ነነዌ Nineveh
ነነዌ የአሦራውን ጥንታዊ ዋና ከተማ ስትሆን በላዕላይ መስጴጦምያ በአሁኑ አጠራር በሰሜናዊ ኢራቅ የምትገኝ ከተማ ስትሆን ከተማዋን ሶርያ፣ ቱርክ እና ኢራን ያዋስኗታል፡፡
ነነዌ የአሦራውያን ከተማ |
በወቅቱ በአሦራውያን ግዛት ትልቋ የዓለም ከተማ ስትሆን በወቅቱ ታላቅ የሃይማኖት መዲና እንዲሁም የአሶራውያን አማልክት (ኬሽታር) ማምለኪያ ስፍራ ተገንብቶባትም ነበር፡፡ የከተማው ቅጽር ርዝመት ዐሥራ ሁለት ኪ.ሜ እንደነበርና በውስጥዋም ብዙ ሕንጻዎች ተሠርተውባት ነበር (ዮና 4፡11)፡፡
ነነዌ በመጀመሪያ ስሟ የተጠቀሰው በዘፍጥረት 10፡11 ላይ ሲሆን የአሦር ግዛት ዋና ከተማ፤ በንጉሡ ሕዝቅያስ ዘመን የይሁዳ ነቢይ የነበረው ኢሳይያስ የኖረባት፤ ሰናክሬም በ705 - 681 ዓዓ የገዛት፤ በኋላም በሁለት ልጆቹ አድራማሌቅና ሶርሶር በተባሉ ልጆቹ የተገደለባት ከተማ ናት፡፡ ኢሳ 37፡37-38
ነነዌ በአሁኑ አጠራር በሰሜናዊ ኢራቅ ከተማ ሞሱል (Mosul) በሚባል ስም ትጠራለች፡፡ በወቅቱ መቶ ሃያ ሺኽ ሰው ያኽል ይኖርባት የነበረ ሲሆን ከተማዋን ትንንሾቹን መንደሮች ጨምሮ ዞሮ ለመጨረስ ሶስት ቀን ይፈጃል።
በሕዝቅያስ ዘመነ መንግሥት አሦራውያን እግዚአብሔርን እጅግ አድርገው ተፈታትነውት ስለነበረ የእግዚአብሔር መልአክ ሠራዊታቸውን አጠፋ «በዚያችም ሌሊት የእግዚአብሔር መልአክ ወጣ፥ ከአሦራውያንም ሰፈር መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ገደለ፤ ማለዳም በተነሡ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሁሉ በድኖች ነበሩ። የአሦርም ንጉሥ ሰናክሬም ተነሥቶ ሄደ፥ ተመልሶም በነነዌ ተቀመጠ» (2ኛ ነገ. 19፥10፥35) ተብሎ በቅዱስ መጽሐፍ እንደተጻፈ።
በዚህች ከተማ የሚኖሩት ሰዎች የሚሠሩት ክፋትና ኃጢአት እጅግ ከመብዛቱ የተነሣ ጽዋው ሞልቶ መጥፊያቸው ስለ ደረሰ ለፍጥረቱ ርኅራኄ ያለው እግዚአብሔር ግን ንስሐ ይገቡ ዘንድ ነብዩ ዮናስን ልኮላቸዋል፡፡ ይህ ነብይ ከአሕዛብ ወደ አሕዛብ የተላከ ነብይ ነው፡፡
ነብዩ ዮናስ |
እግዚአብሔር አሶራውያን ንሰሐ የሚገባ ልብ እንዳላቸው ስለሚያውቅ ስለሆነም የራሱን ሰው ነቢዩ ዮናስን ላከው። ዮናስ ግን መሄድ እንቢ አለ። “የእግዚአብሔርም ቃል ወደ አማቴ ልጅ ወደ ዮናስ እንዲህ ሲል መጣ፦ ተነሥተህ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፥ ክፉታቸውም ወደ ፊቴ ወጥቶአልና በእርስዋ ላይ ስበክ “ አለው።
ዮናስ በብዙ መልኩ የተለየ ነቢይ ነው። አይሁዳዊ ነው። የተላከው ግን ወደ አሕዛብ አሦራውያን ሲሆን በጊዜው አሶራውያን እና እስራኤላውያን በጠላትንነት የሚተያዩ ሕዝቦች ነበሩ። ነነዌ የታላቋ የአሦራውያን ዋና ከተማ በነበረች ግዜ አሦራውያን እስራኤላውያንን ገዝተዋቸው ነበር። በወቅቱ አሶራውያን በጣም ጠንካራ ሕዝቦችም ነበሩ።
