የሰብአ ሰገል ምንነት፥ ታሪክ፥ ኮከቡ፥ ጉዟቸው፥ በስተመጨረሻው መሰወራቸው
አባታችን አዳም በዕለተ አርብ በነግህ ከተፈጠረ በኋላ እናታችን ሔዋን በሳምንቱ አርብ በዘመናችን አነጋገር 3 ሰዓት ላይ ከግራ ጎኑ ተፈጠረች። በገነትም 7 ዓመት ከ3 ወር ከ 17 ዕለታት ካሳለፉ በኋላ ሕግን ተላልፈው እፀ በለስን በመብላታቸው ከገነት ተባረሩ። በዚህ ግዜ አምላካችን እግዚአብሔር ለአዳም የተስፋ ቃል ሰጠው፤ እርሱም ከልጅ ልጅህ ተወልጀ ከ5 ቀን ከመንፈቅ በኋላ አድንሃለሁ የሚል ቃል ነበረ። ይህ የተስፋ ቃልና ከመላእክት ለአዳም የተሰጡትን ስጦታዎች አዳምና የልጅ ልጆቹ ሲቀባበሉት ቆይቶ ከካሕኑ መልከጼዴቅ እጅ ላይ ደረሰ። ከመልከጼዴቅ አንዳንዶቹ ለአብርሃም ተሰጠ ሲሉ አንዳንዶቹ ደግሞ ለኢት-ኤል ተሰጠ ይላሉ።
መልከጼዴቅም ኢት-ኤልን እንዲህ አለው፦
“ ይህን የዕንቁ እንክብል ውሰድ፤ ሄደህም በአባይ ወንዝ መነሻ ኑሮህን መስርት። እንክብሉ በርሃብና በመከራ ወቅት ይጠቁራል፤ በጥጋብና በመልካም ወቅቶች ደግሞ ያበራል፤ ኢትዮጵያውያን የሚሆኑ ትውልዶችህ ይህን ዕንቁ ተንከባክበው እንዲጠብቁ እዘዛቸው። የሰላሙ ንጉሥ መወለዱንም አንድ ብሩህ ኮከብ ከሰማይ ያመላክታቸዋል፤ ጨረሮቹም ንጉሡ ወደ ሚወለድበት አቅጣጫ ይፈነጥቃሉ። በተወለደበት ቦታ ላይ ሲደርሱ ኮከቡ ንቅናቄውን ያቆማል። ነግሥታቱ ልጆችህም በዚያ ለንጉሡ ‘አንተ የዘላለም አምላክ ነህ’ ብለው ይስገዱለት። ልዩ የሆነውንም የኢትዮጵያ ‘ዮጵ’ የተባለውን ቢጫ ወርቅ፤ እንዲሁም ዕንጣንና ከርቤ ለሰላሙ ንጉሥ ገጸ-በረከት ያቅርቡለት። ”
ከዚህ በኋላ ደሸት(ዘረ ደሸት) 1400-1600 ቅ.ል.ክ ላይ በጣና ዳር ሆኖ ሲጸልይና ከዋክብትን ሲመራመር ድንግል ከነልጅዋ በራእይ ተመለከተ፤ እርሱንም በወርቅና በብር ሰሌዳ ላይ ጽፎ ለትውልድ አስተላለፈ። ከነሸምሸልና ከነ ቀራሚድ በኋላ ደሸት ጣና አከባቢ ጎጃም ውስጥ ደሸት በተባለ ስፍራ ላይ ይኖር ነበረ።
ሰብአ ሰገሎች ማን ናቸው ?
