‹‹ቃና ዘገሊላ›› ምንድነው?
ቃና ዘገሊላ በቀጥታ ትርጉም የገሊላዋ ቃና ማለት ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን አስተምህሮ በጥምቀት በዓል ማግስት(ጥር 12) ቀን የቃና ዘገሊላ በዓል ይከበራል፡፡ ይህ በዓል ከጌታ ጥምቀት በዓል ጋር ተያይዞ በድምቀት የሚከበር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዳራ ያለው በዓል ነው፡፡ በዓሉ ቃና ዘገሊላ የሚል ስያሜ ያገኘው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የገሊላ ሀገር ክፍል በምትሆን ቃና በተባለችው ቦታ በፈፀመው ተአምር መነሻነት ነው፡፡ የቃና ዘገሊላ ጥንተ ነገሩ ወይም ታሪኩ የተፈፀመው የካቲት 23 ቀን ነው፡፡ ነገር ግን አባቶቻችን የውኃን በዓል ከውኃ በዓል ጋር ለማክበር ብለው የየካቲቱን በዓል ወደ ጥር 12 አምጥተውታል፡፡ ይህም ውኃ ወደ ወይን የተለወጠበትን በዓል ከጌታ ጥምቀት በዓል ጋር ለማስተሣሠር ለማስኬድ ነው፡፡ በመሆኑም የቃና ዘገሊላ በዓል ጥር 12 ቀን ይከበራል፡፡