የአምሐራ ሕዝብ የዘር ሀረግ ፣ የተድባበ ጽዮን አመሰራረት እና አምሐራ ሳይንት
======= ======= =======
ዘመናት ተነባብረው ሰማ ሰማያት የሚደርስ የእድሜ ክምር ቢሰሩ ታሪክ የበለጠ ያደምቁት እንደሆነ እንጅ አያደበዝዚትም፡፡ታሪክም የክንዋኔ ወቅቱን እያሰላ እና እየቀመረ ልደትና ህልፈትን በየተራ እየመዘገበና እያፈራረቀ በገቢረ ተቃርኖ አንዱ የሌላውን ሁነት እያጎላ የሚሔድ በመሆኑ በሂደት የሚገጥመው ውጥንቅጥ ባህሪ ለውበቱ ተጨማሪ ድምቀት ይሰጠዋል፡፡
በዘመን በቦታ በባታሪኩና ተዛምዶ ባላቸው ክስተቶች ውህደት የሚዘከር ማህበረሰባዊ ክንዋኔ የራሱን የጉዞ ምህዋር ተከትሎ ለአፍታ ሰይቦዝን አሻራውን እየጣለ ወደ ሌላው ክንውን ይሸጋገራል፡፡ለዚህ ሽግግር በዋቢነት ቆመው ምስክርነታቸውን የሚናኙት በዘመናቱ ዑደት የመዘወርነት ሚናቸውን የሚጫወቱት ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ኪነ ጥበባዊ ክንውኖች ውሎቸው ከደለደለው ቦታ ላይ ኋላ ቀሪና ወሬ ነጋሪ ማህተማቸውን በጽናት ቆሞ የእምነት ቃሉን ሲያስከብር ይኖራል፡፡
ሰው ሰራሽ ትውፊትም ይሁን የተፈጥሮ ክስተት የያዘውን መልእክት ሳይጨምር ወይም ሳይቀንስ ማንነቱን በትክክል ያሥረዳል፡፡የመልዕክቱ ይዘት በረቂቅነት ወይም በግዝፈት በስፋት በይም በጥበት የሚወሰሰን ላይሆን ይችላል፡፡ታሪክ በታሪክነቱ ይዘከራል፤የአስረጅነት ደርሻም እንደ ባታሪኩ የብርታት ልክና የተውስታ መጠን ይለያያል፡፡
የሰው ልጅ ከሌሎች ፍጥረታት እንድልቅ ያደረጉት ተፈጥሮ ልዩነቱ፣ማህበራዊ የአኗኗር ዘደውና ቋንቋው ናቸው ማለት ይቻላል፡፡የእነዚህ ልዩነቶች ህብር ቀስ በቀስ የሰውል ልጅ አጎልብቶ ሎሎችን በበላይነት እንድመራ አደረገውና በድንግልና የተሸበበችውን አለም በጥበቡ ልጓሟን ፈትቶ እንደፈለገ ሊያሰግራት አስቻለው፡፡
ከአዳም መፈጠር ጀምሮ አስከ አሁን ድረስ ያሉትን የብሉይና የሐድስ ዘመናት ተጉዞ ለመምጣት የመንገዱ ርዝማኔና ጠመዝማዛነት የሁነቶች ውስብስብነት እርምጃን የሚያደናቅፍ ቢሆንም በሀሳብ ማዕበል እየተገፉና አቋራጭ መንገዱን እየመረጡ የመጓዙን ጥበብ በመጠቀም ዓለም ከተፈጠረ ዘመን ም ከተቆጠረ እስካሁን ያለውን ታሪክ በዓይን ህሊና ለመቃኘት ካልሆነ በስተቀር በዚች አጭር ጽሁፍ ቀንጭቦ ለማቅረብ የማይቻል መሆኑን አንባቢ ይገነዘበዋል፡፡ምክናየቱም አባይን በጭልፋ ስለሚሆን፡፡
የሰው ልጅ መጀመሪያ የሆነው አዳም ሲፈጠር ( ቅድመ ልደት ክርስቶስ ) የዘመን ቁጥር አንድ ተባለ፡፡ ከግራ ጎጎኑ ከተፈጠረችለት ሄዋን ጋር በመሆን በዝተውና ተባዝተው መሬትን እንድሞሏት በተሰጠው የፈጠሪ ትዕዛዝ ቀስ በቀስ ምድር በህዝብ ተሞላች፡፡እስከ 4000 ዓ.ዓ ድረስም ሰው ልጅ በተፈጥሮ ባገኘው እውቀት እየተገዛ፣በልበ ብርሃንነት እየተመራ እስከ ዘመነ ሙሴ ቆየ፡፡እስከዚያ ዘመን ድረስ የተጻፈ ነገር ባለመኖሩ አራቱ ሽህ ዘመን የህገ ልቦና ዘመን ተባለ፡፡
በጥፋት ውሃ ዘመን ለአዳም አስረኛ ትውልድ የሆነው ኖህ ከስምንት ቤተሰቦቹ ጋር በመርከብ ሲያመልጥ ሴም፣ካምና ያፌት የሚባ ልጆቹን ይዞ ነበር፡፡ካም ቀደም ብሎ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ከልጆቹ ጋር የኖህን እምነት አስፋፍቶ ስለነበር ኢትዮጵያ በህገ ልቦና ዘመን ጭምር አመልኮተ እግዚአብሔር ትከተል እንደነበር የመጽሐፈ ቅዱስ ማስጃዎች ያረጋግጣሉ፡፡ለአብነት ብንወስድ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ኢትዮጵያዊ ት ማግባቱ በኦሪት ዘኅልቁ ምዕራፍ 12 ከቁጥር 1 ጀምሮ ተጽፎ ይገኛል፡፡እንደነገደ ካም ሁሉ በሕገ ልበኖና ዘመን ከደቡብ አረብ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ነገደ ዮቅጣን ተብለዋል፡፡አምሐራ የሚለው የዘር ሐረግ የተገኘውም ከዚህ ስረወ መሰረት መሆኑን ተክለጻድቅ መኩሪያ የግራኝ አህመድ ወረራ በተባለው መጽሀፋቸው (1966 ዓ.ም ፣ገጽ 8) አመልክተዋል፡፡
ከላይ በጥቂቱ ጨረፍ ተደርጎ ቀረበው የታሪክ ማስረጃ የአማራ ህዝብ የመጣበትን የመስመር አቅጣጫ ለማመልከትና ከነገደ ዮቅጣን/ከሴማዊያን ጋር ያለውን ተዛምዶ ለመግለጽ የመጣ ነው፡፡ የአማራው ሕዝብ የመጀመሪያው መገኛ ሀገረ አምሐራ ሳጥንትና ቤተ አምሐራ ተብሎ ይተወቅ የነበረው አካባቢ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያረጋግጣሉ(ተክለ ጻድቅ መኩሪያ፡ዝኒከማሁ)፡፡በ1262 ዓ.ም .የነገሰው የአማራ ንጉስ አጼ ይኩኖ አምላክም የአማራው ንጉስ ቋንቋ (አማርኛ) የመንግስቱ ኦፊሲያል ቋንቋ እንደሆነ ያወጀው በአምሐራ ሳይንት ነው፡፡
በሌላ በኩል ከክርስቶስ ልደት በፊት በ1 ሽህ ዓ›ዓ ገደማ ከደቡብ አረቢያ ፈልሰው ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የሴም ዘሮች ሳባ ተብሎ ይጠራ ከነበረው የየመን ክፍል የመጡ ሲሆን ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ በኋላ በሀገሪቱ ቀድመው ከገቡት የካም (የኩሽ)ዘሮች ጋር በመቀላቀል በባህል፣በኢኮኖሚና በማህበራዊ ህይዎት ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት ችለው ነበር፡፡የሳባ ቋንቋንም ለኢትዮጵያውያን ያስተዋወቁትም እነሱው ናቸው፡፡ኢትዮጵያውያን ከግዕዝ ቋንቋ አስቀድሞ በሳባ ቋንቋ ሲጠቀሙ የቆዩ ስለመሆናቸው በሀገራችን የሚገኙ የድንጋይ ላይ ጽሑፎች ማስረጃወች ናቸው፡፡
