Thursday, 4 November 2021

ኤክሳይዝ ታክስ ምንድነው?

ኤክሳይዝ ታክስ የቅንጦት እቃዎች ሆነው ዋጋቸው ጨመረም አልጨመረም መሰረታዊ በመሆናቸው ምክንያት የገበያ ፍላጎታቸው በማይቀንስ ዕቃዎች ላይ፣ እንዲሁም የሕብረተሰቡን ጤንነት የሚጎዱና ማህበራዊ ችግር የሚያስከትሉ ዕቃዎችን አጠቃቀም ለመቀነስ ሲባል የተጣለ ታክስ ነው፡፡

ታክሱ በሀገር ውስጥ በሚመረቱና ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ በአንዳንድ የተመረጡ ዕቃዎች ላይ ብቻ የተጣለ ነው፡፡

በዓለማችን ለመጀመሪያ ጊዜ ኤክሳይዝ ታክስ የተጀመረው በእንግሊዝ ፓርላሜንት በ1643 ሲሆን በወቅቱ የመንግስት ገቢን ከፍ ለማድረግ ታስቦ የተጣለ እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ በኢትዮጵያም ታክሱ ከረጅም ጊዜያት ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ ሲሆን የመንግስትን የገቢ አቅም በማሳደጉ ረገድ የበኩሉን ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡

ዓላማው

ማህበራዊ ችግር የሚያስከትሉና የህብረተሰቡን ጤንነት የሚጎዱ ምርቶችን መቀነስ እንዲሁም የቅንጦት የሆኑ የፍጆታ እቃዎች ላይ ተፅዕኖ ማሳደር ነው፡፡ የተሻለ ገቢ ያላቸው ሠዎች በሚጠቀሙባቸው እቃዎች እና የመግዛት ፍላጎታቸው በማይቀንስባቸው ምርቶች ላይ ታክሱ ይጣላል፤ ምክንያቱም ለአገር ተጨማሪ ገቢ ያስገኛልና፡፡

የቅንጦት እቃዎች ከሠው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎት በላይ የሆኑ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ውድ የሆኑ መጠጦች፣ ሲጋራ፣ ሽቶ የመሳሰሉትን ያካትታል፡፡ የህብረተሰቡን ፍላጎት በማይገድቡ እቃዎች ላይ ሲባል እቃዎቹ ኤክሳይዝ ታክስ ስለተጣለባቸው በተጠቃሚዎች ላይ ብዙም የዋጋ ልዩነት የማያመጡ፤ ነገር ግን ለመንግስት ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኙ ለማለት ነው፡፡ ይህ የታክስ ዓይነት ለህብረተሰቡ ጤንነት አደጋ የሆኑ የትምባሆ እና ሌሎች ምርቶች ላይ ዋጋቸው እንዲጨምርና የተጠቃሚዎቹ ቁጥር እንዲቀንስ ታስቦ የሚጣል ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሀገር ውስጥ አምራቾችን ለማበረታታት እንዲሁም ከውጪ የሚገቡ እቃዎች ሀገር ውስጥ የተመረቱትን ከገበያ ውጭ እንዳያደርጓቸው ታስቦ ይጣልባቸዋል።

ስሌት

ታክሱ የሚሰላበት ዋጋ /ስሌት/ ዕቃዎቹ በሀገር ውስጥ የተመረቱ ከሆነ የማምረቻ ወጪው ይሆናል፡፡ ይህም ማለት ምርቱ ሲመረት በቀጥታ ለምርቱ ተግባር የሚውሉ ጥሬ ዕቃዎችና የጉልበት ዋጋ፣ ቀጥተኛ ያልሆኑ ግብዓቶች/overhead costs/ እና ተጨማሪ ወጪዎች ናቸው፡፡ ስሌቱ የማምረቻ መሳሪያዎችን የእርጅና ቅናሽ ታሳቢ አያደርግም፡፡ እንዲሁም ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡ ዕቃዎች ላይ ከሆነ ታክሱ የሚሰላው የዕቃው የግዥ ዋጋ፣ የመድህን አረቦን እና የመጓጓዣ ወጪዎች እንዲሁም የጉምሩክ ቀረጥ ናቸው፡፡

የመክፈያ ጊዜው

ዕቃዎች የተመረቱት በሀገር ውስጥ ከሆነ ከተመረቱበት ወር ቀጥሎ ባሉት 30 ቀናት ውስጥ፤ ዕቃዎቹ ከውጪ ሲገቡ ደግሞ አስመጪው ግለሰብ ወይም ድርጅት ከጉምሩክ ክልል በሚያወጣበት ጊዜ ታክሱ ይከፈላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ዕቃዎቹን ያመረተው ግለሰብ ወይም ድርጅት የታክስ ባለስልጣኑ በሚፈቅድለት የዕቃ መጋዘን ውስጥ ታክስ ሳይከፍል እንዲቀመጥለት ፈቃድ ከጠየቀና ባለስልጣኑም ከፈቀደ ለዕቃዎቹ ታክስ የሚከፈለው ከመጋዘን ሲወጡ ይሆናል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የአምራቹን የስራ እንቅስቃሴ ተመልክቶ የዕቃ መጋዘን እንደሚያስፈልገው ካመነ እንዲያቋቁም ይፈቅድለታል፡፡

በመሆኑም የሚኒስቴሩ ወኪል በስፍራው ተገኝቶ ያልተቆጣጠረ እንደሆነ ምንም አይነት ዕቃ በመጋዘኑ ማስቀመጥም ሆነ እንዲወጣ ማድረግ አይቻልም፡፡ በሌላ በኩል አምራቹ ተገቢ የሂሳብ መዝገቦችንና ሰነዶችን ሳይዝ ከቀረ፣ የየወሩን የሂሳብ መግለጫ ካላቀረበ፣ በአዋጁ በተወሰነው ጊዜ ውስጥ ማለትም ምርቱ ከተመረተበት ወር ቀጥሎ ባሉት 30 ቀናት ውስጥ ታክሱን ካልከፈለ ወይም ያቀረበው የሂሳብ መግለጫ በምርመራ ትክክለኛ ሆኖ ካልተገኘ ታክሱ እስኪከፈል ድረስ ባለስልጣኑ አምራቹን ማንኛውንም ዓይነት ዕቃ ከማምረቻው ቦታ ወይም ከዕቃው መጋዝን ውስጥ እንዳያወጣ መከልከል ይችላል፡፡

# በአዝመራመላኩ #MoR

No comments: