Saturday, 12 February 2022

የ"ቶ" ፊደል ምስጢር እና ታሪክ

የ "ቶ" ፊደል የተፈጠረዉ አለም ሲፈጠር ነዉ። የሰዉ ልጅ የተፈጠረዉ በ"ቶ" ቀመር መሆኑ አጀብ ያስብላል። በግዕዝ የፊደል ስርአት መሰረት (ተ ቱ ቲ ታ ቴ ት ቶ) "ቶ" ሰባተኛዋ ፊደል ነች። ሰባት ቁጥር ብዙ ትርጉምና ምስጢር አለው፡፡ ሰባት ቁጥር በቤተክርስትያን ፍፁምነትን ይወክላል።

Friday, 4 February 2022

ካልተጻፈ ታሪክ የለም! ወደ ማይጠየፈን አይጠየፍ፤ የንጉስ ሚካኤል መንደር ደሴ ላኮመልዛ ወይራ አምባ

 


ሚካኤል “አባ ሻንቆ” photo credit ሽፍታ

በዛሬዋ ዕለት ጥር 27/1842 ዓ.ም ራስ ሚካኤል “አባ ሻንቆ” ከዛሬዋ ደሴ ላኮመልዛ  በፊት ደግሞ  ወይራ አምባ ከሰሜኗ  የፍቅር ከተማ ክፍለ ሀገር ተንታ ተወለዱ። 

ደሴ  እንኳን ለሀገሬ ሰው ይቅርና በ7ኛው ክፍለ ዘመን ከአርመን ተሰደው ለመጡ ክርስቲያኖች መጠጊያ፤ ሰው እምነቱ  እርስ በእርስ የማይባላባት፤ ሙስሊም ክርስቲያኑ የሚለው የወግ ማዕረግ በተግባር የሚታይባት የፍቅር ተምሳሌት ከተማ፤ እስላም ክርስቲያኑ፣ በረኸኛው ከደገኛው፣ ብሔረሰብ ሕዝቡ፣ ተፈጠሮና ሰው… ሁሉም በፍቅር የሚኖሩባት ምድር ደሴ። 

Monday, 31 January 2022

ባርነትን የመረጠ የሚመክተው ጋሻ የሚጠጋበት ዋሻ የለውም

አንዱዓለም አስናቀ (የ'የሽወርቅ ልጅ)

የዜግነት ክብር በኢትዮጵያችን ፀንቶ የሚለው  የኢትዮጵያ ህዝብ ብሔራዊ መዝሙር እንዲዘመር እንጅ እንዲከበር በመንበረ ብልጽግናም ዛሬም አልተፈቀደም።  ስለዲሞክራሲ ብዙ ሲነግረን የኖረው መንበረ-ኢህአዴግ  የሚናገርለት ዲሞክራሲ በተግባር ሲታይ  አፈና ድብደባ እስርና ግድያ ሆኖ ቆይቷል። የግፍ አጥቢያው  ወንበረ-ብልጽግና ተግባራዊ ዲሞክራሲን ከኢህአዴግ አስበልጦ በወንበዴዎቹ በትምክተኝነት የህዝብን ሉአላዊነት በመንጠቅ  ጋዜጠኞችን  እንዲሁም የእውነት ታጋይዎችን ማሰሩን  ግድ ሆኖበታል ውርስ ነውና።  

በወያኔ ጎዳና ብልጽግና ዛሬም ውሸት ይናገራል (2.2 ቢልየን ብር) ለአንድ ህንጻ ማደሻ ይውላል። በወያኔ ዝማሬ ሁሉም ነገር ኢትዮጵያ እንዳደገች ህዝቡ ተለውጦ የድህነትን ሸማ አስፈንጥሮ እንደጣለ ህዝቡ ያሻውን መናገር እና ማድረግ እንደቻለ ዘወትር እንሰማለን፤ ግን በተግባር ግን በአስለቃሽ ጭስ ተቆልተን በጥይት እናራለን።  

በመንበረ ብልጽግና በጧትና በማታ  በዘወትር መልእክቱ  ሀገር በለፀገ ህዝብ ተለወጠ የሚል ድስኩሩን በሆድ አደር ሚዲያዎች እንሰማለን፤ እኛ ግን የቀን ስራ ሰርተን ዳቦ መግዛት ቸግሮናል፤ 30 ቀን ዘምተን የቤት ኪራይ መክፈል አቅቶናል፤ በቀላጤው ወንድማችን ሸኔ  (በኦነግ) መከራችን በየቀኑ ይጨምራል።  