ይሁን እንጅ በስነ ጽሁፍ ደረጃ ከፍተኛውን ቦታ ይዞ የሚገኘው ግዕዝ ነው፡፡የግዕዝ ስነ ጽሁፍ ተስፋፋው የክርስትና ሃይማኖት ወደ ኢትዮጵያ ከገባበት ድኅረ ልደት ክርስቶስ ከ4ኛው ምዕተ አመት ጀምሮ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ጳጳሳት ከእስክንድሪያ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ በርካታ የሃይማኖት መጻሐፍት ወደ ግዕዝ ተተርጉመዋል፡፡የግዕዝ ሥነ ጽሁፍ ቅርስ የተበራከተውና የዳበረው ወርቃማው ዘመን ተብሎ በሚጠራው በአፄ ዘርአ ያዕቆብ ዘመነ መንግስት ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ጸሐፍት ከዚያ ጊዜ ጀምሮ አያሌ ድርሳናትን(ታከ ነገስታትን፣ክበረ ነገስታትን፣ዜና መዋዕሎችን፣ወዘተ.) አዘጋጅተው አውርሰውናል፡፡
ወደ ቀድሞው ነገር እንመለስና የሕገ ልቡና ዘመን ተገዶ ሕገ ኦሪትን ሙሴ በጻፈው ቀሪው 1500 ዓ.ዓ በዚሁ ሕግ የሰው ልጅ እንድተዳደርበት ሆነ፡፡ ከዚሁ ጋር በዘመነ ኦሪት የቃል ኪዳን ታቦት የእግዚአብሔር ማደሪያና በምድር ላይ ያስቀመጠው ማህተሙ ተቀረጸ፡፡አስርቱ ቃላት የተጻፈባቸው ሁለቱ የድንጋይ ጽላቶች የሚቀመጡበት ታቦት ከእንጨት የተሰራና ውጭውም በወርቅ የተለበጠ ነበር፡፡
ለዚህ ታቦት የመጀመሪያውን መቅደስ ያሰራው ጠቢቡ ንጉስ ሰሎሞን እንደነበረ ከዚያም በ587 ዓ›ዓ ናቡከደነጾር ኢየሩሳሌምን ሲያቃጥል ታቦተ ህጉ በኢየሩሳሌም አለመኖሩ ብቻ ሳይሆን እስራኤላዊያን ሁለተኛውን ቤተ መቅደስ ከጦርነት በኋላ ሲገነቡ ታቦተ ሕጉ በውስጡ ያልነበሩ መሆኑን በታሪክ መዛግብት ተጽፎ ይገኛል፡፡
በእስራኤል ጥበበኛ እና ገናና የነበረው ንጉሥ ሰሎሞን በዘመኑ ብቻ ሳይሆን አሁን ድረስ የሚሞገስ ብልህ ለመሆኑ አያጠራጥርም ፡፡የኢትዮጵያና የመካከለኛው ምስራቅ ግንኙነት በተለይ ነበንግዱ ዘርፍ በመጠናከሩ ምክናየት ንግስተ ሳባ በኢትዮጵያ ነግሳ በነበረችበት ዘመን የእስራኤሉን ንጉስ ዝናና ብልሃት በመስማት አድናቆቷ እየጨመረ በመምጣቱ በተላይ ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል እየተመላለሰ በንግድ ዓለም ከፍተኛ ደረጃ ላይ የነበረው ‹‹ታምሪን›› የሚባል ነጋደ ንግሥት ሳባ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ ንጉስ ሰሎሞንን እንድትጎበኘው ይበልጥ በማነሳሳት እረገድ ከፍተኛውን ሚና እንደተጫወተ ይናገራል፡፡ታምሪን ንጉስ ሰሎሞን ታላቁን ቤተ መቅደስ በሚያስገነባበት ወቅት ለንጉስ ሰሎሞን ወርቅ ከለገሱት ሰዎች አንዱ እንደነበር ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡
ክብረ ነገስት እንደሚገልጸው የክርስቲያናዊት ኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያው ሰሎሞናዊ ሥርወ መንገስት አመሰራረት ከዚሁ የንግስተ ሳባ የእስራኤል ጉብኝት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ክብረ ነገስት ፡ንግስተ ሳባ ስጦታ ይዛ ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ ከንጉስ ሰለሞን ጋር መገናኘቷን ፣ከንጉስ ሰሎሞን ጸንሳ መመለሷንና ቀዳማዊ ምኒልክ የተባለ ወንድ ልጅ መውለዷን ፣ቀዳማዊ ሚኒሊክ ሲያድግ ወደ እስራኤል ሄዶ ከአባቱ ጋር መገናኘቱንና ጽላተ ሙሴን ወደ ኢትዮጵ ያ ይዞ መጥቶ የነገሰ የመጀመሪያው ሰሎሞናዊ ክርስቲያናዊ ንጉስ መሆኑን በዝርዝር ያስረዳል፡፡
ንጉስ ሰሎሞን ቀዳማዊ ምኒሊክን ቅብኣ መንግስት ቀብቶ ከአስራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች በተውጣጡ በኩሮች ታጅቦ ወደ ኢትዮጵያ እንድመለስ አደረገው፡፡በኩሮቹ እስራኤላውያን ታቦት ጽዮንን እና ሎሎች ታቦታትን በተመሳሳይ ሰርተውና በወርቅ ለብጠው በማስቀመጥ የሙሴን ታቦታት ሕግ ከመገልገያ ንዋየ ቅድሳት ጋር በመያዝ ወደ ኢትዪጵያ መጡ፡፡የአራቱ መናብርት ስልጣንም ከበኩሮች እና ታቦተ ሕጉ ጋር አብሮ መጣ፡፡አራቱ መናብርትም
1.አክሱም ጽዮን
2.ተድባበ ጽዮን
3.ጽርሃ ጥዮን
4.መርጡለማርያም (ኋላ በሐድስ ኪዳን ጣና ቂርቆስ ) የተባለው፡፡
ቀዳማዊ ምኒሊክ አስራ ሁለቱን በኩር እስራኤላውያን ከታቦተ ህጉ ጋር ይዞ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ እናቱ ሳባ በክብር ተቀብለችው፡፡ታቦተ ጽዮንን እና ሌሎችንም ታቦታት ቤተ መቅደስ አሰርታ በክብር አስቀመጠቻቸው፡፡ ለካህናቱም በመቅደሱ ዚሪያ ያለውን ሰፊ ቦታ ሰጠቻቸው፡፡ልጇን ምኒሊክንም አነገሰችው፡፡(ታሪክ ዘመን ዘዳግማዊ ምኒሊክ ከገጽ 13-19)