ሰበ ሰገል በመንገድ ላይ |
ስለ ሰብአ ሰገሎች ከማብራራታችን በፊት የስማቸውን አንድምታ ማወቅ ይኖርብናል። ሰብእ ማለት በግእዝ ቋንቋ ሰው ማለት ሲሆን ሰገል ማለት ደግሞ ጥበብ ፈላስፋ እንደማለት ነው። በእንግሊዘኛው ሐዲስ ኪዳን ‘Magi’ ይላቸዋል፤ በብዙ ቁጥር ሲሆን ደግሞ ‘Magus’ ይላቸዋል። እነዚህ ነገሥታት በሥነ-ከዋክብት እውቀት ላይ የተራቀቁ እንደነበሩ ሁሉም ተመራማሪዎች ይስማሙበታል። በቀደምቱ ዓለም ደግሞ ሥነ-ጠፈር፥ ሥነ-ከዋክብትንና ሥነ ሕክምናን ከዓለም አስቀድማ ያጠናችና ጥበቡን ያስተላለፈች ቅድስት ምድር ኢትዮጵያ እንደነበረች ብዙዎች ይስማማሉ።
ተመራማሪው ሉስያን “The Ethiopian where the 1st who invented the science of stars and gave name to the planets ” በማለት ኢትዮጵያ በሥነ ከዋክብትና በተለያዩ ዘርፎች ገናና ጥበብ ከነበራቸውን ሀገራት ውስጥ ተጠቃሽ ናት።
መምሕር መስፍን ሰሎሞን “7 ቁጥር” በተባለው መጽሐፋቸው ላይ “ባቢሎን፥ ግሪክ፥ ሕንድ፥ ኢትዮጵያ፥ ሮም፥ ቻይናና ፋርስ በቀደመው ዓለም 7 የሥነ-ጠፈር አጥኚ ሀገራት ናቸው” በማለት አስፍረዋል።
ነገር ግን ስለ ሰብአ ሰገል መነሻ ስፍራ አንድ ወጥ የሆነ አስተሳሰብ የለም፤ ትልቅ ጥናት የሚያስፈልገው የታሪክ ክስተት ነው።
አንዳንዶቹ በፋርስ ከነበረ “Magauno” ማኅበረሰብ የመጡ ናቸው ይላሉ፤ ይሄም “magic” የሚለው ስያሜ የመጣበት ማኅበረሰብ እንደሆነ ይገመታል። አንዳንዶቹ የፋርስ ሰዎች ናቸው በማለት ዘረ-ደሸት የተባለ ሰው በፋርስ ይኖር ነበረ ይላሉ፤ ይህ ግን በጣም አስቂኝ ነገር ነው ዘረ-ደሸትን ከዞሮአስተር ጋር እያየያዙት ነው። በሀገራችን ደሸት የተባለ ቦታ አሁን ድረስ ጣና አከባቢ ይገኛል። ታዲያ ይህንን ታሪክ ከኢትዮጵያ በማውጣት ለሌላ ዓለም እየሰጡ ነው፤ ልክ የትሮይ ጦርነትን ኢትዮጵያውያን ተዋግተው ታሪኩ ግን ለግሪክ እንደተሰጠው የታሪክ መዛባትና ስርቆት ማለት ነው።
ታላቁ የቤተ-ክርስቲያናችን ሊቅ አለቃ አያሌው ታምሩ ሰብአ ስገል 3 ሲሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነበሩ ብለው “የኢትዮጵያ እምነት በ፫ቱ ሕግጋት” በተባለው መጽሐፋቸው ላይ አስፍረው አልፈዋል። በርካታ የታሪክ ተመራማሪዎች ቁጥራቸው 3 ናቸው በማለት ስማቸውን እንዲህ በማለት ይዘረዝራሉ።
* ሜልኩ [ሜልኪዮር]- የፐርሽያ ንጉሥ
* ማንቱሲማር [ጋስፓር]- የሕንድ ንጉሥና
* በዲዳስፋ የኢትዮጵያ ንጉሥ በሚለው ስያሜ በርካታ ተመራማሪዎች ይስማማሉ። ተመራማሪዎቹ ሰብአ ሰገል 3 ናቸው ያሉበት ዋና ምክንያት ወርቅ፥ ዕጣንና ከርቤን በመገበራቸው ነው።
ከምዕራባውያን ተመራማሪዎች ውስጥ ዊልያም ሊዮ ሀንስበሪና ኢሀርፐር ጆንሰን “Africa’s Golden Historical Facts” በተባለው ጽሁፋቸው ላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ናቸው ቁጥራቸውም 3 ናቸው ይላሉ። አንዳንድ ተመራማሪዎች 3 ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ 12 ናቸው እያሉ የየራሳቸውን ማስረጃዎች ያቀርባሉ።
ሰብአ ሰገል ኢትዮጵያዊ ለመሆናቸው ማስረጃዎች
ሰብአ ሰገሎች ኢትዮጵያዊ ናቸው ከሚሉት ውስጥ አለቃ አያሌው ታምሩ፥ አባ ተስፋ ሥላሴ ሞገስ፥ ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ፥ መሪ ራስ አማን በላይ እንዲሁም ከላይ የተጠቀሱት ዊልያም ሊዮ ሀንስበሪና ኢሀርፐር ጆንሰን ተጠቃሽ ናቸው።
እኒህ መረጃ አድርገው የሚያቀርቧቸው ማስረጃዎች ውስጥ ትንቢተ ኢሳያስ 60፥ 6 ላይ ያለው ቃል ዋነኛው ነው፤ ነገሥታቱ የሳባ ነገሥታት ናቸው ብቻ ስለሚል ነገሥታቱ የሳባ ነገሥታት ናቸው ማለት እኒህ ነገሥታት የተነሱት ከኢትዮጵያ ነው ማለት ነው። እንዲሁም መዝ. 71፥ 9-10 ላይ “በፊቱም ኢትዮጵያ ይሰግዳሉ፤ ጠላቶቹም አፈር ይልሳሉ” በሚለው ቃል ላይ “ኢትዮጵያ” ብሏልና እነዚህ ሰብአ ሰገል ኢትዮጵያዊ ናቸው ብለው ማስረጃ ያቀርባሉ። ከላይ የተጠቀሰው የደሸት ታሪክም አንዱ ማስረጃ ሲሆን ዋናው ማስረጃ ደግሞ ኢትዮጵያ ከዓለም ብቸኛዋ ወርሃ ተኅሣሥን ከሰብአ ሰገል ጋር አያይዛ የሰየመች መሆኑ ነው። ታኅሣሥ ትርጉሙ የማሰስ የመፈለግ ወር ማለት ነውና።
ስለ ሰብአ ሰገል በመጽሐፍ ቅዱስ በማቴ. 2 ላይ የተነገረ ሲሆን ከምሥራቅ መጡ ይላል እንጂ ስማቸውን አይዘረዝርም። ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳና መሪ ራስ አማን በላይ በሰብአ ሰገል ዙሪያ ተመሳሳይ አመለካከቶች ሲኖራቸው ሰብአ ሰገል 12 ናቸው የተነሱትም ከኢትዮጵያ ነው ይላሉ።
የእያንዳንዱን ነገሥታት ስምም በመጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ብለው አስፍረዋል።
1- የጎንጂ ንጉሥ አጎጃ ጃቦን ዮጵ ወርቅ ይዞ ተነሣ
2- አቦል
3- ቶና
4- በረካን 3ቱ የአጎጃ ጃቦን ወንድም የዳጋ ነገሥታት ነበሩ።
5- የሱዳንና የአረብ ንጉሥ መሊ አቡሰላም
6- የሰገልና የማጂ ንጉሥ መጋል
7- የኤውላጥ[ኦጋዴን]ና የሶማሊያ ንጉሥ መቃዲሽ ከርቤ ይዞ ተነሣ
8- የአዳል ንጉሥ አውርና
9- የአፋር ንጉሥ ሙርኖ ዕጣን ይዘው።
10- የአዘቦ ንጉሥ አጋቦን
11- የኑባው ንጉሥ ሀጃቦንና
12- በሳባ ከተማ በሃማሴን ይቀመጥ የነበረው አርስጣ ናቸው።
ሰብአ ሰገል 12 መሆናቸው ከ12ቱ ሐዋርያት ጋር የተያያዘ መለኮታዊ ምስጢር አለው በማለት 2ቱ ተመራማሪውች የኢትዮጵያ ትንሣኤ ታሪክና ስውሩና ያልተነገረው የኢትዮጵያውያንና የአይሁዳውያን ታሪክ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ አስፍረዋል።
አባ ተስፋ ሥላሴ ሞገስ በመጽሐፋቸው ላይ ሰብአ ሰገል 3 ነገሥታትና 2 ልዑላን ናቸው በማለት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ናቸው ይሉንና እኒህ ነገሥታት ኢትዮጵያዊ ናቸው፤ ቀለማቸው ግን ነጭ ሊኖር ይችላል። ያ ኢትዮጵያዊነታቸውን አይፍቅም። ኢትዮጵያዊ ከአንድ እናትና አባት 4 አይነት ቀለም ያላቸው የተለያዩ አበባ የመሰሉ ልጆችን ይወልዳሉና ይላሉ በጥናታቸው ላይ።
አባ ተስፋ ሥላሴ ሞገስ የነገሥታቱን ስምና የትውልድ ቦታ እንዲህ በማለት ያብራሩታል።
1- ናሁ አዳም(ከወንድሙ ጋር) ተነሳ ከኢትዮጵያ
2- ራይናስ(ከወንድሙ ጋር) ከምሥር
3- አሕራም ከየመን
ኮከቡን ያዩት በነገሡ በ13ኛው ዕለት ሲሆን የጉዞው መሪ ከ3ቱ ኢትዮጵያውያን ውስጥ እስከ መካከለኛው ምሥራቅ ይገዛ የነበረው ናሁ አዳም ነው ይላሉ።
በአጠቃላይ በሰብአ ሰገል ማንነት ላይ ሁሉም ተመራማሪዎች ቢያንስ ከ3 ወይንም ከ12 አንዱ ኢትዮጵያዊ ነው በማለት ይስማማሉ።
ከላይ የጠቀስናቸው የመጽሐፍ ቅዱስ የትንቢተ ኢሳያስና የመዝሙረ ዳዊት አገላለጾችና አንድምታዎች በተጨማሪም ኢትዮጵያ በሥነ-ጠፈር ምርምር የተራቀቀች መሆኗ ሰብአ ሰገል ኢትዮጵያዊ ናቸው ወደሚለው ጥናት ይወስደናል።
በዚያም ሆነ በዚህ ሰብአ ሰገል ውስጥ አንዱ ወይንም ከዚያ በላይ የሆኑት ኢትዮጵያዊ ናቸው የሚለው ሃሳብ ሁሉንም ተመራማሪዎች ያስታርቃል።
ሰብአ ሰገል የተመለከቱት ኮከብ ምን አይነት ነው? መቼስ ታየ?
ከጠዋቱ ፀሐይ እንደወጣች ልክ ሦስት[፫] ጫማ በዘመናችን አነጋገር ከጠዋቱ 3 ሰዓት እንደሆነ ጂራቱ 13 ክንድ የሚያህል 7 ሕብረ ቀለማት ያለው በጣም የሚያምር ጂራታም ኮከብ ከምሥራቅ በኩል ወጥቶ በኢትዮጵያና በዓለም ላይ አበራ፤ ይህንን ኮከብ የሚያዩት ለማየት ከአምላካችን ሥላሴ የተፈቀደላቸው ብቻ ናቸው። ይላሉ አባ ተስፋ ሥላሴ ሞገስ።
በተመሳሳይ የታኅሣሡ ስንክሳር “ልውጥ ኮከብ” ይለዋል፤ ይህም የሚቀያየር የሚሰወር ኮከብ ለማለት ሲሆን አንድም ሕብረ ቀለሙን ለመግለጽም ነው። ሰብአ ሰገል በመሃል ከተማ በሚገቡበት ጊዜ ኮከቡ ይሰወራቸው ነበር ይላል። ኮከቡ አንዴ ሕጻን የታቀፈች ድንግል ብላቴናን አንዴ ደግሞ ራስ፥ እጅና እግር ያለውን ሰው ይመስል ነበረ። ይህ ኮከብ የታየው ክርስቶስ ከመወለዱ ከ2 ዓመታት በፊት ነበረ፤ ይሄም ቀድሞ በቅድስት ሥላሴ ፈቃድ የተከናወነ ጎዞ መሆኑን ያመለክተናል። ምክንያቱም ከ2 ዓመት በኋላ በቤተልሔም ስለሚደርሱ ነው።
