ባሕረ ጥበባት የሆነች ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን አስተምህሮዋ ሙሉ በሙሉ በመለኮታዊ መገለጥ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በሥጋዊና በደማዊ የግል አስተሳሰብና ፍልስፍና ላይ የተመሠረተ አንድም አስምህሮ የላትም፡፡ ከልዑል እግዚአብሔር ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የነበራቸው ልጆቿም ቅድስናን ገንዘብ ያደረጉ ናቸው፡፡ ቅድስናንም ገንዘብ ማድረጋቸው ሰማያዊው ምሥጢር ፍንትው ብሎ እንዲታያቸው ምክንያት ሆኗቸዋል፡፡
ፈጣሬ ዓለማት ልዑል እግዚአብሔር አንድ ዓለም ብቻ ሳይሆን 20 የተለያዩ ዓለማትን እንደፈጠረ የምታውቅ ብቸኛዋ የእምነት ተቋም ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ብቻ ናት፡፡ ስነ ፍጥረትን እጅግ በሚገርም ሁኔታ ተንትኖ የሚያቀርበው መጽሐፈ አክሲማሮስም ሆነ ሌሎቹ ቤተክርስቲያን ድርሳናት እንደሚያስረዱት ከሆነ እግዚአብሔር 20 የተለያዩ ዓለማትን ፈጥሯል። እነዚህም፡- 5ቱ ዓለማተ መሬት፣ 4ቱ ዓለማተ ማይ፣ 2ቱ ዓለማተ ነፋስ እና 9ኙ ዓለማተ እሳት ናቸው፡፡