ዛሬም በህወሃት ችግራችን እንዲያገረሽ  እንጂ እንዲቀንስ አይፈለግም።  በመንበረ ብልጽግና ለጥቂቶቹ ሀገራችን ገነት ሆና ሲደላቸው ሲመቻቸው  ብዙሀኑ ግን በችግርና በረሀብ መማቀቁን ህይዎቱን ቀጥሎበታል። እናም ኤሎሄያችን ጩህታችን ዛሬም ያስተጋባል። ለኢትዮጵያ ትንሳኤ ለፍትህ፣ ለእኩልነት ለነፃነት  እንደ ህዝብ ካልታገልክ ባርነትን ከመረጥክ የምትመክተው ጋሻ የሚ የምትጠጋበት  ዋሻ የለህም።

Friday, 28 January 2022

ጥር 21 የእመቤታችን በዓለ ዕረፍት

ጥር 21 በዓለ አስተርእዮ (የእመቤታችን በዓለ ዕረፍት)

እንኳን ለዚህች ታላቅ በዓሏ አደረሰን፡፡ 

ወላዲተ አምላክ ምንም እንኳን የአምላክ እናት ብትሆንም ሞተ ሥጋ ለሁሉም ዕጣ ፈንታ በመሆኑ በስድሳ አራት አመቷ ከሞት ወደ ሕይወት ከመከራ ወደ ደስታ የተሸጋገረችበት ዕለት ነው፡፡
ታላቁ የቤተክርስቲያን አባት ቅዱስ ያሬድም “ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የአጽብ ለኩሉ” ትርጉሙ ሞት ለማናኛቸውም ሰው ሁሉ የተገባ ነው የማርያም ሞት ግን ሁሉን ያስደንቃል፡፡ በማለት አደነቀ፡፡ በመሆኑም በዓሉ የወላዲተ አምላክ በዓለ ዕረፍት ከመሆኑ የተነሳ ታላቅ በረከት የሚያስገኝ ስለሆነ በየዓመቱ ይከበራል፡፡

Wednesday, 19 January 2022

ቃና ዘገሊላ



 ‹‹ቃና ዘገሊላ›› ምንድነው?

ቃና ዘገሊላ በቀጥታ ትርጉም የገሊላዋ ቃና ማለት ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን አስተምህሮ በጥምቀት በዓል ማግስት(ጥር 12) ቀን የቃና ዘገሊላ በዓል ይከበራል፡፡ ይህ በዓል ከጌታ ጥምቀት በዓል ጋር ተያይዞ በድምቀት የሚከበር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዳራ ያለው በዓል ነው፡፡ በዓሉ ቃና ዘገሊላ የሚል ስያሜ ያገኘው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የገሊላ ሀገር ክፍል በምትሆን ቃና በተባለችው ቦታ በፈፀመው ተአምር መነሻነት ነው፡፡ የቃና ዘገሊላ ጥንተ ነገሩ ወይም ታሪኩ የተፈፀመው የካቲት 23 ቀን ነው፡፡ ነገር ግን አባቶቻችን የውኃን በዓል ከውኃ በዓል ጋር ለማክበር ብለው የየካቲቱን በዓል ወደ ጥር 12 አምጥተውታል፡፡ ይህም ውኃ ወደ ወይን የተለወጠበትን በዓል ከጌታ ጥምቀት በዓል ጋር ለማስተሣሠር ለማስኬድ ነው፡፡ በመሆኑም የቃና ዘገሊላ በዓል ጥር 12 ቀን ይከበራል፡፡

Tuesday, 18 January 2022

ገሀድ፣ ከተራ እና የጥምቀት በኢትዮጵያ


═════ ❁ ═════

ገሀድ :

➢. ገሃድ የቃሉ ትርጉም መገለጥ መታየት ነው፡፡ በጥምቀት መገለጥ መባሉ ሰው የሆነው አምላክ በዓለም ሲኖር እስከ 30 ዓመት እድሜው ድረስ ሰዎችን ለማዳን የመጣ መሲህ ሰው የሆነበት፣ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ እሱ መሆኑን ሳያውቁ ከኖሩ በኃላ በ 30 ዓመት እድሜው በባሕረ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ እጅ ሲጠመቅ አብ በደመና ሆኖ ‹‹የምወደው ልጄ ይህ ነው›› በማለቱ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል በራሱ ላይ ሲያርፍ በመታየቱ ነቢያት ይወርዳል ይወለዳል ይሰቀላል ይሞታል ይነሳል ብለው የተናገሩለት መሲሕ እርሱ መሆኑ ተገልጦአልና እንዲሁም ሦስቱ አካላት በአንድ ጊዜ ታይተዋልና ምስጢረ ሥላሴ የተገለጠለት በመሆኑ ገሃድ ይባላል፡፡(ማቴ 3፡13-17)