በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ ራሱ ማርሻል ግራዚያኒ ፣ የሜትሮፖሊታን ጳጳስ አቡነ ኪርል እንዲሁም ታላላቅ የኢጣሊያ ሹማምንቶች ፣ ለፋሺስቶቹ ያደሩ ከሀዲ ባንዳዎችና መኳንንቶች ተገኝተው ነበር፡፡ እኩለ ቀን ሲሆን ግራዚያኒ በቤተ መንግሥቱ መግቢያ ደረጃ ላይ ሆኖ ለተሰበሰበው ሕዝብ ዲስኩር ማሰማት እንደጀመረ ቀደም ብሎ ጥቃት ለማድረስ ተዘጋጅተው በነበሩት አብርሃ_ደቦጭ ፣ሞገስ አስገዶም እና ስምዖን አደፍርስ አማካይነት በግቢው በር በኩል ሁለት የእጅ ቦምቦች ተከታትለው ፈነዱ፡፡
ለሶስተኛ ጊዜ የፈነዳው ቦምብ ግን ከፍተኛ የፋሺስት ኢጣሊያ ባለሥልጣናት ከተቀመጡበት መካከል አረፈ፡፡ በቀጣዮቹ ደቂቃዎች አራት ተጨማሪ ቦምቦች ተወርውረው ፈነዱ፡፡ በፍንዳታው ግራዚያኒ ጀርባውን ቆስሎ ወደቀ፣ የኢጣሊያ አየር ኃይል አዛዥ የነበረው ጀነራል አውሬሊዮ ሊዮታ ቀኝ እግሩንና ቀኝ ዐይኑን አጣ ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጉይዶ ኮርቲሲ እና ሌሎች ኢጣሊያውያን እንግዶች በፈንጂው ተጎዱ፡፡ ፍንዳታው ጋብ ሲል ከንቲባ ኮርቴሲ ከወደቀበት ተነስቶ የተሰበሰቡት ኢትዮጵያውያን ላይ በማነጣጠር የመጀመሪያውን ጥይት ተኮሰ። የፋሺስት ፖሊሶችም ምሣሌውን በመከተል ለቀጣይ ሶስት ቀናት የቆየውንና ከተማውን ያዳረሰውን አሰቃቂ ጭፍጨፋ ከዚያው ከቤተ መንግሥት ውሥጥ ጀመሩ፡፡
ፋሽስት ኢጣሊያ በወቅቱ ድርጊቱን ለመበቀል በወሰደው አሰቃቂ ጭፍጨፋ እዚያው ግቢ ውስጥ ከሶስት መቶ በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያንን ጨፈጨፈ። ቀጥሎም የተማሩ ወጣቶችን ፣ የጦር መኮንኖችንና ካህናትን፣ የደብረ ሊባኖስ መነኮሳትን ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያዊያን በፋሽስት ኢጣሊያ እየተለቀሙ በግፍ ተጨፈጨፉ።
ከቃጠሎ ያመለጡትን ደግሞ እያሳደዱ በአካፋ ፣ በዶማና በመጥረቢያ እየቆራረጡ የደም ጎርፍ አወረዱ። ባጠቃላይ በሦስት ቀናት የፋሽስቶች ጭፍጨፋ ቁጥራቸው 30,000 ሺህ በላይ የአዲስ አበባና አካባቢው ነዋሪዎች በጅምላ ተጨፈጨፉ። ቦንቡን የወረወሩት አብርሀ ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም ከራስ አበበ አረጋይ ጦር ጋር ተቀላቀሉ ። በኋላም በሱዳን በኩል ከሀገር ለመውጣት ሲሞክሩ ቀድሞ ፎቶዋቸው ተበትኖ ስለነበር በፋሺስት ወታደሮች ተይዘው በስቅላት ተገደሉ ።
በስተመጨረሻም አፄ ኃይለሰላሴ በ ሱዳን በኩል ጣልያንን ከእንግሊዝ ሰራዊት ጋር ሆነው ድል አድርገው ወደሀገራቸው ሲገቡ የ አብርሃም እና የሞገስ አስከሬን ተቆፍሮ ወጥቶ አሁን አዲስ አበባ በሚገኘው የ ቅድስት ስላሴ አርበኞች ሃውልት ስር እንዲያርፍ አድርገዋል።ወደ መንበራቸው ከተመለሱ በኋላ የካቲት 12 ለተጨፈጨፉት 30,000 ኢትዮጵያውያን ሰማዕታት በ1934 ዓ.ም ሐውልት በአዲስ አበባ ስድስት ኪሎ ላይ ቆሞላቸዋል። በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ላይ የተፈጸመው ይሕን ዘግናኝ የሽብርና የጭፍጨፋ ድርጊት፣ 28 ሜትር በሚረዝመው፣ ባለሦስት ጎኑ የሰማዕታት ሐውልት ዙሪያ በሚታዩት ልጥፍ ቅርፆች እንዲተረኩ ተደርጓል።
No comments:
Post a Comment