ቀዳማዊ ምኒሊክ በትረ መንግስቱን ከጨበጠ በኋላ የአራቱን መናብርት ስልጣን ለይቶና ሕገ ኦሪትን እንድስፋፋ ለማድረግ ሹመት ሰጥቶ ስርዓቱን ከትውልድ ወደ ትውልድ እንድተላለፍ አደርጓል፡፡በዚህም መሰረት
1.ለአክሱም ጽዮን የንቡረእድነት ማዕረግ
2.ለተድባበ ጽዮን የፓትርያርክነት ማዕለግ
3.ለመርጡ ጽዮን የርዕሰ ርኡሳንነት ማዕረግ
4.ለጽርሃ ጽዮን (ጣና ቂርቆስ) ደግሞ የሊቀ ካህናት ማዕረግ ሰጥቶ እስከ ኃይለ ስላሴ ዘመነ መንገስት ድረስ ሲሰራባቸው ኖረዋል፡፡በተሰጣቸው ስልጣን በተለይ በስርአተ ንግስ ወቅት፡-
ንቡረእዱ ለንጉሱ ዘውድ ይደፋሉ
ፓትርያርኩ ሰይፈ መንገስቱን ያስታጥቃሉ፣ጸሎት ይሰጣሉ
ርእሰ ርኡሳኑ ልብሰ መንግስቱን ያለብሳል
ሊቀ ካህናቱ ደግሞ ቅብአ መንገስቱን ይቀባል
ታሪክ ታክ ነውና ከሕገ ልቦናና ሕገ ኦሪት ዘመን እስካሁን ስንመጣ የምንገልጻቸው ሁነቶች ተረት እንዳይመስሉ ቢያንስ የሕገ ኦሪት ሰርአታት እስካን መዝለቃቸውን ብናይ ከጥንቱ አሰራር ሳይወጡ ዛሬም የምናከናውናቸው ልማዳዊ ደርጊቶች አሉ፡፡ለአብነት የሚከተሉትን መጥቀስ ይቻላል፤
የታቦት አከባባር(ሥርአተ ዑደት)
ቀዳሚት ሰንበትን ማክበር
የቅኔ ማህሌት ሰርአታትና መዝሙር መሳሪያዎች
የካህናት አልባሳት
ግርዛት
የሚበሉ እና የማይበሉ እንስሳትን መለየት
እንግዳ መቀበል ወዘተ
ሕገ ኦሪትን ከምንጊዜም በላይ ቀዳማዊ ምኒሊክ በኢትዮጵያ ሲያሥፋፋ በአምሐራ ሳይንት ም የራሱን መገነጫ ተግባራት አከናውኖ ነበር፡፡እንደትአሚናዳብ የተባለውን የቀዳማዊ ዳዊትን የወንድም ልጅ ወደ አምሐራ ሳይንት በመላክ አሁን ርዕሰ አድባራት ወገዳማት ተድባበ ማርያም ባለችበት ቦታ ላይ ሕንጻ ቤተክርስቲያን እንድገነባ አድርጎ ነበር፡፡አሚናዳብም ህንጻውን አስገንብቶ እንዳጠናቀቀ በቦታዋ ላይ በፓተርያርክነት ለመጀመሪያ ጊዜ የሾመው አዛርያስ የተባለውን ነው፡፡
አዛርያስ በተድባበ ማርያም ፓትርያርክ ሁኖ ሲመጣ አካባቢውን ለ12ቱ ነገደ እስራኤላውያን በኩሮች ለሀገራቸው ማስታወሻ ይሆናቸው ዘንድ በአምሳሌ ኢየሩሳሌም ስለሰየማቸው ቦታወቹ እስካሁን በእነዚህ ስያሜዎች ይጠራሉ፡፡አሁን ተድባበ ማርያም ያለችበት ከፍተኛ አምባ 12 በሮች ያሉት ሲሆን ዙሪያውን ገደል ነው፡፡አምባውን ገሊላ ሲለው ከአምባው ወጥተን በፊት በር በኩል ያሉትን ኬብሮን፣ጋዛ፣ሎዛ፣ደብረ ታቦር፣ቢታንያ አላቸው፡፡ከፊት በር በስተቀኝ ጌላት፣ኢያርኮ፣ኢየሩሳሌም፣ጎለጎልታ ብሏቸዋል፡፡በቦረና መግቢያ ያሉትን ደግሞ ሊባኖስ፣አርሞንኤም፣ደማስቆ፣ደብረፋራን ብሎ ሰይሟቸዋል፡፡
