ታሪክ ሦስቱን ዘመናት/ትውልድ (ኃላፊውን፣ ነባራዊውንና መጻዒውን) የሚያስተሳስር ድንቅ ድልድይ ነው፡፡
ታሪክ አንድን ጉዳይ ከሥር መሠረቱ ጀምረን እንድናውቀው ስለሚያግዘን የአንድን ክሰተት እውነታነት በስሜት ያይደለ አሳማኝ በሆነና ቅቡልነት ባለው መልኩ (logically) እንድንሞግተው፣ አልያም እንድንቀበለውም ያግዘናል፡፡ እናም ታሪክን በአግባቡ የሚያጠና ትውልድ በቂ መረጃ ያለው (well informed)፣ በራሱ የሚተማመን (self-confident) እና ትክክለኛውን ውሳኔ መስጠት የሚችል (decision maker) ይሆናል፡፡
የትናንቱን ውሎአችንን ገምግመን፣ ዛሬን በጥበብ ለመኖር፣ ለነገው ደግሞ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ ታሪክ ትልቅ ድርሻ አለው፡፡ እናም ያለፈውን ስህተት ለማረም፣ በጎ በጎ ጅምሮችን ለማበረታታት፣ የጠባይ ለውጥ ለማምጣትም የሚያግዝ የእውቀት ዘርፍ ነው፡፡ (ግዛው፤ታሪክ፣ ትርክና ታሪካችን፤ 2005:43).
ምንጊዜም ቢሆን ያለፈውን ታሪክ የሚዘነጉ ሰዎች መልሰው መሳሳታቸው አይቀሬ ነው፡፡ ታሪክን የሚያስታውሱ አንዳንዶች ደግሞ ሊማሩበት ሳይሆን የጥንቱን ቁስል በመነካካት የበለጠ ለማድማት፣ ለመበቀል፣ የጥላቻን እሳት ለማቀጣጠል ሊጠቀሙበት ይጥራሉ፤ ይህ አካሄድ ግን ኋላቀርነት እንጂ የሰለጠነ አካሄድ ሊሆን አይችልም፡፡ የታሪክ መሠረታዊው ጠቀሜታ ግን መጥፎውን ታሪካዊ ክስተት ለማውገዝና ከዚያ ልምድ በመቅሰም ዳግመኛ እንዳይከሰት ለመከላከል፣ በአንጻሩ መልካሙን ክስተት ደግሞ ለማበረታታት (ደጋግሞ እንዲከሰት ለማድረግ) ነበር፡፡ በምንም መንገድ የትላንቱን የምናጠናው ጥላቻን ለመቀስቀስ፣ ግጭቶችን ለማራገብ፣ ቁስሎችን ለመነካካትና እንዳይድኑ ለማመርቀዝ አይደለም (ታየ ቦጋለ፤ መራራ እውነት፤ 2011፡37)፡፡
የሚያሳዝነው ግን ሰው በዚህ ረገድ ከታሪክ መማር አለመቻሉ ነው፡፡ በርናርድ ሻውና ሄግል የሚባሉ ሁለት የታሪክ ምሁራን ይህን ሐቅ በተመለከተ ትዝብታቸውን ሲያስቀምጡ፡- ‹‹ከታሪክ የምንማረው ትልቅ ቁምነገር ቢኖር የሰው ልጅ ከታሪክ መማር አለመቻሉን ነው›› ብለዋል፡፡ (Hobsbawn, Eric J (1990). Nations & Nationalism Since 1780).
በመሠረቱ ታሪክ አሁን ላለውና የሚመጣውንም ትውልድ ለማቅናት (አቅጣጫ ለማስያዝ) እንጂ ያለፈውን ለመበቀል አይጻፍም፤ ይህ የ21ኛው መ/ክ/ዘመን አካሄድ አይደለም፡፡ አንዱ ምሁር፡- ‹‹በታሪክ ውስጥ የተፈጸመን ስህተት በክፉ መበቀል ዳግም መሳሳት ነው›› እንዳሉት (ግዛው፤2005:116). ‹‹ያለፈው ታሪክ ትክክል አይደለም›› የሚል ቢኖር እንኳን ጥበብ በተሞላበትና በተጨባጭ ማስረጃ ላይ ተመሥርቶ ለማረቅ መጣር እንጂ በጥላቻ ተሞልቶ ታሪክን ለመጻፍና ለመረዳት መሞከር ወደ ባሰ ስህተት ይመራል፡፡
በታሪክ ውስጥ ስለሚታወሱት ግለሰቦችም ቢሆን (ቀደምት የሀገሪቱ መሪዎች ነገሥታትን ጨምሮ) ዶ/ር ገበዜ
ጣፈጠ ቀድሞ በተጠቀሰው መጽሐፋቸው እንደሚሉት፡- ‹‹ታሪካዊ ሥራዎችን ከሰሩት ሰዎችም ጋር በታሪክ አማካኝነት እየተዋወቅን ከእነርሱም መካከል በአካል አብረውን እንዳሉ ያህል የምንወዳቸውም የምንጠላቸውም ይኖራሉ፡፡ የአንዳንድ ሰዎችን ዝና በታሪክ ሰናነብ መንፈሳችን ይቀሰቀሳል፣ የአንዳንዶችንም ስናነብ መንፈሳችን ያዝናል፡፡›› እንዳሉት የተደበላለቀ ስሜት ይኖረናል፡፡
ነገር ግን በጎም ይሁን ክፉ ሥራ ሠርተው ያለፉትን መሪዎች እየወቀሱ፣ ሁሌ በሞት ካሸለቡትና ስለራሳቸው መከራከር ከማይችሉት ጋር ትግል መግጠም ሥልጡንነት አይደለም፤ እነርሱ ከዚህ በኋላ ለምን ይህን እንዳደረጉ መልስ ሊሰጡን አይችሉምና! የአገራችን ሕዝብ ‹‹የሙት ወቃሽ አትሁን›› የሚለውም ለዚሁ ነው፡፡ አሁን ያለው ትውልድም በአያቶቹና በቅድመ አያቶቹ ጥፋት ሊወቀስ፣ እንደ ‹‹ማስተሠርያ ፍየልም›› ሊቅበዘበዝና ተላልፎ ለሞት ሊሰጥ አይገባውም፤ በዚያ የታሪክ ክስተት ውስጥ ምንም ዓይነት የአዎንታዊም ይሁን የአሉታዊ ድርሻ አልነበረውምና፡፡ አሁን ከእኛ የሚጠበቀው ‹‹የወደፊቱ ትውልድ እንዴት በተስተካከለ አካሄድ ይቀረጽ?›› የሚለውን ጥያቄ መመለስ መሆን አለበት፡፡
የትኛውም ታሪክ ያለ ስህተት አይታለፍም፤ እድፍና ድፍርስ አይታጣበትም፡፡ ይህ ደግሞ በሁሉም የዓለም ታሪክ ውስጥ ያለ ሐቅ እንጂ ለእኛ (ለኢትዮጵያ) ብቻ የተለየ ክስተት አይደለም (ግዛው፤ 2005:103). ታሪክ የሚመለከታቸው (በታሪክ ውስጥ የሚያልፉት)፣ መልካምም ይሁን ክፉ ታሪክ የሚሰሩት ሰዎች ናቸው እንጂ መላእክት ስላልሆኑ ‹‹ለምን ተሳሳቱ?›› ሊባል አይችልም፡፡
በአጠቃላይ እነዚህንና መሰል የታሪክ አጠናን ነጥቦችን (ግቦችን) መገንዘብ በተለይም በአሁኑ ጊዜ ከታሪካዊ ዘገባዎችና አሉታዊ ተጽእኖዎቻቸው ጋር ተያይዘው የሚነሱትንና ተያያዥ ጉዳዮችን በአግባቡ ለማስተዋል ያግዘናል፡፡ በዚህም መሠረት ‹‹በውኑ ታሪክን የማጥናትና የማወቅ ጥቅሙ/ግቡ ምንድን ነው?›› ለሚለው ቁልፍ ጥያቄ የሚከተሉትን መጠይቃዊ ምላሾች እንጠቁም፡-
በታሪክ የተፈጸመን ስህተት ለመድገም ወይስ ከዚያ ተምረን የተሻለ ነገር ለመሥራት?
ጥቁር ጠባሳ አስመዝግበው ያለፉ የጥንት ሰዎችን ተግባር እያነሣን ለመራገም ወይስ ከእነርሱ የተሻለ አሳብ አመንጭተን ትውልድ የሚያንጽ አሻራ ማስቀመጥ?
ተጣምሞ ያለፈውን የታሪክ ክስተት የበለጠ ለማጣመም ወይስ በቅን አስተሳሰብ እንዲቃና መጣር?
እንደ ቀደሙቱ ኋላቀር የሆነውን አስተሳሰብ ተከትለን ሁለተኛ ጥፋት ለማምጣት ወይስ እንደተማረው የ21ኛ መ/ክ/ዘ ትውልድ በእውቀት (በሥልጣኔ) የተሻልን መሆናችንን ማስመስከር?
አንድ ሰውስ ‹‹አወቀ›› የሚባለው ታሪክን ስለተማረ ነው ወይስ ባገኘው እውቀት ላይ ተመርኩዞ የመፍትሔው አካል በመሆን የበኩሉን አስተዋጽኦ አበርክቶ ለማለፍ? ወዘተ. የሚሉ ጉዳዮች በውል ሊጤኑ ይገባቸዋል፡፡
በአጠቃላይ የታሪክ ጥቅሙና ዋና ግቡ ካለፉት ክስተቶች ጋር በጥበብ ታርቆ ወደፊት መራመድ እንጂ በየቀኑ እየተላተሙ ሌላ ስህተት መሥራት አይደለም፡፡ የሚያሳዝነው ግን አንዳንድ የሀገራችን መሪዎችና የፖለቲካ አቀንቃኞች ሕዝቡን ከዚህ እውነታ በተቃራኒ አሰልፈው ወደፊት ከማራመድ ይልቅ ‹‹ካለፈው ታሪክ ጋር ጦርነት እንዲገጥሙ›› ይገፋፋሉ፤ የውጭ ታሪክ ምሁራን እንኳን በትዝብት መልክ፡- ‹‹Battling with the Past: New Frameworks for Ethiopian Historiography›› ብለው እስኪጽፉብን ድረስ (Triulzi, Alessandro,2002)፡፡ እናም የጽሑፋችንን መሠረታዊ መልእክት በዚህ የፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም አገላለጽ ለመቋጨት እንሞክር፡- ‹‹የታሪክ ጥቅሙ ያለፉትን ለማወደስም ሆነ ለመውቀስ አይደለም፤ የነበረውን እውነት በትክክል ገልጾ የሚመጣውን ትውልድ ከስህተት ለመጠበቅ ነው እንጂ፡፡ ምክንያቱም የሚያስፈራው ያለፈው ሳይሆን የሚመጣው ነውና!››
ታሪክን በአግባቡ ለመረዳት የሚያግዙ መሠረታውያን
==================================
አንድን ታሪክ በትክክል ለመረዳት የሚያግዙ መሠረታዊ መርሖዎች አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ዋና ዋናዎቹ፡- ጊዜ፣ ቦታና ክስተትን ሳይነጣጥሉ ጉዳዩን በተገቢው ዐውድ ለመረዳት መሞከር የመጀመሪያው ሲሆን ትክክለኛውን የታሪክ ምንጭ (Source) መጠቀም ደግሞ ሌላኛው ነው፡፡ ምንም እንኳን የዚህ ክፍል ጽሑፋችን በእነዚህ ሁለቱ መሠረታዉያን ላይ ትኩረት ቢያደርግም ታሪክን በአግባቡ ለመረዳት ግን አመለካከትን ከማስተካከል ጀምሮ በስሜት ከመነዳት እስከ መቆጠብ ድረስ የሚዘልቁ ከግለሰባዊ ስሜት የዘለቁ ጥንቃቄዎች ያሻሉ፡፡
1) ጊዜ (time)፣ ቦታ (place) እና ክስተት (event)
-------------------------------------------------------
የታሪክ ባለሙያዎች እነዚህን ሦስቱን (ጊዜ ፣ ቦታ እና ክስተት) ‹‹የታሪክ አረዳድ መሠረታውያን›› ይሏቸዋል፡፡ አንድን የታሪክ ጉዳይ ከእነዚህ ሦስቱ ነጥሎ ለማየት መሞከር ምንጊዜም ቢሆን ወደ ስህተት ያመራል፤ በእነርሱ አገላለጽ ‹‹ወንጀልም›› ነው፡፡ ከብዙ ዘመናት በፊት ተከስተው ያለፉትን ታሪኮችን ስናነብ በወቅቱ የነበሩትን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊና ፖለቲካዊ ምህዳሮችን በመረዳት በዚያ ከባቢያዊ ኩነት ውስጥ ራሳችንን በማጥመቅ መሆን አለበት፡፡ አለበለዚያ በነባራዊው እይታና ግንዛቤ የጥንቱን ክስተት ለመመዘን ብንሞክር ‹‹በድሮ በሬ እንደማረስ›› ያለ የአረዳድ ክፍተት ይፈጥራል፡፡ ለምሳሌ፡- በቀደሙት የኢትዮጵያ ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸመ አንድን ጉዳይ በዛሬው የፖለቲካ ቅኝት መዝነን ‹‹ትክክል ነው›› ወይም ‹‹ስህተት ነው›› ብንል የታሪክ ጭብጥ ስህተተኛ ያደርገናል፡፡ ይህ ዓይነቱ ‹‹የታሪክ ስህተት/ወንጀል›› በታሪክ ምሁራኑ ቋንቋ ‘Anachronism’ ይባላል፤ አንድን የታሪክ ክስተት ከተከሰተበት የጊዜ ዐውድ አውጥቶ በማይመለከተው ዘመን ውስጥ መዝፈቅ ማለት ነው [Ana=detach, Chronos= time]፡፡
ዛሬ ላይ ቆመን ባልኖርንት ዘመን መልካምም ይሁን መጥፎ ታሪክ ሠርቶ ያለፈን ሰው ‹‹እንዲህ ማድረጉ ጥሩ ነበር›› አልያም ‹‹ማድረግ አልነበረበትም›› ብለን መፈረጁ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ ለመሰል ጉዳዮች በሚዛናዊነት ፍርድ ለመስጠት የሚያስችለን አድራጊውም ሆነ ድርጊቱ በነበሩበት የጊዜ፣ የቦታና የክስተት ሁኔታ ውስጥ ራስን ማስቀመጥ ሲቻል ብቻ ነው፡፡ የዛሬውንና የትናንቱን አስተሳሰብ፣ የአሁኑንና የጥንቱን ትውልድ እያነጻጸርን ማየት ይከብዳል፡፡ አንድ ግለሰብስ እንኳ በአስተሳሰቡ እየበሰለና እየተሻሻለ ስለሚመጣ ሁልጊዜ እኩል (ወጥ) አቋም አይኖረውም፤ ሊኖረውም አይችልም፡፡ እናም ዛሬ ከትናንትናው ልምድ በመቅሰም ለነገው ሕይወቱ የተሻለ መንገድ መጥረግ ይገባዋል እንጂ በሕጻንነቱ የሠራቸውን ስህተቶች እያሰበ ራሱን ሊወነጅለውና ሊፈርድበት አይገባውም፤ ይህን በማድረጉም አንዳች ጥቅም አያገኝም!
ይህ ሁሉ ሲባል በታሪክ ውስጥ ‹‹መጥፎ ክስተት›› ሊባል የሚችል ምንም የለም ለማለት ሳይሆን ደግም፣ ክፉም ለማለት ፍርዱ እንዲህ ቀላል አለመሆኑን ለማሳየት ያህል ነው፡፡ አሳብ ልንሰጥበት ካስፈለገ እንኳን ዛሬ ላይና እዚሁ ቦታ ተቀምጠን ሣይሆን ተመጣጣኝ ዘመናትን ወደኋላ ተጉዘን እነዚያ የታሪክ ባለድርሻ አካላት በነበሩበት ዐውድ ውስጥ ራስን በማስቀመጥ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ‹‹ካለፈው ታሪክ ጋር በብልጠት መታረቅ እንጂ በሞኝነት አይጋፈጡትም፤…የወደፊቱን እንጂ ያለፈውን ማስተካከል አንችልም›› እንዲል የታሪክ ምሁሩ (ግዛው፣ ታሪክ፣ ትርክትና ታሪካችን፤ 2005:230, 251).
2) ትክክለኛውን የታሪክ ምንጭ (Source) መጠቀም
-----------------------------------------------------------
የታሪክ ማስረጃዎች ከሌሉ ታሪክ የሚባል ስለማይኖር ምንጮቹ በጊዜ ቅደም ተከተል ተሰድረው፣ አስተማማኝ መሆናቸው በታሪክ አጠናን ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ተፈትሾና ተረጋግጦ መቅረብ አለበት፡፡ በዚህ መሠረት ያልተሰናዳ እና ያልተሰነደ ታሪክ ልቦለድ፣ ፈጠራ፣ ፖለቲካ ወይም ስሜት እንጂ ታሪክ አይደለም (ታየ ቦጋለ፤ መራራ እውነት፤ 2011፡ 66)፡፡
የታሪክ መረጃ ምንጮች በርካታ ናቸው፤ የተጻፉም ያልተጻፉም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ስለዚህም እውነተኛ ታሪክ ሊያጠናም ሆነ ሊጽፍ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ትክክለኛውን የመረጃ ምንጭ መጠቀሙን ማረጋገጥ ተቀዳሚ ተግባሩ ማድረግ አለበት፡፡ ከጥሩ ምንጭ ያልቀዳ ሰው ንጹህ ውኃ ያመጣል/ይጠጣል ብሎ ማሰብ ዘበት ነው፡፡ ከድፍርስ ምንጭ በመቅዳት የደፈረሰ ታሪክ መጻፍ የታሪክ ወንጀለኛ ያደርጋል፤ መጪውን ትውልድም መበከል ነውና ኢ-ሥነ ምግባራዊ ነው፤ ለአእምሮም የሚመች አይሆንም፡፡
በታሪካችን ውስጥ ትክክለኛ የመረጃ ምንጭ እጥረት፣ ያለውንም በትክክል ያለመጠቀም ችግርና ከራስ ፍላጎት ጋር የሚስማሙትን ብቻ መርጦ የመጠቀም አባዜ በእጅጉ ይስተዋላል፡፡ በታሪክ ምሁራን ግምገማ መሠረት ለታሪክ መረጃ ምንጭነት ተመራጭ የሚሆኑት ነገሮች የሚከተሉትን መመዘኛ መሥፈርቶች የሚያሟሉ ከሆነ ነው፡-
ሀ) ታሪኩ በተፈጸመበት ቅጽበት (ዘመን) የተጻፈ ከሆነ፡- አንድ ታሪክ የተፈጸመበትና ታሪኩ የሚጻፍበት ጊዜ እየተራራቀ በሄደ ቁጥር የታሪክ ምንጩ (ጽሑፉ) ተዓማኒነት እየቀነሰ ለምሳሌ፡- አንድ ክስተት በተፈጸመበት ዘመን ላይ የኖረና ሳይቆይ በነዚያው ዘመናት ውስጥ ያየውን ጽፎ ያስቀመጠ ሰው ባልነበረበት ዘመን ስለተፈጸመው ክስተት ከሚጽፍ ሰው ይልቅ የተሻለ ተቀባይነት ይኖረዋል፡፡ በሰሚ ሰሚ የሚተላለፉ መረጃዎች ሁሉ ሙሉ በሙሉ ውሸት ናቸው ተብሎ ባይደመደምም እውነታነቱ ግን እየቀጣጠነ ለመሄዱ ምንም ጥርጥር የለውም!
ለ) ቀጥተኛ ተሳትፎ (Direct Experience):- በጉዳዩ ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ የነበረው ሰው የታሪክ መረጃ ምንጭ ሲሆን ተዓማኒነቱ ከፍ ያለ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ፡- በጦርነት ውስጥ ራሱ የተሳተፈ ሰው ወይም ደግሞ በውጊያው ቦታ ተገኝቶ በዓይኑ የተመለከተ ሰው ስለ ጦርነቱ አጠቃላይ ታሪክ ቢጽፍ ያምርበታል፡፡ ‹‹ማን ይናገር? የነበረ፣ ማን ያርዳ? የቀበረ›› የሚለው የአገራችን ነባር ብሂልም ይህንኑ የሚያሳይ ነው፡፡
ሐ) ዕድሜ ጠገብ የታሪክ ክምችቶች (Ancient Archives):- እነዚህ በጽሑፍ የተቀመጡ፣ የቁሳቁስ ቅሪቶች፣ በጥንታዊነታቸውና በታሪክ ማዕከልነታቸው በሚታወቁ ቦታዎች ውስጥ የሚገኙ ማናቸውም ምልክቶች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ቋሚ ምስክርነቶች በአግባቡ ‹‹የሚያናግራቸው›› ባለሙያ ካገኙ አፍ ባይኖራቸውም እውነተኛውን ታሪክ እንደ ስሜታዊው ሰው ሳይጨምሩና ሳይቀንሱ ‹‹አፍ አውጥተው›› የመናገር ብቃታቸው እጅግ ከፍ ያለ ነው፡፡ በተመረጡ ታሪካዊ ቦታዎች የቁፋሮ ምርምሮች (Archeological Investigation) የሚደረገውም ለዚሁ ሲባል ነው፡፡
መ) የታሪክ ጸሐፊዎችን ማንነት ጠንቅቆ ማወቅ፡- ስለተጻፈው ጉዳይ ትክክለኛነት ለመመዘን ልናስተውለው የሚገባን ሌላው ቁልፍ ነጥብ የጸሐፊው ማንነት ነው፤ የጽሑፉ ዓላማና ይዘት በጸሐፊው ዳራ (የአስተሳሰብ ማሕቀፍ፣ የትምህርት ደረጃ፣ የዘውግና የሃይማኖት ተጽዕኖዎች) ይወሰናልና፡፡ የሚጻፉ ጉዳዮች በጸሐፊው ማንነት ተጽዕኖ ሥር የሚወድቁ ከሆነ ደግሞ ተዓማኒነታቸው እጅግ አናሳ ይሆናል፡፡ የዚህን ዝርዝር ጉዳይ ራሱን በቻለ ርእሰ ጉዳይ እንመለስበታለን፡፡
ሠ) አመለካከትን ማስተካከል፡- ከታሪክ መረጃ ምንጭ ጋር የሚያያዘው ሌላው ጉ
ዳይ እኛ ለውጭ (ምዕራባውያን) ጸሐፍት ያለን ልዩ ከበሬታ (ድርድር አልባ ቅቡልነት) ነው፡፡ ይህ ነጮችን ብቻ የሚመለከት ሳይሆን ኢትዮጵያውያን ሆነውም ወይ እዚያ ስለተማሩ ብቻ የምዕራባውያኑን አሳብ ተጭነው የመጡትን ወይም የምዕራባውያንን አስተሳሰብ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ቃል ተቀብለው የራሳቸውን ታሪክ በሌሎች መስታወትነት ለማየት የሚቋምጡትን ሁሉ የሚያጠቃልል ነው (Messay Kebede, Gebrehiwot Baykedagn, Eurocentrism, and the Decentering of Ethiopia, 2006)፡፡ ይህ ሲባል ግን በኢትዮጵያውያን ስለተጻፈ ብቻ አንድ ታሪክ ትክክል ይሆናል ለማለት ሳይሆን ‹‹የአገር ውስጥ›› ስለሆኑ ብቻ ንቀን ሌላውን ማዳነቁ ‹‹በእጅ የያዙት ወርቅ›› ዓይነት እንዳይሆን ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱን የ ‹‹ምዕራባዊነት›› ልክፍት የታሪክ ምሁራኑ ‘Euro-centrism’ ይሉታል (Messay, 2006:816)፡፡ እውቁ ዶ/ር እጓለ ገ/ዮሐንስ ደግሞ ‹‹የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ›› በተሰኘው ድንቅ መጽሐፋቸው ይህንን አካሄድ ‹‹የአውሮፓ መንፈስ›› ብለው ከነቀፉ በኋላ ስለ ኢትዮጵያ ሥልጣኔ ቅ/ያሬድን እንደ ማሳያ አቅርበው የምዕራቡ ከአገርኛው ቢሰናሰል ግን የተሻለ ውጤት ሊያመጣ እንደሚችል ሲያመላክቱ ‹‹በተዋሕዶ ከበረ›› ብለው ቋጭተዋል፡፡
የሚዛናዊነት ‹‹ሚዛን መድፋት›› ለታሪክ ተዓማኒነት
=================================
በ ‹‹ታሪክ›› ስም የተጻፈ ሁሉ ታሪክ ሊሆን አይችልም፡፡ በተለይ ሚዛናዊነቱ በተጨባጭ ማስረጃ ሳይመሰከርለት የተጻፈ ነገር ከታሪክነቱ ይልቅ ‹‹የሀሰት ትርክትነቱ›› ያመዝናል፡፡ ሚዛናዊ ካልሆነ ደግሞ ሐሳዊ ወይም የውሸት ታሪክ (Pseudohistory) መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡
አንድን ታሪክ ‹‹ሚዛናዊ›› ነው ወይስ አይደለም ለማለት ወሳኙ ጉዳይ የሕዝቦች ድምጽ ብልጫ፣ የወጣቶች ጩኸት፣ የሽማግሌዎች ስምምነት አልያም የመንግሥት ድጋፍ አይደለም፤ ከእውነተኛ ምንጭ ተቀድቶ፣ ሙያዊ ሥነ ምግባርን በጠበቀ ባለሙያ ተሰንዶ ያለ መጨመር ያለ መቀነስ እውነታውን ብቻ ሙያዊ በሆነ ትንታኔ እና አጻጻፍ ቁጭ ማድረግ ሲቻል ብቻ ነው እንጂ፡፡
ሐሳዊ ታሪክ ከመደበኛና ተቀባይነት ካለው ትረካ /ትርክት/ ዘዴ ያፈነገጠ አቀራረብ ያለው ነው፡፡ ይዘቱም ቁርጥራጭ የበዛበት፣ ቅንጥብጣቢና ያልተያያዘ ከመሆኑም በላይ ወደ ከፍተኛ የርዕዮት ዓለም ወይም ሀገራዊ ስህተት የሚያመራ ነው፡፡
የታሪክን ሚዛናዊነት ለማስጠበቅ ተግዳሮት ከሚሆኑ እሳቤዎች እና አካሄዶች ውስጥ አንዱ ‹‹ጽንፍን በጽንፍ የማረም›› አካሄድ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- ከዚህን በፊት የነበረው ታሪክ ‹‹ወደዚያ አጋድሎ ነበር›› ብሎ አንዱን ጽንፍ ለማስተካል ሲባል አሁን ደግሞ በሌላ ጽንፍ ‹‹ወደዚህ ያጋደለ›› ታሪክ ለመጻፍ መሞከርን ያካትታል፡፡ የተዛባ ታሪክ አዘጋገብ ካለ ያንን በሳይንሳዊ ጥናት ላይ ተመሥርቶ ሞያዊ በሆነ መልኩ ማረም እንጂ ‹‹ይህ ሕዝብ ወይም ግለሰብ ከዚህን በፊት በታሪክ ውስጥ ጉዳት ደርሶበታልና ለሞራል ካሳ ይሆነው ዘንድ የሚያበረታታ ታሪክ እንጻፍለት›› በሚል ዓይነት ግንዛቤ መሄድ ስህተትን በስህተት ለማረም መሞከር ነው፤ ሞራላዊም አይሆንም፡፡
ታሪክን ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ብቻ መዘገብ ያለብን ‹‹ሞራላዊ›› ስለሆነ ብቻም አይደለም፤ ታሪክ ሲዛባ ነገ ላይ ይዞት የሚመጣው ጦስ ስላለም ጭምር እንጂ፡፡ ከትናንት ይልቅ ነገን መፍራታችን ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ ‹‹ነገን የምንፈራው [ደግሞ] በሁለት ምክንያቶች ነው፡- አንዱ ነገ አዝሎ የሚመጣውን አለማወቃችን ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ነገን በፍላጎታችን መሠረት ለመቅረጽ ችሎታም ሆነ ብቃት እንደሌለን ራሳችንን በማሳመን ነው›› (አዳፍኔ፤ ገጽ.74)፡፡
ምንጊዜም ቢሆን ልዩነት የሚፈጠረው በ ‹‹ታሪክ መሠረታዊ ጭብጥ›› ወይም ‹‹እውነታው›› ላይ አይደለም፤ ያንን እውነታ በምንረዳበት፣ በምንተነትንበት እና በምንዘግብበት ሁኔታ ላይ እንጂ፡፡ እናም ታሪክ ከተጨባጭ ኩነቱ አፈንግጦ በተለያዩ ሰዎች እውቀት ደረጃ፣ ግላዊ ፍላጎትና ፖለቲካዊ ውሳኔ ጋር እየተገናዘበ ከሄደ አደገኛ ይሆናል፤ ታሪክ መሆኑም ይቀርና ተረት ወደመሆን ያጋድላል፡፡
ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው አሁን ያለው ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ›› አተራረክ ሚዛናዊነት ጉዳይ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአንድ አገር ውስጥ ባሉት ዜጎች መካከል እንኳንስ ወጥ የኢትዮጵያ ታሪክ ቀርቶ ‹‹ኢትዮጵያ›› ስለምትባለው አገር እንኳን አንድ ዓይነት ግንዛቤ ለመያዝ ትውልዱ እየተቸገረ ነው፡፡ ይህን መሰል አለመገነዛዘብ የፈጠረው ደግሞ በቀዳሚነት ታሪክ ሚዛናዊነቱን እና ሙያዊ ሥነ ምግባሩን በጠበቀ መልኩ አለመዘገቡ ነው፡፡
ምንም እንኳን ታሪክን ሙሉ በሙሉ እንከን የለሽ ፍጹማዊ ለማድረግ ባይቻልም ፍላጎቱና ገለልተኝነቱ ካለ ተጨባጭ መረጃዎችን ሰብስቦ በማጥናት፣ ከፍጹም ስሜታዊነት በጸዳ መልኩ ሳይንሳዊ ትንተናዎችን በማካተት የተጽኖዎችን ኃይል ቀንሶ በአንጻራዊነት የተሟላ ታሪክ ማቅረብ ይቻል ነበር፡፡ ግን ታሪክ የሚጻፈውና የሚጠናው ለተለያየ ዓላማ ሆነና በ ‹‹ታሪክ›› ስም በርካታ ውሸቶች እየተፈበረኩ፣ ኢ-ሚዛናዊ በሆነ መልኩም በመዘገባቸው ምክንያት ብቻ የሚገዳደሉ የአንድ እናት ልጆችን በየዕለቱ እያስተዋልን ነው፡፡
በጥልቀትና በጥንቃቄ ያልተመረመረ፣ በሚዛናዊነትም ያልተጻፈ ታሪክ የትውልድ ጅምላ ጨራሽ መሣሪያ የመሆን ዕድሉ የሰፋ ነው፡፡ በአባባል ደረጃ፡- ‹‹ነገን የአንተ ለማድረግ ያለፈውን አትዘንጋ›› በተባለው መሠረት ያለፈ ታሪክን መመርመርና መጻፍ የአሁኑን ትውልድ ከጥፋት ሊታደግ ካልቻለ ትርፉ ድካም ብቻ ይሆናል፡፡ በታሪክ ውስጥ ‹‹ሚዛናዊነት›› ሚዛን ሊደፋ (ልዩ ትኩረት ሊሰጠው) የሚገባውም ለዚህ ነው፡፡
አንድ ሰው ታሪክን ለመጻፍ ሲነሣ ከምንም በላይ ሚዛናዊ መሆን አለበት ላልነው ሀሳብ ማጠናከርያ እንዲሆን የታሪክ ምሁሩ ባህሩ ዘውዴ (ፕሮፌሰር ኤምረተስ) በቅርቡ ‹‹የታሪክ አጻጻፍና አጠናን›› በሚል በተዘጋጀው ሕዝባዊ ገለጻ (Public Lecture) ላይ ከተናገሩት አንዱን እንደ ማሳያ እናቅርብ፡፡ አሁን ባለው ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ አጻጻፍ›› ትርክቶች ውስጥ አንደኛው ጽንፈኛ ቡድን ንጉሥ ምኒልክን ‹‹እምዬ፣ መልአክ ነው!›› እያለ ሲያሞካሽ ሌላኛው ጽንፈኛ ቡድን ደግሞ ‹‹ጭራቅ ነው!›› እያለ ይጽፋል፡፡ ታሪክ ሚዛናዊ ሆኖ ይጻፍ ከተባለ ግን ‹‹ምኒልክ ሰው ብቻ እንጂ መልአክም፣ ጭራቅም አይደሉም!›› ሰው ከሆኑ ደግሞ እንደሰው የተሳሳቷቸው ስህተቶቻቸውም፣ እንደ ሰው ያከናወኗቸው መልካም ተግባሮቻቸውም በታሪክ መጻፍ ይኖርባቸዋል፤ በዚህ ትውልድ ዘንድ የታሪክ ድርጊት ስህተቱ ይታረም፣ መልካምነቱ ይቀጥል ዘንድ፡፡ ታሪክን ስናጠና፣ ስንጽፍና ስንረዳ ሚዛናዊነት ራሱ ‹‹ሚዛን ይድፋ!›› የምንለውም ለዚሁ ነው፡፡
የታሪክ ጸሐፊዎች ሰብእና በታሪክ እውነትነት ላይ ያለው ተጽእኖ
==================================
የአንድን ታሪክ እውነተኛነት ለመመዘን ከሚያግዙን ቁልፍ ነጥቦች መካከል ታሪኩን የጻፉ ወይም የተናገሩ ሰዎችን ማንነት (ዳራ) በጥንቃቄ መመርመር ነው፡፡ በተለይ በዘውግ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ እና መሰል ጫናዎች ውስጥ ሆነው ሲጽፉ ዋናውን የታሪክ ጭብጥ የማዛነፍ እድላቸው ከፍተኛ ይሆናልና፡፡ ‹‹ስለታሪኩ ጸሐፊ ማንነት አስቀድሞ ማወቅ ስለተጻፈው ጉዳይ እውነተኛነት ለመመዘን መንገድ ይጠርግልናል›› እንዲል (Edward Carr, What Is History? 1961)፡፡ በዚህ ጽሑፋችንም ልናስገነዝብ ያሰብነው የታሪክ ሚዛኑ በታሪክ ጸሐፊዎቹ ሰብእናም እንደሚወሰን፣ ታሪክን ስናጠናም ከዚሁ አኳያ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባን ለማሳየት ነው፡፡ ለመሆኑ ታሪክን የሚጽፉ ሰዎች ምን ዓይነት ሰብእና እንዲላበሱ ይጠበቃል? (ጥቂቶቹን እንደሚከተለው እንመልከት)
1) ከራስ ፍላጎት ነጻ መሆን፡-
-----------------------------------
ሰዎች የመጻፍ አቅምና ፍላጎት ስላላቸው ብቻ ታሪክን ሊጽፉ አይችሉም፤ በእንደዚህ ዓይነቱ ጉዳይም መደፋፈር አይገባቸውም፡፡ ታሪክ የግላዊና የራስ አድልዎ ስሜትን በመቆጣጠር በምርምር ተደግፎ ከጽሑፍም፣ ከሰውም ሆነ ከቁስ አካል የሚገኘውን መረጃ አንጥሮ በማውጣትና በዚህም ትራስ ድርጊቶችንና ገድሎችን የሚያፍታታ፣ ያለፈውን በማብራራት ለወደፊቱም የሀገርና የዜጎች እጣ ፈንታ ፋና ወጊ የሆነ ዕውቀት የሚሰጥበት የትምህርት ክፍል ነውና፡፡
እናም ከሁሉ በፊት የወገንተኝነት አስተሳሰብ፣ የግል አመለካከትና የውስጥ ምኞት ከአንድ የታሪክ ጸሐፊ ሊርቁ የሚገባቸው መሰናክሎች ናቸው፡፡ ‹‹ታሪክን ለመጻፍ የሚያስብ አንድ ሰው ቤተ መጻሕፍት ከመግባቱ በፊት የራሱን አቋምና የውስጡን ፍላጎት በሙሉ አሽቀንጥሮ መጣል ይኖርበታል፤ አለበለዚያ ግን በእውነተኛው ሚዛን ለመራመድ ይቸገራል›› እንደተባለው (Hobsbawm, Eric. Nations & N ationalism Since 1780, Cambridge University Press 1990:3)፡፡
2) ሦስቱ ‹‹ተሰጥዖዎች››፡-
---------------------------------
ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ የተባሉ ጸሐፊ "መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር" በሚለው መጽሐፋቸው (በ1916ዓ.ም ታትሞ የነበረ፣ በድጋሚ በ2003 ዓ.ም በታተመው ገጽ 3-5 ላይ) እንደሚገልጹት፡-
እውነተኛ ታሪክ ለመጻፍ ቀላል ነገር አይደለም፡፡ የሚከተሉትን ሦስት የእግዚአብሔር ስጦታዎች ያስፈልጋል፡፡ መጀመሪያ ተመልካች ልቦና፡- የተደረገውን ለማስተዋል፤ ሁለተኛ የማያዳላ አእምሮ፡- (ያለ ወገንተኝነት) በተደረገው ለመፍረድ፤ ሶስተኛ የጠራ የቋንቋ አገባብ፡- የተመለከቱትን የፈረዱትን /በትክክል/ ለማስታወቅ፡፡ ያገራችን የታሪክ ጻፎች ግን በእነዚህ ነገሮች ላይ ኃጢአት ይሰራሉ፡፡ በትልቁ ነገር ፋንታ ትንሹን ይመለከታሉ፣ ለእውነት መፍረድንም ትተው በአድልዎ ልባቸውን ያጠባሉ፤ አጻጻፋቸውም ድብልቅልቅ እየሆነ ለአንባቢው ግልጽ አይደለም፡፡
3) ስለሚጽፈው ጉዳይ ያለው ቅርበት እና ግንዛቤ፡-
----------------------------------------------------------
ታሪክን ለመጻፍ የሚነሳ ማንኛውም ሰው አስቀድሞ ስለሙያው በቂ እውቀት ሊኖረው ይገባል፤ ይህ በታሪክ የትምህርት ዘርፍ ‹‹መመረቁን›› ብቻ ለመጥቀስ ሳይሆን በትክክል ስለታሪክ ‹‹ማወቁን›› ለማስመር ነው፡፡ ስለሚጽፈው ጉዳይም ቅሩበ-ክስተት (occasion proximate) መሆን ይጠበቅበታል፤ በተጨባጭ ከሚያውቀው ሐቅ ጋር ለማመሳከር ያስችለው ዘንድ፡፡ ለምሳሌ፡- ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ ስለአገሩና ሕዝቡ ተጨባጭ ሁኔታ ከማያውቀው የውጭ ዜጋ ይልቅ አብሮ የኖረና የሕይወት ተሞክሮም ያለው ኢትዮጵያዊ ቢጽፍ የተሻለ ሊሆን ይችላል፤ የራሱን ሕዝብ ታሪክ ‹‹ለማሳመር›› ብሎ እንዳይጽፍ ግን እየተጠነቀቀ፡፡ ‹‹ቅርበት›› ሲባል ግን የግድ ኢትዮጵያ ውስጥ የተወለደ፣ ኢትዮጵያዊ የሆነ ማለት አይደለም፡፡ ምክንያቱም፡- ኢትዮጵያዊ ሳይሆኑ፣ ነገር ግን ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ በጥንቃቄ እና በጥልቀት አጥንተው ከመጻፍም በላይ መላ የሕይወታቸውን ትኩረት በኢትዮጵያ ጥናት ላይ ያደረጉ እንደ እንግሊዛዊው ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ያሉ ጥቂት የውጭ ዜጎች መኖራቸውንም ልንዘነጋ አይገባም፡፡
4) ከሙያዊ ሥነ ምግባር አንጻር፡-
-----------------------------------------
አንዳንዶች ደግሞ ሞያው ሳያኖራቸው ቀርቶ ሳይሆን ሞያቸውን ራሱን ለተንኮል እና ለሤራ ይጠቀሙበታል፤ ታሪክን አጣምሞ እና በርዞ በመጻፍ፡፡ በታሪክ አጠናን ሂደት ‹‹ሐሳዊ ታሪክ›› (Pseudohistory) የሚባለውም መሰል የአጻጻፍ ሁኔታዎችን ለመግለጽ ነው፡፡ አካዳሚያዊ መለኪያው ሳይጠበቅ ወይም ሳይሟላ ቀርቶ ጭፍን፣ ተቃራኒና ጽንፈኛ አቋም ይዞ መቅረብ የራስን ፍላጎትና እምነት ብቻ በታሪክ አጻጻፍ ላይ አስርጎ ማስገባት የአድልኦና የወገናዊነቱ መንፈስ ስለሚጫነው ኢ-ታሪካዊ ወይም ሐሳዊ ታሪክ (Pseudohistory) ወደ መጻፍ ያደርሳል፡፡
አንዳንድ ጸሐፊዎች ደግሞ ረቂቅ በሆነ ዘዴ የሚፈልጓቸውን ማስረጃዎች ብቻ እየለቀሙ በጥንቃቄ ስለሚያሰናዱት ሐሳዊነቱ ለተራ አንባቢ በቀላሉ ላይከሰት የሚችልበት አጋጣሚ አለ፡፡ ዋናው ግባቸው ታሪክን ለሚፈልጉት ዒላማ መጠቀም ስለሆነ ሐሰቱን ጭምር እውነት እንደሚመስል አድርጎ መተረክ የተካኑበት ነው፡፡
በነጭ ልክፍት ክፉኛ የተያዙ ‹‹የታሪክ›› ጸሐፍትም አይጠፉም፡፡ እነርሱ የሚገዙት ለሞያቸው ሣይሆን ከእነርሱ የፊት ቀለም ለተለየና ‹‹በሰለጠነው ዓለም›› ለሚኖር ጸሐፊ ነው፤ ከጉዳዩ ጭብጥ ይልቅ የመረጃቸውን ምንጭ በዚህ ይመዝኑታል፡፡
ለጥቅም ፍለጋ ሲሉ ስፖንሰር ያደረጓቸውን ወይም ሌላ ውለታ ሊውሉላቸው ቃል የገቡላቸውን አካላት ለማስደሰት ሲሉ ‹‹ታሪክ›› ብለው የሚጽፉትም ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡ እነዚህ ‹‹ውሻ በበላበት ይጮሃል›› የሚለው ብሂል በደንብ ይገልጻቸዋል፡፡ በመሠረቱ ‹‹ታሪክ›› ሆኖ መጻፍ ያለበት እነዚህ ሰዎች የሞነጫጨሩት ሣይሆን ሰዎቹ በታሪክ ስም የሚነግዱት ንግድ ነው፡፡ ታሪክ ግን በየትኛውም ተጽዕኖ ሥር ተኩኖ የሚጻፍ ሣይሆን አስቀድሞ ራስን ከመሰል አስተሳሰቦችና የጥቅም ቁርኝቶች ነጻ አውጥቶ ሌላውን በእውነተኛው መረጃ ከሀሰት ትርክት ነጻ ለማውጣት የሚጻፍ ነው፡፡
5) ከስሜታዊ አተረጓጎም ይልቅ ትኩረት ለምሁራዊ ትንተና
---------------------------------------------------------------------
ታሪክን መረዳትና መጻፍ ‹‹ለእውነት መገዛትን›› ይፈልጋል፤ በድጋፍም ሆነ በጭፍን ጥላቻ ተሞልቶ ታሪክን ለመጻፍ መሞከር የሠለጠነ አካሄድ አይደለም፡፡ አንዳንድ ሰዎች ግን የነበረውን ታሪክ ትተው የራሳቸውን ፍላጎትና ምኞት ይጽፋሉ፤ በስሜት መነዳት (sensual drive) ማለት እንዲህ ዓይነቱ ነው፡፡ ታሪክ በራሱ ተጨባጭ እውነታ (objective reality) ነው፤ ነገር ግን ጸሐፊዎች ብዙውን ጊዜ የራሳቸውን የተዛባ የግል ትንታኔ (distorted subjective analysis) ሲቀላቅሉበት ይስተዋላል (Kim, Ji Yang. National Historiography of Ethiopia .2010:1)፡፡ ይህ እውነታ በድንቅ አገላለጽ እንደሚከተለው ተገልጾአል፡-
‹‹ታሪክ እርጉዝ ነው፤ አንድ የታሪክ ጸሐፊ አንድን ጉዳይ ራሱ
እንደተረዳውና አንዲሆን በተመኘው ልክ እንዲሁም በራሱ የግንዛቤ ደረጃ ትርጉም መስጠት ሳይሆን በቂ የአዋላጅነት እውቀትና ልምድ ሊኖረው ይገባል ((ግዛው፣ ታሪክ፣ ትርክትና ታሪካችን፤ 2005: 79)፡፡
እነርሱ ያሰቡትን አሳብ ሌላው በቀላሉ እንዲቀበላቸው ሲፈልጉ በደፈናው ‹‹ታሪክ እንዲህ ይላል›› የሚሉ አሉ፤ በየትኛው መጽሐፍና ገጽ ላይ ይህ እንደተገለጸ ግን አይጠቅሱም፡፡ ምናልባት ከጠቀሱም ደግሞ መጽሐፉ የሚለውን በትክክል ከመጻፍ ይልቅ በራሳቸው ቃላትና ትንታኔ ቃኝተው ያንሻፍፉታል፡፡ ‹‹እንዲህ ማለቱ ነው›› ብለውም የራሳቸውን የተዛባ ብያኔ (distorted interpretation) ሲያስቀምጡ የመደበኛውን ጸሐፊ አቅጣጫ አስተው ወደ ራሳቸው ምኞት ለመሳብ ይጥራሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ የታሪክን ምንጭ አላግባብ መጠቀም (abusing historical sources) ነው፡፡
ሌሎች ደግሞ በግል ምርጫ ላይ ተመርኩዘው ከታሪክ መረጃ ምንጮች ውስጥ የሚፈልጉትን (የእነርሱን አሳብ የሚደግፈውን) ብቻ በመምረጥ ይቀበላሉ፤ አሳባቸውን የሚሞግት (የሚቃወም ሲኖር ደግሞ ይንቃሉ፡፡ ይህም ለታሪክ እውነታ የመገዛት ሳይሆን በታሪክ ስም የግልን ስሜትና ፍላጎት ማርካት ነው፡፡ በአንድ ምሁር እንዲህ ተገልጾአል፡- ‹‹በዚህ ዘመን የመጡ የታሪክ ጸሐፊዎች ብዙዎቹ ስሜት-ተኮር (emotionally-bound) ታሪክ ይጽፋሉ፤ ‹ኢትዮጵያ› የሚሏትም እነርሱ ሊያዩ የሚፈልጓት ናት እንጂ በተጨባጭ ያለችዋን አይደለም›› (Triulzi, Alessandro. Battling with the Past: New Frameworks for Ethiopian Historiography. 2002:279)፡፡
6) መሥዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀት፡-
-----------------------------------------------
በመጨረሻም፡- አንድ ሰው ታሪክ ለመጻፍ ሲነሣ የሆነ ድርሰት እንደሚያደራጅ ብቻ አድርጎ ማቅለል የለበትም፤ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር፣ ሕዝቡንም እንደ ማኅበረሰብ የማቆም አለማቆም ያህል ትልቅ ጉዳይ ስለሆነ፡፡ እናም እውነተኛና ‹‹ውኃ የሚያነሣ›› ታሪክ ለሕዝብ ለማቅረብ መሥዋዕትነትን ይጠይቃል፡- ራስን ማሸነፍ፣ ሥልጣን ያላቸውን ባለመፍራት ለእውነት መቆምና ከትክክለኛው ምንጭ መቅዳት፡፡ ታሪክን የሚጽፍ እውነታን ብቻ ቢያንጸባርቅ ሌላ ታሪክ ይሰራል፤ አለበለዚያ ግን ‹‹ሆዱን ለመሙላት ብሎ የሞላውን ታሪክ ቢያጎድል›› በምድር ታሪክ ራሱ፣ በሰማይ ደግሞ በታሪክ ስም ፍጡራኑ በግፍ የተገደሉበት እግዚአብሔር ይጠይቀዋል፡፡
No comments:
Post a Comment