሰወረውን ግን ተመራምረው ቢደርሱበት እን ረቂቁን ምሥጢር አይደርሱበትም፥ ነቢያት ግን መንፈስ ቅዱስ በገለጠላቸው ጥበብ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ሆኖ የማያውቀውን ወደፊትም ሊሆን የማይችለውን እንደሚሆን እንደሚደረግ አስቀድመው ተናግረዋል፡፡ ለምሳሌ ያህል ብናነጻጽር የዘመኑ ጠበብቶች ብዙ የሚያስደንቅ ምርምር ተመራምረዋል፡፡ ብዙ አለ ተብሎ ያልታሰበ ነገር አግኝተዋል፡፡ ያገኙት ነገር ሁሉ ግን ያና የተሠወረ እንጂ እግዚአብሔር ያልፈጠረውን አይደለም፡፡ ለምር,ምር የሚጠቀሙበት መሣሪያም ቁስ ነገር ነው፤ የሚያገኙትም ግኝት ቁስ አካል ነው፡፡ ነቢያት ግን በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ መመርመሪያ መሣርያነት የሚገኙት ግኝት መንፈሳዊ ግኝት ነው፡፡
      ቴሌስኮፕ የተባለው መሣሪያ ቁስ፤ የራቀውን፣ የተሠወረውን አቅርቦ አጕልቶ ያሳያል፡፡ ነገር ግን እርሱም ቁስ አካል ነው፤ በእርሱም የተገኘውም ነገር አስቀድሞ እግዚአብሔር የፈጠረው ለሰው ተሠውሮ የቀረ ቁስ አካል ነው እንጂ ያልነገረ አይደለም፡፡ ለዚህ ንጽጽር የኢሳይያስን ትንቢት ብንመለከት ጌታ ከመወለዱ 6) ዓመት በፊት ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ሆኖ የማያውቀውን፣ ወደፊትም የማይሆነውን ድንግል በድንግልና ፀንሳ እንደምትወልድ በመንፈስ ቅዱስ ቴሌስኮፕነት አይቶ ተናገረ፡፡ ሴት ያለ ወንድ ዘር መፅነስ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ሆኖ አያውቅም፡፡ ኢሳይያስ ግን ሆኖ ባያውቅም እንደሚሆን በእርግጠኝነት ተናገረ፡፡ ይህ ቃል መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ተልኮ በመጣበት ጊዜ ባያረጋግጥልን ኖሮ ለማመን ምንኛ ከባድ ነው? “መልአኩ ገብርኤል ናዝሬት ወደምትባል ወደ ገሊላ ከተማ ከዳዊት ወገን ለሆነው ለሚባል ሰው ወደ ታጨች ወደ አንዲት ድነግል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ፡፡ መልአኩም ወደ እርሷ ገብቶ. . . ማርያም ሆይ በእግዚአብሔር ዘንድ ጸጋ አግኝተሻልና አትፍሪ፡፡ እነሆም ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ” አላት፡፡ (ሉቃ. 1፥፳6)
      ነቢያት ስለክርስቶስ የተናገሩት ሁሉ ተፈጽሟል፤ ባይፈጸም ኖሮ ነቢያት ባልተባሉ ነበር፡፡ የተናገሩት በአንድ መንፈስ ቅዱስ ስለሆነ ያልተፈጸመ ነገር የለም፡፡ ስለዚህ ነው ቅዱስ ኤፍሬም “ኦ ዝ ነገር ለእሉ እለ ተነበረዩ ዘበአሐዱ መንፈስ በእንተ ክርስቶስ… በአንድ በመንፈስ ቅዱስ ስለ ክርስቶስ የተናገሩ የነቢያት ነገር ምን ይደንቅ!” ብሎ የተናገረው ስለ ጌታችን መወለድ ቅዱስ ዳዊትም “እነሆ በኤፍራታ ሰማነው በዱር ውስጥም አገኘነው” ብሎ ተናግሯል፡፡ (መዝ. )16)
      የበዓላት ራስ ስለሆ ስለከበረ ልደት በዓል የከበረ ወንጌል እንዲህ አለ፡፡
      በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን ዕጣ በቤተልሔም ጌታ ኢየሱስ በተወለደ ጊዜ እነሆ ሰብአ ሰገል ከምሥራቅ መጥተው ወደ ኢየሩሳሌም ደረሱ ኮከቡም በምሥራቅ አይተን እንሰግድለት ዘንድ መጥተናልና የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? እያሉ፡፡
      እኚህ ሰብአ ሰገል ከዋክብት የሚያጠኑ ፈላስፎች ነበሩ፡፡ ይቅር ባይ እግዚአብሔር በረቂቅ ጥበቡ በሚያምኑት መንገድ ሳባቸው፤ እነርሱ ከዋክብትን ይመረምሩ ነበርና፡፡ ይህንንም የተለየ ኮከብ ገለጠላቸው፤ ባዩትም ጊዜ ደስ አላቸው፡፡ መልኩ በብዙ ዓይነት ልውጥ ነውና፡፡ ሕፃን የታቀፈች ድንግል ብላቴናን ይመስላል እርሱም በቀን ይጓዛል፤ በሌሊትም ይሠወርና ሲቆሙ በሌላ አንጻር ይገለጥላቸዋል፡፡
      እነርሱም ወደ ኢየሩሳሌም ሲደርሱ ያ ኮከብ ተሰወራቸው፡፡ እጅግ አዘኑ የሚያደርጉትንም አላወቁም፡፡ ከዚህም በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ ገብተው ስለተወለደው ንጉሥ ጠየቁ፡፡ የእሊህም ሰዎች ቁጥራቸው ሺህ ነው፡፡ ለእያንዳንዱም ንጉሥ ዐሥር ዐሥር ሺህ ሠራዊት አለው፡፡ ንጉሡ ሄሮድስም በሰማ ጊዜ ደነገጠ፤ ኢየሩሳሌምም በመላዋ ከእርሱ ጋር ደነገጠች፡፡ የካህናት አለቆችና የሕዝቡን ጸሐፊዎች ሁሉ ሰብስቦ ክርስቶስ በየት ይወለዳል ብሎ ጠየቃቸው በይሁዳ በቤተልሔም ነው አሉት፡፡ በነቢዩ እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፡፡
      የኤፍራታ እጻ ቤተልሔም አንቺ ከይሁዳ ነገሥታት አታንሺም ወገኖቼ እስራኤልን የሚጠብቅ ንጉሥ ካንቺ ይወለዳልና፡፡ ከዚህም በኋላ ሄሮሰድስ ሰብዓሰገልን ጠርቶ ኮከቡ የታየበትን ዘመን ከእነርሱ ተረዳ፡፡ ሄዳችሁ የዚያን ሕፃን ነገር እርግጡን መርምሩ ያገኛችሁትም እንደሆነ እኔም መጥቼ እሰግድለት ዘንድ በእኔ በኩል ተመልሳችሁ ንገሩኝ ብሎ ወደ ቤተልሔም ሰደዳቸው የነገራቸውንም ሰምተው ከንጉሡ ሄዱ እነሆ ምስራቅ ያዩት ኮከብ ወደ ቤተልሔም እስከሚያደርሳቸው ይመራቸው ነበር ሕፃኑ ካለበት ዋሻ ላይ ደርሶ ቆመ፡፡

      ኮከቡንም ባየ ጊዜ እጅግ ደስ አላቸው፡፡ ወደ ቤትም በገቡ ጊዜ ሕፃኑን ከእናቱ ከድንግል ማርያም ጋር አገኙት ወድቀውም ሰገዱለት፡፡ ሣጥናቸውም ከፍተው ወርቅ፣እጣን፣ ከርቤ እጅ መንሻ አቀረቡለት፡፡
      በእግዚአብሔር ፈቃድ ዮሴፍ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሕፃን ጌታ ኢየሱስ በዚያች ዕለት ወደ ቤተልሔም መጡ ስለዚህም ሰብዓሰገል አገኟቸው የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስተስ ያለ ናዝሬት በሌላ ቦታ አላደግገምና ከተወለደም እድሜው ሁለት ዓመት ሆኖት ነበር ሆኖት ነበር፡፡  
      አምላክ ነውና ስለ መንግስቱ ወርቅን ገበሩለት፣ ማኅየዊ ለሆነ ሞቱ ምልክትም ከርቤን ገበሩለት፡፡ ወደ ሄሮድስም እንዳይመለሱ መልአክ በሕልም ነገሯቸው፤ በሌላ መንገድም ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ገቡ፡፡ አምላክ በሥጋ ስለመገለጡ አዋጅ ገጋሪዎችና ሰባኪዎች ሰባኪዎች ሆኑ፡፡
      ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ነቢዩ ሕዝቅኤል እንዲህ ብሎ ትንቢት ተናገረ፡፡ “እግዚአብሔርም፡- ይህ በር ተዘግቶ ይኖራ እንጂ አይከፈትም ሰውም አይገባበትም፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶበታል ተዘግቶ ይኖራል” አለ፡፡(ሕዝ. ፵9 1-9)
      ነቢዩ ዳንኤልም አለ “ሌሊት በራዕይ አየሁ፤ እነሆም የሰው ልጅ የሚመስል ከሰማይ ደመናት ጋር መጣ በዘመናት ወደ ሸመገለውም ደረሰ፤ ወደ ፊቱም አቀረቡት ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ሁሉ ይገዙለት ዘንድ ግዛትና ክብር መንግሥትም ተሰጠው፤ ግዛቱም የማያልፍ የዘላለም ግዛት ነው፥ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው፡፡” (ዳን.703 -09)
     ኢሳይያስ “ከእሴይ ሥር በትር ትወጣለች አባባም ከግንዱ ይወጣል አለ፡፡” ኢሳ. 011
     ዳግመመኛም “ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነቱም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል አለ፡፡”  (ኢሳ. 96)
      ዳዊት በመዝሙ እንዲህ አለ “እግዚአግሔር አንተ ልጄ ነህ ዛሬ በተዋሕዶ ወለድሁህ አለኝ፡፡ ለምነኝ አሕዛብን ርስት አድርጌ እሰጥሃለሁ፤ ግዛትህም በመላው ዓለም ነው፡፡ ዳግመኛም አብ ስለ ቀዳማዊ ወልድ በኃይል ቀኝ ከአንተ ጋር ሳለሁ ከአጥቢያ ኮከብ በፊት ከሆድ ወለድሁህ እንደ መልከ ጼዴቅ ሥርዓት አንተ የዓለሙ አገልጋይ ካህን ነህ ብሎ እግዚአብሔር ማለ፤ ከማለም አይጸጸትም፡፡” (መዝ. 2-7) ትርጓሜውን ይመልከቱ ቤዛ ይስሐቅ በግዕ ከኅቱም ዕፀ ሳቤቅ እንደተገኘ፤ ለእስራኤልም በበረሃ ውስጥ ከኅቱም ዐለት ውኃ እንደፈለቀ፤ የደረቀች የአሮን በትርም እንደለመለመችና እንዳፈራች በሶምሶንም እጅ ውስጥ ከአህያ መንጋጋ አጥንት ውኃ እንደፈሰሰ፤ እንዲሁ የጌታችን ልደት በኅቱም ድንግልና ሆነ፡፡
      በዕፀ ጳጦስ ውስጥ እሳት እንደነደደች ዕፂቱም እንዳልተቃጠለች እንዲሁ የመለኮት አሳትነት ድንግል ማርያምን አላቃጠላትም፡፡
      ለእርሱም ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ከቸር አባቱ ከአብ፣ ከባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስ ጋር ጌትነት ክብር ምስጋና ሰጊድ በትክክል ይገባል ለዘላለሙ አሜን፡፡
      ሰማዕታትን በደም፤ ጻድቃንን በገዳም ሐዋርያትን በአጽናፈ ዓለም ያጸና የባሕርይ አምላክ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖታችን ያጽናን፤  አሜን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን 

No comments: