ምዕራፍ1፡ የ666 እና የአውሬው ምንነት
📌 የ666 ትርጉም፡-
በመጀመሪያ ደረጃ፣ 666 ቁጥር ከክርስትና መጽሐፍ ቅዱስ የመጣ ነው። የዮሐንስ ራእይ 13:18 "ጥበብ ያለው ሰው አውሬውን ቁጥር ያስብ፤ ቁጥሩ ደግሞ የሰው ቁጥር ነውና፤ ቁጥሩም ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት (666) ነው።" በራእዩ ውስጥ፣ "አውሬ" የሚለው ቃል የሐሰት ነቢይ ወይም ፀረ-ክርስቶስ (AntiChrist) ማለት ነው። ስለዚህ 666 የፀረ-ክርስቶስ ምልክት ወይም "ቁጥር" ነው። ይህ ክፉ፣ ከእግዚአብሔር ጋር የሚቃረን ኃይልን ያመለክታል።
ከስሙ ትርጉም ስንነሳ፤ እነዚህ ሦስት ስድስቶች ምንድን ናቸው? በብዙ መልኩ ሊቃውንት አባቶቻችን ቢተረጉሙትም ለግንዛቤ ያህል ሁለቱን ጠቅሼ አልፋለሁ።
✔ 1ኛ... 666 ማለት፤ የመጀመሪያው 6 የሚወክለው የሰው ልጅ የተፈጠረበትን ቀን ነው። ይህም ስድስተኛው ቀን ነው። ሁለተኛው 6 የሚወክለው የቀትር አጋንንት (ማለትም የአየር ላይ አጋንንት) ከሰማይ ወደ ምድር የተበተኑበትን ሰዓት ይወክላል። ሦስተኛውና የመጨረሻው 6 ደግሞ የሚወክለው፤ መድሀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት፣ ጠላት ዲያቢሎስ ድል የተነሳበት፣ ነፍሳት ከሲኦል የወጡበት ሰዓት ስለሆነ በዋናነት እነዚህን ሦስት ስድስቶችን የያዙትን ጊዜአት እንደሚቃወም ለመግለፅ ራሱን በሦስት ስድስቶች (666) ወከለ በማለት ሊቃውንት አባቶች ያመሰጥሩታል።
✔ 2ኛ.... 666 ምንድን ነው ለሚለው ደግሞ፤ አባቶቻችን በጥንት መፅሐፍቶች ላይ ከትበውልን እንዳለፉት፤ ሦስት ስድስቶች የሆኑበትን ምክንያት 'ሥላሴን እቃወማለሁ' ማለት ነው ይላሉ። እንዴት ቢሉ፤ ሥላሴ ማለት 'ሠለሰ' ከሚለው የግዕዝ ግስ የወጣ ሲሆን 'ሦስት አደረገ፣ ሦስት' የሚል ትርጉም አለው። የሥላሴ ሦስትነት ምን አይነት ሦስትነት ነው ቢሉ መልሱ ልዩ ሦስትነት ነው። የስድስቶች ብዛት (666) ሦስት የሆነበት ምክንያት አንድም የሥላሴን ልዩ ሦስትነት እቃወማለሁ ሲል ነው ይላሉ።