ስለ ኮከቡ ምንነት በቤተክርስቲያን አስተምሕሮ መሰረት ሁሉም አንድ ወጥ ሃሳብ አላቸው፤ ‘ኮከቡ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ነው’ የሚል። ለዚህም ማስረጃ የሚሆነን ኮከብ በቀን አይታይምና ኮከብ ዝቅ ብሎ እነርሱ ባሉበት ደረጃ አይጓዝም የሚል ነው። ኮከብ የተባለው በምስጢራዊ አነጋገር ነው ይላሉ መተርጉማነ መጻሕፍት።
የሰብአ ሰገል ጉዞ [ከኢትዮጵያ ወደ ኢየሩሳሌም]
ሰብአ ሰገል ከኢትዮጵያ ወደ ኢየሩሳሌም የሄዱት ስዊዝ ካናል ከመከፈቱ በፊት መንገድ ነበረ በዚያ ነው። ከቦታው ለመድረስም 2 ዓመት ፈጅቶባቸዋል። በትርክቶች መሰረት ሲነሱ 12 ነገሥታት ሲሆኑ ኢየሩሳሌም ግን የደረሱት 3ቱ ናቸው ይባላል፤ ምክንያቱም ስንቅ ስላለቀባቸውና ጦር ስለ ተነሳባቸው ነው ይላሉ። ይህ ግን በኢትዮጵያ መዛግብት ዘንድ ተቀባይነት የለውም።
ሰብአ ሰገል ኢየሩሳሌም ሲደርሱ ከተማዋ ተሸበረች እነ ሄሮድስ ደነበሩ፤ ለወረራ የመጡ መስሏቸው ነበረና ኢትዮጵያውያን ሮማውያንን ከጥንት ጀምሮ አይቀጡ ቅጣት ይቀጧቸው ነበረና። እነርሱም ለንጉሡ ልንሰግድለትና ሥጦታ ልንሰጥ መጣን ሲሉ ሄሮድስ ተደሰተ ለርሱ መስሎት ነበረና፤ ለርሱ አለመሆኑን ሲረዳ ግን ተበሳጨ ከእኔ ውጭ የይሁዳ ንጉሥ አለ እንዴ በሚል ተናደደ። እነርሱንም ንጉሡን ስታገኙት ንገሩኝ እኔም መጥቼ እንድሰግድለት አላቸው።
ሰብአ ሰገል ከበረቱ በደረሱ ጊዜ ኮከቧ ቆመች[ ከላይ መልከጼዴቅ ያለውን ይመልከቱ] ወደ ውስጥም ገብተው ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስና ለእናቱ ለድንግል ማርያም ሰግደው ዮጵ ወርቅ፥ ዕጣን፥ ከርቤ፥ ቅባት፥ አክሊል፥ ዘውድ፥ በትረ መንግሥት፥ በትረ መስቀልና ሽቶ ሥጦታ አበረከቱ። ሰብአ ሰገል ከዚህ ሁሉ በኋላ አስቀድሞ የአምላክን ሰው መሆን ለድንግል ማርያም ባበሰራት በሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ትእዛዝ በነፋስ ኃይል በብርሃን ሰረገላ በስውር ዓለምን ዙረው ወደ ሀገራቸው ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ የአምላክን ሰው መሆን የምስራች ለኢትዮጵያ ሕዝቦች በሙሉ አበሰሩ የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች በመሆን ሰበኩ። ከዚህ በኋላ ዋልድባ [አርምኃ ደጋ] በመግባት ከአበው ጋር በመቀላቀል አምላክን ሲያገለግሉ ኖሩ።
ሰብአ ሰገል በሕይወት ይኖራል እንጂ አልሞቱም፥ ቅዱስ ገብርኤል ጌታን ዳግም እስከምታዩት ድረስ አትሞቱም ብሏቸዋልና አሁን እንደነ ነብዩ ሄኖክ፥ ቅዱስ ኤልያስ፥ ቅዱስ ያሬድ፥ ቅዱስ ነአኩቶለአብ፥ አቡነ አረጋዊ እንዲሁም ሌሎች ቅዱሳን ተሰውረው ይገኛሉ።
No comments:
Post a Comment