ነቢዩ ዮናስ ግን፦”እኔ ንስሐ ባይገቡ እስከ ሦስት ቀን ድረስ ነነዌ እንደምትጠፋ ለሕዝቡ ካስተማርኩ በኋላ እግዚአብሔር እንደ ልማዱ ራርቶ ቢተዋቸው ሐሰተኛ ነቢይ ልባል አይደለምን?” ብሎ በመርከብ ወደ ተርሴስ ኮበለለ።እንዲህም ማድረጉ በየዋህነቱ ነው፥ዮናስ ማለት ርግብ ማለት ነውና፥ርግብ ደግሞ የምትታወቀው በየዋህነቷ ነው።
“ዮናስ ግን ከእግዚአብሔር ፊት ወደ ተርሴስ ይኰበልል ዘንድ ተነሣ፤ ወደ ኢዮጴም ወረደ፥ ወደ ተርሴስም የምታልፍ መርከብ አገኘ፤ ከእግዚአብሔርም ፊት ኰብልሎ ከእነርሱ ጋር ወደ ተርሴስ ይሄድ ዘንድ ዋጋ ሰጥቶ ወደ እርስዋ ገባ። እግዚአብሔርም በባሕሩ ላይ ታላቅ ነፋስን አመጣ፥ በባሕርም ላይ ታላቅ ማዕበል ሆነ፥ መርከቢቱም ልትሰበር ቀረበች” ቁ.3።
“መርከበኞቹም ፈሩ፥ እያንዳንዱም ወደ አምላኩ ጮኸ፤ መርከቢቱም እንድትቀልልላቸው በውስጥዋ የነበረውን ዕቃ ወደ ባሕር ጣሉት፤ ዮናስ ግን ወደ መርከቡ ውስጠኛው ክፍል ወርዶ ነበር፥ በከባድ እንቅልፍም ተኝቶ ነበር።”
በመርከብ ውስጥ ያሉት ሁሉ መጸለይ ጀመሩ። ከችግሩ ሊያመልጡ ብዙ ሞከሩ። ጸሎት ትልቅ መፍትሄ መሆኑን የተረዱ ሰዎች ናቸው። መርከቢቱን ከሸክሟ ሊያቀሉ እቃቸውን ወደ ባሕር ጣሉ። ዮናስ ግን ምንም ማድረግ አልፈለገም፤ ወደ መርከቢቱ ታችኛው ክፍል ገብቶ ተኛ። ምክንያቱ ደግሞ ከእግዚአብሔር “ስላመለጠ” ነው።
በዮናስ ድርጊት የተገረመው የመርከቡ አለቃ ወደ ዮናስ ቀርቦ፦ "ምነው ተኝተሃል? እንዳንጠፋ እግዚአብሔር ያስበን እንደ ሆነ ተነሥተህ አምላክህን ጥራ አለው”። ተሳፋሪዎቹ ደግሞ ያ ሁሉ መከራ በማን ምክንያት እንደ መጣባቸው ለማወቅ ዕጣ ቢጣጣሉ፥ዕጣው በዮናስ ላይ ወደቀበት። ነቢዩ ዮናስ በሰው ዘንድ ያልታወቀ ድካሙን ወደ ማስተባበል አልሄደም፥እኛ ብንሆን እንኳን የተሰወረውን በዐደባባይ የተገለጠውንም ቢሆን ዐይናችንን በጨው አጥበን ስናስተ ባብል ነው የምንገኘው።
ነብዩ ዮናስ ወደባህር ሲወረወር |
ተሳፋሪዎቹ በራሱ ከፈረደ ዘንዳ ብለው አልቸኮሉም፥ባይሳካላቸውም እርሱንም ጭምር ለማትረፍ ከወደብ ለመድረስ ታገሉ። በመጨረሻም፦”አቤቱ አንተ አንደ ወደድህ አድርገሃልና ስለዚህ ሰው ነፍስ አታጥፋን፥ንጹሕ ደምንም አታድርግብን፤”ብለው ወደ ባሕር ጣሉት፥ባሕሩም ከመናወጥ ጸጥ አለ።ልክ እንደዚህ ኃጢአታችንን ተናዝዘን ቀኖናችንን ስንፈጽም የታወከው ነገር ሁሉ ከረቂቅ አእምሮአችን ጀምሮ ጸጥ ይላል።የኅሊና እረፍት፥ የልቡና ሰላም እናገኛለን።ሀገርም ቤተ ክርስቲያንም ሰላም ያገኛሉ።እየዋሹ፥እየሰረቁ፥ እያመነዘሩና ደም እያፈሰሱ ጻድቅ ነኝ ማለት የትም አያደርስምና።
No comments:
Post a Comment