በስርአተ ማህበሩና በየመንግስታቱ አስተዳደራዊ ለውጥ በተካሄደ ቁጥር መንግስቱን የረጅም ጊዜ ግብ ለማሳካት በሚደረገው ጥረት በብዙ ጉዳዮች ዙሪያ ጥገናዊ ለውጥ ቢስተዋልም በእምነት ዙሪያ ግን ነባራዊ ይዘቱን ለመቀየር አስቸጋሪ ስለሆነ ሳይደብስ ከአንዱ ወደ ሌላው እየተሸጋገረ መምጣቱ በራሱ አስደናቂ ነው፡፡ይህ የሚያመለክተው በብሉይ ዘመን (ቅድመ ልደት ክርስቶስ)165 ነገስታት በኢትዮጵያ ነግሰዋል፣ከክርስቶስ ልደት በኋላም 160 መንግስታት እስካሁን ተፈራርቀዋል፡፡ከሶስት መቶ ሃያ መንግስታት ጋር ተቻችሎ የቆየ እምነት፣ባህልና ወግ አለን ማለት ነው፡፡
በዘመነ ሐድስ (ከክርስቶስ መወለድ በኋላ) ርዕሰ አድባራት ወገዳማት ተድባበ ማርያም አክሱም ጋር ሕገ ወንጌል ተቀብላ አሁኑ ትውልድ ድረስ ያሸጋገረች መሆኗም የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ኢዛናና ሳይዛና በመባል ይታወቁ የነበሩት ወንድማማቾች (በኋላም በስመ ክርስትናቸው አብርሃናአጽብሃ የተሰኙት)በ328 ዓ.ም የአክሱም ጽዮንን ቤተ መቅደስ ካስገነቡ በኋላ በ330 ዓ.ም አምሐራ ሳይንት መጥተው የተድባበ ማርያምን ህንጻ ቤተክርስቲያንን ማስፈገንባታቸውን የታሪክ ድርሳናት ያመለክታሉ፡፡
በዚች ታላቅ ደብር በርካታ ንዋያተ ቅድሳት አሉ፡፡
መቸም የነገስታቱን ነገር ደጋግሞ ማንሳት መሰላቸትን ሊፈጥር ቢችልም በኋለኛው የአክሱም ዘመነ መንግስት በአጠቃላይ ቤተ አምሐራ የሚባለው አካባቢ በተለይ ደግሞ አምሐራ ሳይንት የሀገሪቷ ማህበረ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ አንድ ማዕከል የነበረው መሆኑ በታክ ድርሳናት እንደሚጠቁም መግለጽ ተገቢ ነው፡፡በኋላም መንበረ መንግስቱ ወደ ቤተ አምሐራ ሲዛወር የአማራዎቹ ቋንቋ ግዕዝን ተክቶ መንግስት መስሪያ ቋንቋ መሆን እድል አግኝቷል፡፡ በዚህ ረገድ አምሐራ ሳይንት የነበራትን ሚናም መገመት ይቻላል፡፡እንድሁም በታቦር ተራራ በስተቀኝ በኩል ባለው አደባባይ አጼ ይኩኖ አምላክ በ1270 ዓ.ም አማርኛ ኦፊሲያል ቋንቋ እንድሆን ማድጋቸውን የሚጠቁሙ መረጃዎች አሉ፡፡(የኢትዮጵያ ፊደል ታሪክ ፣ገጽ 76-77 )ይመልከቱ፡፡
# በመጨረሻም ውድ የአምሐራ ሳይንት ልጆች ዘራፍ በል ሳይንቴ የሚለውን ቅኝት አሁን ላይ መቃኘት ያለብን አንድ አሃድ ያለው ማህበረሰብ በመፍጠር እንደ ትውልድ የበኩላችንን ኃላፊነት ለመወጣት የአምሐራ ሳይንት ልማት ማህበር አባል በመሆን የድርሻችንን እንወጣ።
ምንጭ፡-የአምሐራ ሳይንት ባህልና ቱሪዝም ሲምፖዚየም መጽሔት 2002
No comments:
Post a Comment